በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጥፋት ቀን ሰዓት ጋር በተያያዘ የሚሰጡት መላ ምቶች ፍጻሜያቸውን ሊያገኙ አይችሉም፤ ምክንያቱም አምላክ ምድርንም ሆነ የሰው ልጆችን በተመለከተ ብሩህ ተስፋ ሰጥቷል

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ የሚገኝበት አሳሳቢ ሁኔታ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት ተነግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ወደፊት ብሩህ የሆነ ጊዜ እንደሚጠብቃቸውም ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚናገረውን ነገር ውድቅ ለማድረግ መቸኮል ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም ዝርዝር መረጃ የያዙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በአስደናቂ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተመልከት፦

  • “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል።”—ማቴዎስ 24:7

  • “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4

እነዚህ ትንቢቶች በአንዳንዶች አመለካከት ከቁጥጥር ውጭ የሆነውን ዓለም ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። በአንድ በኩል ሲታይ በእርግጥም ዓለማችን ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም የዓለም ሁኔታ ከሰው ልጆች ቁጥጥር ውጭ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው የሰው ልጆች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል ጥበብም ሆነ አቅም የላቸውም። የሚከተሉት ጥቅሶች ይህን በግልጽ ያሳያሉ፦

  • “ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።”—ምሳሌ 14:12

  • “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።”—መክብብ 8:9

  • “[ሰው] አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።”—ኤርምያስ 10:23

የዓለም ሁኔታ በዚሁ እንዲቀጥል ከተተወ በምድራችን ላይ ዓለም አቀፍ ጥፋት የሚከሰትበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ሁኔታ ፈጽሞ አይከሰትም! ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጣል፦

  • “[አምላክ] ምድርን በመሠረቶቿ ላይ መሠረታት፤ እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም።”—መዝሙር 104:5

  • “ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4

  • “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

  • “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የማያሻማ መልስ ይሰጣሉ። የሰው ዘር በአየር ብክለት፣ በምግብና በውኃ እጦት ወይም በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት ከምድር ገጽ ተጠራርጎ አይጠፋም። በኑክሌር ፍንዳታም ቢሆን ይጠፋል ብለን የምንሰጋበት ምንም ምክንያት የለም። ለምን? ምክንያቱም የፕላኔታችን የወደፊት ዕጣ በአምላክ ቁጥጥር ሥር ነው። እርግጥ ነው፣ አምላክ ለሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል፤ ሆኖም ያደረጉት ውሳኔ የሚያስከትልባቸውን መዘዝ ማጨዳቸው አይቀርም። (ገላትያ 6:7) እንዲህ ሲባል ግን ዓለማችን ከሹፌሩ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነና ለከባድ አደጋ መዳረጉ እንደማይቀር ባቡር ሆኗል ማለት አይደለም። አምላክ ያስቀመጠው ድንበር ወይም ገደብ ስላለ የሰው ልጆች በራሳቸው ላይ ከልክ ያለፈ ጉዳት ሊያደርሱ አይችሉም።—መዝሙር 83:18፤ ዕብራውያን 4:13

ይሁን እንጂ አምላክ ከዚህም የበለጠ ነገር ያደርጋል። በዓለማችን ላይ “ብዙ ሰላም” እንደሚያሰፍን ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:11) በዚህ ርዕስ ውስጥ የተገለጹት ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቁ ትንቢቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በመማራቸው ካገኟቸው በርካታ አስደሳች ተስፋዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

የይሖዋ ምሥክሮች፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና የተለያየ ብሔር ያላቸው ወንዶችንና ሴቶችን ያካተተ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ ይሖዋ እንደሆነ የተገለጸውን እውነተኛውን አንድ አምላክ ያመልካሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ፍርሃት አያድርባቸውም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይላል፦ “ሰማያትን የፈጠረው፣ እውነተኛው አምላክ፣ ምድርን የሠራትና ያበጃት፣ አጽንቶም የመሠረታት፣ መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ ያልፈጠራት ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።’”—ኢሳይያስ 45:18

በዚህ ርዕስ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ምድርንና የሰው ልጆችን በተመለከተ የሚያስተምራቸውን አንዳንድ ትምህርቶች ተመልክተናል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለውን ብሮሹር ትምህርት 5 ተመልከት። ብሮሹሩን www.jw.org/am ላይ ማግኘት ትችላለህ

በተጨማሪም www.jw.org/am ላይ የሚገኘውን አምላክ ምድርን የፈጠረው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ መመልከት ትችላለህ (የሕትመት ውጤቶች > ቪዲዮዎች በሚለው ሥር ይገኛል)