የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?

መልሱ የሚገኘው ከየት ነው?

መልሱ የሚገኘው ከየት ነው?

ከየአቅጣጫው የሚሰማው መጥፎ ዜና አስፈርቶህ ምናልባትም ሽብር ለቆብህ ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በ2014 በወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት የነበሩት ባራክ ኦባማ፣ በዜና ማሰራጫዎች በሚተላለፉት መጥፎ ዜናዎች ምክንያት በርካታ ሰዎች “ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት . . . እየተሽከረከረ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ሊቆጣጠረው አይችልም” የሚል መደምደሚያ ላይ እንደደረሱ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ይህን ሐሳብ ከተናገሩ ብዙም ሳይቆይ ፕሬዚደንቱ በዓለማችን ላይ ያሉትን አብዛኞቹን ችግሮች ለማስተካከል ስለተያዙት ዕቅዶች በጋለ ስሜት ተናግረዋል። መንግሥት የወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች “የምሥራች” እንደሆኑ ከገለጹ በኋላ “ተስፋ አለኝ” እንዲሁም “ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ የሆነ ነገር ይታየኛል” ብለዋል። በሌላ አነጋገር ሰዎች በበጎ ዓላማ ተነሳስተው የሚያደርጉት ጥረት የዓለምን ሁኔታዎች ለመቆጣጠርና ዓለም አቀፋዊ ጥፋት እንዳይደርስ ለመከላከል እንደሚያስችል መጠቆማቸው ነው።

በርካታ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዲህ ያለ ብሩህ አመለካከት አላቸው። ለምሳሌ አንዳንዶች በቴክኖሎጂ መስክ የሚደረገው ፈጣን እድገት የዓለምን ችግሮች ያስወግዳል ብለው ስለሚያስቡ ተስፋቸውን በሳይንስ ላይ ይጥላሉ። ስለ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ በ2030 “ቴክኖሎጂያችን አሁን ካለው አቅም አንድ ሺህ እጥፍ፣ በ2045 ደግሞ አንድ ሚሊዮን እጥፍ ያድጋል” በማለት በእርግጠኝነት ተንብየዋል። አክለውም “በጣም ጥሩ እድገት እያደረግን ነው። የተጋረጡብን ችግሮች የአሁኑን ያህል ከባድ ሆነው ባያውቁም ችግሮቹን የመፍታት አቅማችን ከችግሮቹ ክብደት አልፎ ሄዷል” ብለዋል።

ለመሆኑ ዓለም የሚገኝበት ሁኔታ ምን ያህል የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል? በእርግጥ የሰው ዘር ዓለም አቀፋዊ ጥፋት ተጋርጦበታል? አንዳንድ ሳይንቲስቶችና ፖለቲከኞች ተስፋ ያዘለ መልእክት ቢያውጁም የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ስጋት የሚያድርባቸው በርካታ ሰዎች አሉ። ምክንያታቸው ምንድን ነው?

ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች የኑክሌር መሣሪያዎችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። እንዲያውም አንዳንድ ማን አለብኝ ባይ መሪዎች የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕጎችን ከቁብ አይቆጥሯቸውም። ቀድሞውኑም ቢሆን የኑክሌር መሣሪያ ያላቸው አገሮች አሮጌዎቹን ይበልጥ አጥፊ በሆኑ አዳዲስ ቦምቦች ለመተካት ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ላይ ናቸው። ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ያልነበሯቸው አገሮች ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በጣም ብዙ ሕዝብ የማጥፋት አቅም ያላቸው የጦር መሣሪያዎች ባለቤት ሆነዋል።

መንግሥታት የኑክሌር ጦርነት ለማካሄድ ከምንጊዜውም በላይ የታጠቁ መሆናቸው ዓለማችን “በሰላሙ” ጊዜም እንኳ በጣም አደገኛ ስፍራ እንዲሆን አድርጓል። ቡለቲን ኦቭ ዚ አቶሚክ ሳይንቲስትስ የተባለው መጽሔት “በተለይ ደግሞ የማንም ሰው ቁጥጥርና ትእዛዝ ሳያስፈልጋቸው የመጨረሻ ውሳኔ የሚያደርጉ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያዝዙ ገዳይ መሣሪያዎች ዓለማችንን ከፍተኛ ስጋት ላይ ይጥላሉ” በማለት አስጠንቅቋል።

በጤናችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት። ጥሩ ጤንነት እንዲኖረን በማስቻል ረገድ ሳይንስ ሊያደርግልን የሚችለው ነገር በጣም ውስን ነው። ከፍተኛ የደም ግፊትን፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትን፣ የአየር ብክለትንና ዕፅን ያላግባብ መጠቀምን የመሳሰሉ ለሕመም ሊዳርጉ የሚችሉ ችግሮች በእጅጉ እየተስፋፉ ነው። እንደ ካንሰር፣ ስኳር በሽታ እንዲሁም የልብና የደም ዝውውር ችግር ባሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚሞቱት ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ ነው። በተጨማሪም በአእምሮ ሕመምና በሌሎች በሽታዎች የሚሠቃዩ በርካታ ሰዎች አሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንደ ኢቦላና ዚካ ቫይረስ ያሉ ያልተጠበቁ ወረርሽኞች ከባድ ጉዳት ሲያስከትሉ ተመልክተናል። ይህን ሁሉ ስንመለከት በሽታ ከሰዎች ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ እንገነዘባለን፤ ሙሉ በሙሉ የሚወገድበት ጊዜ ይመጣል የሚል የተስፋ ጭላንጭልም አይታይም!

የሰው ልጆች በተፈጥሮ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት። ፋብሪካዎች የምድርን ከባቢ አየር መበከላቸውን ቀጥለዋል። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተበከለ አየር በመሳባቸው ምክንያት ለሞት ይዳረጋሉ።

ግለሰቦች፣ በርካታ ማኅበረሰቦች እንዲሁም መንግሥታዊ ድርጅቶች ፍሳሾችን፣ ከሕክምናና ከግብርና ምርቶች የሚወጡ ዝቃጮችን፣ ፕላስቲኮችንና ሌሎች በካይ ነገሮችን ውቅያኖስ ውስጥ መድፋታቸውን አላቆሙም። “እነዚህ መርዛማ ዝቃጮች የባሕር እንስሳትንም ሆነ ዕፀዋትን እንዲሁም የተበከሉትን የባሕር እንስሳት የሚመገቡትን ሰዎች ይመርዛሉ” በማለት ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ማሪን ሳይንስ ያብራራል።

በምድራችን ላይ ያለው ጨዋማ ያልሆነ ውኃ መጠንም በእጅጉ እየቀነሰ ነው። ብሪታንያዊው የሳይንስ ጸሐፊ ሮቢን ማኪ “ዓለማችን ሁሉንም የምድር ክፍሎች የሚነካ የውኃ ችግር ተጋርጦበታል” በማለት አስጠንቅቀዋል። ፖለቲከኞች የውኃ እጥረት በዋነኝነት ሰው ሠራሽ ችግር እንደሆነና በዚህም የተነሳ ምድራችን ከባድ አደጋ ላይ እንደወደቀች አምነው ይቀበላሉ።

ተፈጥሮ በሰው ልጆች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት። እንደ ማዕበል፣ ከባድ አውሎ ንፋስና የምድር ነውጥ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች አውዳሚ ለሆነ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ከፍተኛ ጉዳት ለሚያደርስ የመሬት መንሸራተትና ለሌሎች የተለያዩ ጥፋቶች መንስኤ ይሆናሉ። በእነዚህ የተፈጥሮ ኃይሎች የተነሳ የሚሞቱት ወይም ለከባድ ጉዳት የሚዳረጉት ሰዎች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል። ናሳ (ናሽናል ኤሮኖቲክስ ኤንድ ስፔስ አድሚኒስትሬሽን) ያወጣው ጥናት ወደፊት “እስካሁን ከተከሰቱት የበለጠ ኃይል ያላቸው ማዕበሎች፣ ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ የሙቀት ወጀቦች እንዲሁም ጎርፍና ድርቅ የሚፈራረቅባቸው ዑደቶች” የሚከሰቱበት አጋጣሚ እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቁሟል። ታዲያ ተፈጥሮ አንድ ቀን መላውን የሰው ዘር ጠራርጎ ያጠፋ ይሆን?

ሕልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሌሎች ሁኔታዎችም ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ሆኖም በዛሬው ጊዜ እየተከሰቱ ያሉትን መጥፎ ነገሮች አንድ በአንድ በመመርመር የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አጥጋቢ መልስ ማግኘት አትችልም። አንዳንዶች ፖለቲከኞችና ሳይንቲስቶች የሚናገሩትን መስማትም ቢሆን ምንም ፋይዳ እንደሌለው ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ብዙ ሰዎች ከዓለም ሁኔታና ከወደፊቱ ጊዜ ጋር በተያያዘ ለሚነሱባቸው ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ ማግኘት ችለዋል። ይህን መልስ ማግኘት የቻሉት ከየት ነው?