በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?

ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?

ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም?

ሳይንቲስቶች በ2017 መጀመሪያ ላይ አንድ አስደንጋጭ መግለጫ አውጥተው ነበር። በጥር ወር አንድ የሳይንቲስቶች ቡድን ዓለማችን ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጥፋት ወደሚከሰትበት ጊዜ ይበልጥ እንደቀረበ አስታወቀ። ሳይንቲስቶቹ ዓለም አቀፍ ጥፋት ወደሚከሰትበት ጊዜ ምን ያህል እንደቀረብን የሚያሳየውን ምሳሌያዊ የጥፋት ቀን ሰዓት 30 ሴኮንድ ወደፊት እንዲሄድ አድርገውታል። በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰዓት እኩለ ሌሊት ሊል የቀረው ሁለት ደቂቃ ተኩል ብቻ ነው፤ ዓለማችን ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ከነበረው ሁኔታ አንጻር ሲታይ ለዓለም አቀፍ ጥፋት ይህን ያህል የተቃረበበት ጊዜ የለም!

ሳይንቲስቶች ዓለማችን በተለምዶ የዓለም መጨረሻ ተብሎ ለሚጠራው ጊዜ ምን ያህል እንደተቃረበ ለማወቅ በ2018 ድጋሚ ግምገማ ለማካሄድ እቅድ ይዘዋል። የጥፋትን ቀን የሚያመለክተው ሰዓት አሁንም ከዚህ በፊት ተከስቶ የማያውቅ ታላቅ ጥፋት መከሰቱ እንደማይቀር ይጠቁም ይሆን? አንተ ምን ይመስልሃል? ዓለማችን ምንም ተስፋ የለውም? ምናልባት ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ መስጠት ይከብድህ ይሆናል። በመስኩ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎችም እንኳ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። በዓለማችን ላይ ጥፋት መከሰቱ አይቀርም ብለው የሚያምኑት ሁሉም አይደሉም።

እንዲያውም ወደፊት ብሩህ ጊዜ እንደሚመጣ የሚያምኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች የሰው ዘር ተጠራርጎ እንደማይጠፋና ፕላኔታችን ለዘላለም እንደምትኖር እንዲሁም የኑሮ ሁኔታችን እንደሚሻሻል የሚጠቁም ማስረጃ እንዳላቸው ይናገራሉ። የሚያቀርቡት ማስረጃ አሳማኝ ነው? በእርግጥ ዓለማችን ተስፋ አለው ወይስ የለውም?