በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኃይል ብክነትን ማስቀረት የሚቻለው እንዴት ነው?

የኃይል ብክነትን ማስቀረት የሚቻለው እንዴት ነው?

ቤታችንን ለማሞቅና ለማቀዝቀዝ፣ ተሽከርካሪዎቻችንን ለማንቀሳቀስ ብሎም ብዙዎቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ለማከናወን፣ እንደ ኤሌክትሪክና ነዳጅ የመሳሰሉት የኃይል ምንጮች ያስፈልጉናል። ይሁን እንጂ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች፣ ከኃይል ምንጮች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ተፈታታኝ ሁኔታ እያጋጠማቸው ነው።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ጋሪ፣ “የነዳጅ ዋጋ እየናረ መሄዱ” አሳሳቢ ችግር ሆኖበታል። በፊሊፒንስ ያለችው ጄኒፈር ደግሞ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ የማግኘት ጉዳይ ያሳስባታል፤ ምክንያቷን ስትገልጽ “የኤሌክትሪክ ኃይል በተደጋጋሚ ይቋረጣል” ብላለች። በኤል ሳልቫዶር የሚኖረው ፈርናንዶ የኃይል ምንጮች “በሥነ ምሕዳር ላይ የሚያሳድሩት ጫና” ያሳስበዋል። በዓለም ዙሪያ ባሉ ብዙ ቦታዎች፣ የኃይል ምንጮች አካባቢውን ይበክላሉ።

በመሆኑም ‘በኃይል ምንጮች ረገድ ካለው ችግር ጋር በተያያዘ በእኔ በኩል ማድረግ የምችለው ምን ነገር አለ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

የኃይል ምንጮችን በአግባቡ መጠቀም፣ እያንዳንዳችን ልናደርገው የምንችለው ነገር ነው። ኃይልን መቆጠብም ሆነ ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል። የኃይል ፍጆታችን ሲቀንስ በዚህ ረገድ የምናወጣው ወጪም ይቀንሳል። በተጨማሪም የኃይል ምንጮች በአካባቢው ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ እናበረክታለን፤ ምክንያቱም የኃይል ምንጮችን በአግባቡ መጠቀማችን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የኃይል ፍጆታ እንዳይጨምር ያደርጋል።

የኃይል ምንጮችን በአግባቡ ልንጠቀም የምንችልባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እስቲ እንመልከት፦ በቤታችን፣ ከመጓጓዣ ጋር በተያያዘና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ኃይል ለመቆጠብ ምን ማድረግ እንደምንችል ከዚህ ቀጥሎ እናያለን።

ቤት

የቤት ማሞቂያና ማቀዝቀዣ መሣሪያዎችን ስትጠቀሙ ኃይል አታባክኑ። በአንድ የአውሮፓ አገር የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በቅዝቃዜው ወቅት ነዋሪዎቹ በቤታቸው ውስጥ የሚኖረው ሙቀት መጠን ሌላ ጊዜ ከሚያደርጉት በሁለት ዲግሪ ብቻ እንዲቀንስ ማድረጋቸው፣ በዓመቱ ውስጥ የኃይል ፍጆታን ለመቆጠብ ከወሰዷቸው እርምጃዎች ሁሉ የላቀ ውጤት አስገኝቷል። በካናዳ የሚኖረው ዴሪክም ይህ እርምጃ ውጤታማ እንደሆነ ይሰማዋል። በቅዝቃዜው ወቅት “ቤተሰባችን ማሞቂያውን እስከ መጨረሻው ከፍ ከማድረግ ይልቅ ሹራብ በመልበስ ኃይል ይቆጥባል” ብሏል።

ሞቃት በሆኑ አካባቢዎች የቤት ማቀዝቀዣ በመጠቀም ረገድም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይቻላል። በፊሊፒንስ የሚኖረው ሮዶልፎ፣ የአየር ማቀዝቀዣ መሣሪያው የሚያቀዘቅዝበትን መጠን ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋል። ለምን? “በዚህ መንገድ ገንዘባችንን እንቆጥባለን፤ የኃይል ፍጆታችንንም እንቀንሳለን” ብሏል።

ቤታችሁን በምታሞቁበትም ሆነ በምታቀዘቅዙበት ጊዜ በሮቻችሁንና መስኮቶቻችሁን ዝጉ። * የሞቀም ሆነ የቀዘቀዘ አየር ወደ ውጭ እንዳይወጣ በማድረግ ኃይል እንዳይባክን መከላከል ይቻላል። ለምሳሌ ቅዝቃዜ ባለበት ጊዜ በር ከፍቶ መተው፣ ቤቱን ለማሞቅ የሚያስፈልገው ኃይል በእጅጉ እንዲጨምር ያደርጋል።

አንዳንዶች፣ መስኮቶችንና በሮችን ከመዝጋት በተጨማሪ ሙቀት እንዳይወጣ የሚያግዱ መስኮቶችን በመግጠም የኃይል ብክነትን መቀነስ ችለዋል።

ኃይል ቆጣቢ አምፖሎችን ተጠቀሙ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጄኒፈር፣ ኃይል የሚያባክነውን የተለመደውን ዓይነት አምፖል ትተው ኃይል ቆጣቢ የሆነ አምፖል  መጠቀም እንደጀመሩ ገልጻለች። የኃይል ቆጣቢ አምፖሎች ዋጋ ውድ በመሆኑ መጀመሪያ ላይ ብዙ ቢያስወጣንም፣ በአገልግሎት ዘመናቸው ወቅት የሚፈጁት ኃይል በጣም አነስተኛ በመሆኑ ውሎ አድሮ ወጪ ይቀንሳሉ።

መጓጓዣ

ከተቻለ በሕዝብ መጓጓዣዎች ተጠቀሙ። በብሪታንያ የሚኖረው አንድሩ፣ “ወደ ሥራ ስሄድ በተቻለኝ መጠን በባቡር ወይም በብስክሌት እጠቀማለሁ” ብሏል። ኢነርጂ፦ ዋት ኤቭሪዋን ኒድስ ቱ ኖው የተባለው መጽሐፍ ‘የቤት መኪኖች ከሚጭኑት ተሳፋሪ ብዛት አንጻር የሚወስዱት ኃይል፣ አውቶቡሶችና ባቡሮች ከሚወስዱት ኃይል ጋር ሲወዳደር የቤት መኪኖች የሚወስዱት ኃይል ቢያንስ በሦስት እጥፍ ይበልጣል’ ይላል።

ጉዟችሁን አቀናጁ። አስቀድማችሁ ዕቅድ ማውጣታችሁ፣ የምትጓዙበትን አቅጣጫ በማሰብ እግረ መንገዳችሁን የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን ይረዳችኋል። ይህም ብዙ መጓዝ እንዳያስፈልጋችሁ ስለሚያደርግ የኃይል ፍጆታችሁን ለመቀነስ ብሎም ጊዜያችሁንና ገንዘባችሁን ለመቆጠብ ያስችላችኋል።

በፊሊፒንስ የሚኖረው ጄትሮ ለመኪናው በወር ምን ያህል ነዳጅ እንደሚጠቀም አስቀድሞ ይወስናል። “ይህም፣ የማደርጋቸውን ጉዞዎች በጥንቃቄ እንዳቅድ ያነሳሳኛል” ብሏል።

የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች

የምትጠቀሙትን የሙቅ ውኃ መጠን ቀንሱ። አንድ ጥናት እንዳሳየው “ከአውስትራሊያ ከተሞች አጠቃላይ የኃይል ፍጆታ በአማካይ 1.3 በመቶ የሚሆነው የሚውለው፣ በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ውኃ ለማሞቅ ነው”፤ በሌላ አባባል ከእያንዳንዱ ቤተሰብ አጠቃላይ የቤት ውስጥ የኃይል ፍጆታ 27 በመቶ የሚሆነውን የሚወስደው የውኃ ማሞቂያ ነው።

ውኃ ማሞቅ ኃይል ስለሚፈጅ፣ የምንጠቀምበትን የሙቅ ውኃ መጠን መቀነስ ኃይል ይቆጥባል። ከዚህ አንጻር፣ በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ቪክቶር “ሰውነታችንን በምንታጠብበት ጊዜ በተቻለ መጠን ብዙ ሙቅ ውኃ ላለመጠቀም እንሞክራለን” ያለበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም። ስቲቨን ኬንዌ የተባሉት የሳይንስ ሊቅ እንደተናገሩት “ሙቅ ውኃ መቆጠብ በሦስት አቅጣጫ ጥቅሞች አሉት።” ለተገልጋዮች የኃይልና የውኃ ፍጆታቸውን ይቀንስላቸዋል፤ የኃይልና የውኃ አቅራቢ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸው አቅርቦት ይቀንሳል፤ እንዲሁም ቤተሰቦች ወጪያቸው እንዲቀንስ ያደርጋል።

አጥፉ። ይህ መብራቶችን፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎችን እንዲሁም እንደ ቴሌቪዥንና ኮምፒውተር ያሉትን የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ያካትታል። እንደነዚህ ካሉት መሣሪያዎች አብዛኞቹ አገልግሎት በማይሰጡበት ጊዜም ጭምር ኃይል ይወስዳሉ። አንዳንድ ባለሙያዎች፣ ይበልጥ ኃይል ለመቆጠብ እንድንችል መሣሪያውን ከኤሌክትሪክ መስመሩ መንቀል አሊያም ማብሪያ ማጥፊያ ያለው ማከፋፈያ መጠቀም ጥሩ እንደሚሆን ይመክራሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፈርናንዶ እንዲህ የማድረግ ልማድ አለው። “መብራቶችን አጠፋለሁ፣ እንዲሁም የማልጠቀምባቸውን መሣሪያዎች ከሶኬቱ እነቅላለሁ” ብሏል።

በኃይል ምንጮች ዋጋ መናር ወይም ኃይል ማመንጨት በአካባቢው ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ረገድ ለውጥ ማምጣት ባንችልም በኃይል አጠቃቀማችን ላይ ግን ለውጥ ማድረግ እንችላለን። በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ይህን እያደረጉ ነው። ኃይል መቆጠብ፣ ተጨማሪ ጥረትና ዕቅድ የሚጠይቅ ቢሆንም የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አስቡ። በሜክሲኮ የምትኖረው ቫሌሪያ “ገንዘብ እቆጥባለሁ፤ አካባቢዬንም ከብክለት እጠብቃለሁ” ብላለች።

^ አን.10 የማሞቂያ ወይም የማቀዝቀዣ መሣሪያዎችን በትክክል ለመጠቀም የአምራቹን መመሪያ በጥንቃቄ ተከተሉ። ለምሳሌ፣ አንዳንድ መሣሪያዎችን ስትጠቀሙ ንጹሕ አየር ማስገባት ወይም የቆሸሸውን አየር ማስወጣት ስለሚያስፈልጋችሁ በር ወይም መስኮት መክፈት ሊኖርባችሁ ይችላል።