በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

አደጋ ሲደርስ ሕይወት ለማዳን የሚያስችሉ እርምጃዎች

አደጋ ሲደርስ ሕይወት ለማዳን የሚያስችሉ እርምጃዎች

“ጆሮ የሚያደነቁረውን ፍንዳታ ስሰማ ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ። በቢሯችን የአየር ማስተላለፊያ ቀዳዳዎች በኩል ጭስ እየተትጎለጎለ ገባ፤ ከዚያም ረጅም ፎቅ ላይ የነበረው ቢሯችን በእሳት ተያያዘ።”—ጆሹዋ

የምድር መንቀጥቀጥ ደረሰ፤ . . . ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከባድ ጉዳት አደረሰ፤ . . . አሸባሪዎች ጥቃት ሰነዘሩ፤ . . . በትምህርት ቤት ውስጥ ተኩስ ተከፈተ። እንዲህ ዓይነት ርዕሰ ዜናዎች የተለመዱ ሆነዋል። እርግጥ ነው፣ ስለ አደጋ ማንበብ እና በአደጋ ውስጥ ማለፍ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ከአደጋ የመትረፍ የተሻለ አጋጣሚ እንዲኖራችሁ ከአደጋ በፊት፣ በአደጋው ጊዜ እና ከአደጋው በኋላ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?

ከአደጋ በፊት ተዘጋጁ!

‘አደጋ ሊደርስብኝ አይችልም’ ብሎ መናገር የሚችል ሰው የለም። ከአደጋ ለመትረፍ ቁልፉ ዝግጅት ነው። ይሁን እንጂ ዝግጅት የትኞቹን ነገሮች ያካትታል?

 • አእምሯችሁን አዘጋጁ። በማንኛውም ጊዜ አደጋ ሊያጋጥምና ቤተሰባችሁ በአደጋው ሊጠቃ እንደሚችል አምናችሁ ተቀበሉ። አደጋ ከደረሰ በኋላ ዝግጅት ለማድረግ መሞከር፣ ‘ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ’ እንደሚባለው ይሆናል።

 • በአካባቢያችሁ ሊደርሱ ስለሚችሉ አደጋዎች ለማወቅ ጥረት አድርጉ። የአደጋ ጊዜ መጠለያዎች የት እንደሚገኙ እወቁ። የቤታችሁ አሠራርና የሚገኝበት ቦታ በተቻለ መጠን ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑን አረጋግጡ። ቃጠሎ ሊያስነሱ የሚችሉ ነገሮችን አስወግዱ። ጭስ በሚኖርበት ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ መሣሪያዎችን ቤታችሁ ውስጥ ግጠሙ፤ እንዲሁም ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የመሣሪያውን ባትሪ ቀይሩት።

 • ለአደጋ ጊዜ የሚሆኑ ነገሮችን አዘጋጁ። አደጋ ሲፈጠር የኃይል፣ የውኃ፣ የስልክና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ሊቋረጡ ይችላሉ። ስለዚህ መኪና ካላችሁ ነዳጁ ሁልጊዜ ከግማሽ ታንክ እንዳይወርድ አድርጉ፤ እንዲሁም ምንጊዜም ቤታችሁ ውስጥ ምግብ፣ ውኃና ለአደጋ ጊዜ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች የያዘ ቦርሳ አስቀምጡ።—“የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች አዘጋጅታችኋል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከቱ።

  ከአደጋ ለመትረፍ ቁልፉ ዝግጅት ነው

 • የወዳጆቻችሁ ስልክ ቁጥር (በቅርብም ሆነ በሩቅ የሚኖሩ) ይኑራችሁ

 • ከአደጋ የማምለጫ ዘዴዎችን ተለማመዱ። ባላችሁበት ሕንፃ ውስጥ ቅርብ ያለው መውጫ የት እንደሆነ እወቁ፤ በተጨማሪም ልጆቻችሁ ትምህርት ቤት እያሉ አደጋ ቢከሰት ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሠልጥኗቸው። ቤተሰባችሁ አደጋ ሲፈጠር የት እንደሚገናኝ አስቀድማችሁ ወስኑ፤ አንደኛው በአቅራቢያችሁ ሌላው ደግሞ ከአካባቢያችሁ ወጣ ያለ ቦታ ቢሆን ጥሩ ነው፤ እንደ ትምህርት ቤት ወይም ቤተ መጻሕፍት ባሉት ቦታዎች መገናኘት ትችሉ ይሆናል። ባለሙያዎች፣ ከቤተሰባችሁ ጋር ወደ እነዚህ ቦታዎች በእግራችሁ መሄድን እንድትለማመዱ ይመክራሉ።

 • ሌሎችን እንዴት መርዳት እንደምትችሉ አስቡ፤ ለምሳሌ አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን።

በአደጋው ጊዜ አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆሹዋ “ቃጠሎ በተነሳበት ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ቶሎ እርምጃ አልወሰዱም” ብሏል። “ኮምፒውተራቸውን የሚያጠፉ ወይም የውኃ ኮዳቸውን የሚሞሉ ሰዎች ነበሩ። እንዲያውም አንደኛው ሰውዬ ‘ዝም ብለን ብንጠብቅ ሳይሻል አይቀርም’ አለ።” ሌሎቹ ቢያመነቱም ጆሹዋ “አሁኑኑ መውጣት አለብን!” ብሎ ጮኸ። የሥራ ባልደረቦቹ ይህን ሲሰሙ ወዲያውኑ እሱን ተከትለው ደረጃውን መውረድ ጀመሩ። ጆሹዋም ድምፁን ከፍ አድርጎ “የወደቀ ሰው ካለ ተሸክመነው እንሂድ። ሁላችንም መትረፍ እንችላለን!” አላቸው።

 • እሳት ሲነሳ። ጎንበስ ብላችሁ ቅርባችሁ ወዳለው መውጫ ሽሹ። ጭስ እይታን ይጋርዳል፤ በተጨማሪም እሳት ሲነሳ ብዙ ሰዎች የሚሞቱት ጭሱ ስለሚያፍናቸው ነው። ንብረቶቻችሁን ለመያዝ አትሞክሩ። ለጥቂት ሴኮንዶች በመዘግየታችሁ ብቻ ሕይወታችሁን ልታጡ ትችላላችሁ።

 • የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት። እንደ ጠረጴዛ ባሉ ጠንካራ የሆኑ ዕቃዎች ሥር ተጠለሉ ወይም በሁለት ክፍሎች መካከል ወዳለው ግድግዳ ተጠግታችሁ ቁሙ። ከዋናው መንቀጥቀጥ በኋላ ቀጣይ መናወጥ ሊኖር ስለሚችል በተቻለ ፍጥነት ወደ ውጭ ውጡ እንዲሁም ከሕንፃዎች ራቁ። የሠለጠኑ ሕይወት አድን ሠራተኞች ወደዚያ ለመድረስ ሰዓታት ሊፈጅባቸው ስለሚችል አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ሌሎችን ለማዳን ሞክሩ።

 • ሱናሚ ሲመጣ። ባሕሩ በድንገት ወደ ኋላ ካፈገፈገ፣ ከፍ ወዳለ ቦታ በፍጥነት ሽሹ። ይበልጥ ኃይለኛ የሆነ ማዕበል ሊመጣ ስለሚችል ከአካባቢው ርቃችሁ ቆዩ።

 • ውሽንፍር የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ሲከሰት። ወደ አውሎ ነፋስ መጠለያ ቦታ በፍጥነት ሽሹ። አሊያም ቤታችሁ ምድር ቤት ካለው ወደዚያ ውረዱ።

 • ጎርፍ ሲመጣ። በጎርፍ ወደተጥለቀለቁ ሕንፃዎች አትግቡ። በጎርፍ ውስጥ በእግር ወይም በመኪና ለመሄድ አትሞክሩ። ምክንያቱም የጎርፍ ውኃ ከፍሳሽ ጋር ሊቀላቀል ይችላል፤ አሊያም በጎርፉ የተሸፈኑ ስብርባሪ ነገሮች፣ ጉድጓዶች፣ የወደቁ የኤሌክትሪክ ገመዶችና የመሳሰሉት አደገኛ ነገሮች ለጉዳት ሊዳርጓችሁ ይችላሉ።

 • ይህን ያውቁ ኖሯል? 60 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ያለው ጎርፍ መኪናን መውሰድ ይችላል። የጎርፍ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች የሚሞቱት በጎርፉ ውስጥ ለመንዳት ሲሞክሩ ነው።

 • አካባቢውን ለቅቃችሁ እንድትወጡ ትእዛዝ ከተላለፈ ወዲያውኑ ውጡ! የት እንዳላችሁ ለወዳጆቻችሁ ንገሯቸው፤ አለዚያ እናንተን ለመፈለግ ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ።

  ከአካባቢው እንድትወጡ ትእዛዝ ከተላለፈ ወዲያውኑ ውጡ!

 • ይህን ያውቁ ኖሯል? ስልክ ከመደወል ይልቅ የጽሑፍ መልእክት መላክ የበለጠ አስተማማኝ ሊሆን ይችላል።

 • ነዋሪዎች ከቤታቸው ወይም ከመጠለያ ቦታ እንዳይወጡ ትእዛዝ ከተላለፈ ወደ ውጭ አትውጡ። አየሩ በሽታ በሚያስከትሉ ነገሮች፣ በአደገኛ ኬሚካሎች ወይም በኑክሌር ጨረራ እንደተበከለ ከታወቀ ከቤት አትውጡ፤ እንዲሁም በሮችንና መስኮቶችን ጨምሮ አየር የሚያስገቡ ክፍተቶችን ሁሉ ድፈኑ። የኑክሌር አደጋ ከተከሰተ ለጨረራ የመጋለጥ አጋጣሚያችሁን ለመቀነስ ወደ ምድር ቤት ውረዱ፤ አሊያም የቤታችሁ ወለል ላይ ተኙ። የአካባቢያችሁን የቴሌቪዥን ወይም የሬዲዮ ዜና ተከታተሉ። ወደ ውጭ መውጣት አደገኛ እንዳልሆነ የሚገልጽ ማስታወቂያ እስኪነገር ድረስ ከቤት አትውጡ።

ከአደጋው በኋላ ራሳችሁን ከአደገኛ ሁኔታ ጠብቁ!

ለበሽታና ለአደገኛ ሁኔታ ከሚያጋልጥ ነገር ራሳችሁን ለመጠበቅ የሚከተሉትን ነገሮች አድርጉ፦

 • የሚቻል ከሆነ፣ ወዳጆቻችሁ ቤት መቆየት መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከመግባት የተሻለ ነው።

 • የምትኖሩበትን ቦታ ንጽሕና ጠብቁ።

 • በሰውነታችሁ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከያ ሳትጠቀሙ ፍርስራሹን ለማጽዳት አትሞክሩ። የሚቻል ከሆነ ጓንት፣ ጠንካራ ጫማ፣ የአደጋ መከላከያ ቆብ ብሎም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አድርጉ። የተደበቁ የኤሌክትሪክ ሽቦዎችና የጋሉ ነገሮች ጉዳት እንዳያደርሱባችሁ ተጠንቀቁ።

 • በተቻላችሁ መጠን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችሁን አታስተጓጉሉ። ለልጆቻችሁ ስትሉ ለመረጋጋትና ተስፋ ላለመቁረጥ ጥረት አድርጉ። ልጆቻችሁ ትምህርት ቤት ባይሄዱም እናንተ አስተምሯቸው፤ አብራችሁ ተጫወቱ እንዲሁም በቤተሰብ ሆናችሁ አምልኳችሁን አከናውኑ። አደጋው ስላደረሰው ጉዳት በሚገልጹ ዜናዎች ላይ ከሚገባው በላይ ትኩረት አታድርጉ፤ ጭንቀታችሁንና ብስጭታችሁን በቤተሰቦቻችሁ ላይ አትወጡ። የሌሎችን እርዳታ ተቀበሉ፤ እናንተም ሌሎችን እርዱ።

  ከአደጋው በኋላ ዕለታዊ እንቅስቃሴያችሁን በተቻለ መጠን አታስተጓጉሉ

 • አደጋ ብዙ ነገሮችን እንደሚያሳጣ አምናችሁ ተቀበሉ። መንግሥትም ሆነ የእርዳታ ድርጅቶች የሚያተኩሩት የጠፋውን ንብረት በሙሉ በመተካት ላይ ሳይሆን የሰዎችን ሕይወት በማዳን ላይ ነው። በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልገው ንጹሕ ውኃ፣ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8

 • በአደጋው የተነሳ ስሜታችሁ ሊረበሽ እንደሚችል በመገንዘብ እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። እንዲህ ዓይነቱ የስሜት መረበሽ በአብዛኛው የሚያጋጥመው አደጋው ካለፈ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። ፍርሃት፣ ሐዘን፣ የባሕርይ መለዋወጥ፣ ማሰብና መሥራት አለመቻል ብሎም እንቅልፍ ማጣት ሊያጋጥማችሁ ይችላል። በዚህ ጊዜ፣ አሳቢ ለሆኑ ወዳጆቻችሁ ስሜታችሁን አካፍሉ።

ጆሹዋ በሥራ ቦታው ከደረሰው የእሳት አደጋ ቢተርፍም የሚያውቃቸው ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ክርስቲያን ሽማግሌዎችና የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች እርዳታ አደረጉለት። ጆሹዋ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለው የሐዘን ስሜት ተፈጥሯዊ ነገር እንደሆነና በጊዜ ሂደት እየቀነሰ እንደሚሄድ ገለጹልኝ። ሌሊት ላይ የሚያስቸግረኝ ቅዠት፣ ከስድስት ወር በኋላ እየቀነሰ መጣ። አንዳንዶቹ መጥፎ ስሜቶች ግን ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተዋል።”

አደጋዎች ሲደርሱ፣ ፍትሕ እንደተዛባ ሊሰማን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ‘ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂው አምላክ ነው’ የሚል የተሳሳተ ስሜት ያድርባቸዋል። እንደ ጆሹዋ ያሉ ብዙ ሰዎች ደግሞ ሌሎች ሞተው እነሱ በመትረፋቸው የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ጆሹዋ እንዲህ ብሏል፦ “‘ተጨማሪ ሰዎችን ማዳን አልችልም ነበር?’ ብዬ አሁንም ድረስ አስባለሁ። ሆኖም አምላክ በቅርቡ በመላው ምድር ላይ ፍትሕ እንደሚያሰፍንና ሁሉንም ነገሮች እንደሚያስተካክል ያለኝ እምነት ያጽናናኛል። እስከዚያው ድረስ ግን በሕይወት የማሳልፈውን እያንዳንዱን ቀን በጣም ውድ አድርጌ እመለከተዋለሁ፤ እንዲሁም ሕይወቴን ላለማጣት የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።”—ራእይ 21:4, 5 *