በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂው ንጥረ ነገር

አስደናቂው ንጥረ ነገር

“የካርቦንን ያህል ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር የለም” በማለት ኔቸርስ ቢልዲንግ ብሎክስ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። ካርቦን ብቻ ያሉት አንዳንድ ባሕርያት፣ ከሌሎች የካርቦን አቶሞች እንዲሁም ከተለያዩ ንጥረ ነገሮች ጋር በመጣመር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ውህዶችን ለመፍጠር ያስችላሉ፤ በመሆኑም በየጊዜው አዳዲስ የካርቦን ውህዶች እየተገኙ እንዲሁም በቤተ ሙከራ እየተሠሩ ነው።

ቀጥሎ የቀረቡት ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት የካርቦን አቶሞች እርስ በርስ ተጣምረው የተለያዩ ዓይነት ቅርጾችን ሊፈጥሩም ይችላሉ፤ ለምሳሌ የሰንሰለት፣ የፒራሚድ፣ የቀለበት፣ የቱቦ እንዲሁም ዝርግ የሆነ ቅርጽ ሊፈጥሩ ይችላሉ። በእርግጥም ካርቦን አስደናቂ ንጥረ ነገር ነው!

አልማዝ

የካርቦን አቶሞች ቴትራሄድሮን በመባል የሚጠሩ ፒራሚዶችን በመሥራት በጣም ጠንካራ የሆነ ቅርጽ ይፈጥራሉ፤ አልማዝ በተፈጥሮ ከሚገኙ ነገሮች መካከል በጥንካሬው ተወዳዳሪ የሌለው የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። ምርጥ የሚባለው አልማዝ ከካርቦን አቶሞች የተሠራ አንድ ሞለኪውል ነው።

ግራፋይት

እርስ በርስ ከፍተኛ ትስስር ያላቸው የካርቦን አቶሞች እንደ ዝርግ ወረቀት ያለ ቅርጽ በመሥራት ተነባብረው ይቀመጣሉ፤ በእነዚህ የተነባበሩ ንጣፎች መካከል ጠንካራ ትስስር ስለሌለ ተደራርበው እንደተቀመጡ ወረቀቶች አንዱ ንጣፍ ከሌላው ላይ ሊንሸራተት ይችላል። በዚህ የተነሳ ግራፋይት እንደ ማለስለሻ የሚያገለግል ከመሆኑም ሌላ እርሳስ ለመሥራት ከሚያስፈልጉት ንጥረ ነገሮች ዋነኛው ነው። *

ግራፊን

ግራፊን፣ የስድስት ማዕዘን ቅርጽ በመሥራት እርስ በርስ የተያያዙ በርካታ የካርቦን አቶሞች ንጣፍ ነው። ግራፊን ጫና የመቋቋም አቅሙ ከብረት በብዙ እጥፍ ይበልጣል። በእርሳስ የተሠራ አንድ መስመር አነስተኛ መጠን ያለው ግራፊን ሊኖረው የሚችል ሲሆን ይህም በአንድ ወይም በበርካታ ንጣፎች የተቀመጠ ሊሆን ይችላል።

ፉለሪኖች

ውስጣቸው ባዶ የሆነው እነዚህ የካርቦን ሞለኪውሎች የተለያየ ቅርጽ ሊኖራቸው ይችላል፤ በማይክሮስኮፕ ብቻ ከሚታዩት ከእነዚህ ሞለኪውሎች አንዳንዶቹ የኳስ አሊያም ደግሞ የቱቦ ዓይነት ቅርጽ (ናኖቲዩብ ይባላሉ) አላቸው። የፉለሪኖች መጠን የሚለካው በናኖሜትር (የአንድ ሜትር አንድ ቢሊዮንኛ) ነው።

ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት

ዕፀዋት፣ እንስሳት እንዲሁም ሰዎች የተዋቀሩባቸው ሴሎች ከካርቦን የተሠሩ ናቸው፤ ምክንያቱም ካርቦን በካርቦሃይድሬት፣ በስብና በአሚኖ አሲድ ውስጥ ይገኛል።

‘የማይታዩትን የአምላክ ባሕርያት ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።’—ሮም 1:20

^ አን.7 በሐምሌ 2007 ንቁ! ላይ የወጣውን “እርሳስ ያለው አለ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።