ንድፍ አውጪ አለው?
የፒሪዮዲካል ሲካዳ የሕይወት ዑደት
ሲካዳ የሚባሉት አንበጣ መሰል ነፍሳት ከአንታርክቲካ በቀር በሁሉም አህጉራት ውስጥ ይኖራሉ። ፒሪዮዲካል ሲካዳ የሚባለው ዝርያ የሚገኘው ግን በሰሜናዊ ምሥራቅ አሜሪካ ብቻ ሲሆን እነዚህ ነፍሳት የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎችን ለረጅም ጊዜ ሲያስደንቁ ኖረዋል።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፒሪዮዲካል ሲካዳዎች በፀደይ ወራት በድንገት ብቅ የሚሉ ሲሆን የሚቆዩትም ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ነው። ፀሐይ ላይ በሚቆዩበት አጭር ጊዜ ውስጥ የወጣትነት ቆዳቸውን ይቀይራሉ፣ ጆሮ በሚያደነቁር ድምፅ ይዘምራሉ፣ ይበራሉ፣ ይራባሉ ከዚያም ይሞታሉ። የሚገርመው ነገር፣ ቀጣዩ ትውልድ ብቅ የሚለው ከ13 ወይም ከ17 ዓመት በኋላ ሲሆን ይህ እንደ ዝርያቸው ይለያያል። ታዲያ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ነፍሳቱ ምን ያደርጋሉ?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ የእነዚህን ነፍሳት ለየት ያለ የሕይወት ዑደት መረዳት ያስፈልገናል። ፒሪዮዲካል ሲካዳዎች ብቅ ካሉ ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ተቃራኒ ፆታዎች ይገናኙና እንስቶቹ ከ400 እስከ 600 የሚደርሱ እንቁላሎችን በቅርንጫፎች ቅርፊት ውስጥ ይጥላሉ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ነፍሳት ይሞታሉ። በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንቁላሎቹ ይፈለፈላሉ፤ ከዚያም እጮቹ ከዛፎቹ ወደ መሬት ይወድቁና አፈሩን ሰርስረው በመግባት ከመሬት ሥር መኖር ይጀምራሉ፤ እዚያም የቁጥቋጦዎችን ወይም የዛፎችን ሥሮች በመምጠጥ የሚያገኙትን ፈሳሽ እየተመገቡ ለዓመታት ይኖራሉ። ከ13 ወይም ከ17 ዓመታት በኋላ አዲሱ ትውልድ ብቅ ይልና ወላጆቹ የተከተሉትን ዑደት ይደግማል።
ኔቸር የተሰኘው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደሚገልጸው የእነዚህ ሲካዳዎች ውስብስብ የሕይወት ዑደት “የሳይንስ ሊቃውንትን ለብዙ መቶ ዘመናት ግራ ሲያጋባ ኖሯል። . . . ስለ ነፍሳት የሚያጠኑ ሊቃውንት፣ የእነዚህ ነፍሳት ልዩ የሕይወት ዑደት በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት እንዴት እንደመጣ ለመረዳት አሁንም እየጣሩ ነው።” የፒሪዮዲካል ሲካዳዎች የሕይወት ዑደት በእንስሳት ዓለም ታይቶ የማያውቅ እንቆቅልሽ ነው።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የፒሪዮዲካል ሲካዳ የሕይወት ዑደት የዝግመተ ለውጥ ውጤት ሊሆን ይችላል? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?