በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ልማዶችህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?

3 ተስፋ አትቁረጥ

3 ተስፋ አትቁረጥ

‘አዲስ ልማድ ለማዳበር 21 ቀናት ይፈጃል’ የሚል የተለመደ አባባል አለ። እውነታው ሲታይ ግን አንዳንድ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ጉልህ ለውጥ ለማድረግ ከዚህ ያነሰ ጊዜ የሚፈጅባቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ የበለጠ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ይህ ተስፋ ሊያስቆርጥህ ይገባል?

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ አስብ፦ በሳምንት ሦስት ቀን ስፖርት የመሥራት ልማድ ማዳበር ትፈልጋለህ እንበል።

  • በመጀመሪያው ሳምንት ግብህን ማሳካት ቻልክ።

  • በሁለተኛው ሳምንት ስፖርት የሠራኸው ሁለት ቀን ብቻ ነው።

  • በሦስተኛው ሳምንት እንደገና ግብህ ላይ መድረስ ቻልክ።

  • በአራተኛው ሳምንት ስፖርት የሠራኸው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

  • በአምስተኛው ሳምንት ግብህን እንደገና አሳካህ፤ ከዚያ በኋላም በየሳምንቱ ስፖርት መሥራትህን ቀጠልክ።

አዲሱን ልማድህን ለማዳበር አምስት ሳምንት ወሰደብህ። ይህ ረጅም ጊዜ ቢመስልም ግብህ ላይ መድረስ ከቻልክ በኋላ ግን አዲስ ልማድ በማዳበርህ ደስ ይልሃል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳል።”ምሳሌ 24:16

መጽሐፍ ቅዱስ ቶሎ ተስፋ እንዳንቆርጥ ያበረታታል። ዋናው ነገር፣ ምን ያህል ጊዜ ወደቅን የሚለው ጉዳይ ሳይሆን ምን ያህል ጊዜ መልሰን ተነሳን የሚለው ነው።

ዋናው ነገር፣ ምን ያህል ጊዜ ወደቅን የሚለው ጉዳይ ሳይሆን ምን ያህል ጊዜ ተነሳን የሚለው ነው

ምን ማድረግ ትችላለህ?

  • መጥፎ ልማድህ ስላገረሸብህ ይህን ልማድ ጨርሶ ማስወገድ አትችልም ማለት አይደለም። ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ አንዳንድ እንቅፋቶች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ መጠበቅ ይኖርብሃል።

  • ግብህ ላይ መድረስ የቻልክባቸውን ጊዜያት መለስ ብለህ አስብ። ለምሳሌ ያህል፣ ከልጆችህ ጋር የምትነጋገርበትን መንገድ ለማሻሻል እየጣርክ ከሆነ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በልጆቼ ተናድጄ እነሱ ላይ ለመጮኽ ቢቃጣኝም ይህን ከማድረግ የተቆጠብኩት መቼ ነበር? በእነሱ ላይ ከመጮኽ ይልቅ ምን አድርጌያለሁ? አሁንም እንዲህ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ እንደነዚህ ያሉት ጥያቄዎች፣ ግብህን እንዳታሳካ ያደረጉህን እንቅፋቶች እያሰብክ ከመብሰልሰል ይልቅ ባደረግከው መልካም ነገር ላይ ለማተኮር ይረዱሃል።

በሌሎች የሕይወት ዘርፎች ለምሳሌ ጭንቀትን መቋቋምደስተኛ ቤተሰብ መገንባትና እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንዴት ሊረዱህ እንደሚችሉ ማወቅ ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮችን ማናገር ወይም jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን መመልከት ትችላለህ።