አገሮችና ሕዝቦች
ኪርጊስታንን እንጎብኝ
በበረዶ የተሸፈኑ ሰማይ ጠቀስ ተራሮች የከበቧት ኪርጊስታን የምትገኘው በመካከለኛው እስያ ሲሆን ካዛክስታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ ታጂኪስታንና ቻይና ያዋስኗታል። ወደ 90 በመቶ የሚጠጋው የአገሪቱ ክፍል ተራራማ ነው። ትዬን ሻን የተባለው የተራራ ሰንሰለት ከፍተኛው ቦታ (ከባሕር ጠለል በላይ 7,439 ሜትር) የሚገኘው በኪርጊስታን ነው። አራት በመቶ ገደማ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል በደን የተሸፈነ ነው። በመሆኑም በፕላኔታችን ላይ ካሉ የዎልነት ዛፎች የተፈጥሮ ደኖች መካከል ሰፊ የሆነው የሚገኘው በኪርጊስታን መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።
የኪርጊዝ ሕዝብ በእንግዳ ተቀባይነታቸውና በሰው አክባሪነታቸው በጣም የታወቁ ናቸው። በኪርጊስታን ባህል ሕዝቡ፣ በዕድሜ የሚበልጣቸውን ሰው ሲያነጋግሩ እንደ “አንቱታ” ያለ የአክብሮት መግለጫ መጠቀማቸው እንዲሁም ለትልቅ ሰው በሕዝብ መጓጓዣ ላይ ወንበራቸውን መልቀቃቸውና በማዕድ ላይ የተከበረውን ቦታ መስጠታቸው የተለመደ ነው።
አብዛኞቹ ቤተሰቦች፣ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ ልጆች ይወልዳሉ። አብዛኛውን ጊዜ የመጨረሻው ወንድ ልጅ ከወላጆቹ ጋር የሚኖር ሲሆን ትዳር ከመሠረተ በኋላም እንኳ አብሯቸው በመኖር ይጦራቸዋል።
ሴቶች ልጆች ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ ጥሩ ሚስት ለመሆን የሚያስፈልጉ ሙያዎችን ይማራሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሲደርሱ ራሳቸውን ችለው ቤት ማስተዳደር ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ለሙሽሪት ቤተሰቦቿ ጥሎሽ ያዘጋጁላታል። ይህም አንሶላዎችን፣ ብርድ ልብሶችንና አልጋ ልብሶችን፣ ልዩ ልዩ አልባሳትንና በእጅ የተሠራ ምንጣፍን ይጨምራል። ሙሽራው ደግሞ ጥሬ ገንዘብና ከብቶችን ጥሎሽ አድርጎ ይሰጣል።
በደስታም ሆነ በሐዘን ጊዜ በግ ወይም ፈረስ ይታረዳል። ሥጋውም በብልት በብልቱ ተቆራርጦ እያንዳንዱ ክፍል ለተመደበለት ሰው ይሰጣል። እንግዶቹ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ በዕድሜያቸውና በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ መሠረት የየራሳቸው ድርሻ ይሰጣቸዋል፤ ከዚህ ባሕል ጋር በተያያዘም፣ ለትልቅ ሰው የሚሰጠው አክብሮት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ከዚያም ብዬሽባርማክ የሚባለው ባሕላዊ ምግብ ይቀርባል። ምግቡ የሚበላው በእጅ ነው።