በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መላእክት

መላእክት

መላእክት በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችና ፊልሞች ላይ ይጠቀሳሉ፤ የመላእክትን ምስል የያዙ የሥነ ጥበብ ሥራዎችም አሉ። ለመሆኑ መላእክት እነማን ናቸው? ሥራቸውስ ምንድን ነው?

መላእክት እነማን ናቸው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

አምላክ ግዑዙን ጽንፈ ዓለምና የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ከመፍጠሩ በፊት የማሰብ ችሎታ ያላቸው እንዲሁም ከሰው ልጆች በላቀ ደረጃ ላይ የሚገኙ ፍጥረታትን ፈጥሯል። እነዚህ ፍጥረታት ከሰው ልጆች የበለጠ ኃይል ያላቸው ሲሆን የሚኖሩትም አምላክ ራሱ በሚኖርበት መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ነው፤ የሰው ልጆች ይህን መንፈሳዊ ዓለም ሊደርሱበትም ሆነ ሊያዩት አይችሉም። (ኢዮብ 38:4, 7) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ኃያል ፍጥረታት “መናፍስት” እና ‘መላእክት’ በማለት ይጠራቸዋል።—መዝሙር 104:4 *

ለመሆኑ ስንት መላእክት አሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው ነገር በመነሳት በጣም ብዙ መላእክት እንዳሉ መረዳት እንችላለን። በአምላክ ዙፋን ዙሪያ ያሉት መላእክት “እልፍ ጊዜ እልፍ” ወይም “አሥር ሺዎች ጊዜ አሥር ሺዎች” ናቸው። (ራእይ 5:11፤ ግርጌ) ይህን አገላለጽ ቃል በቃል ከወሰድነው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት አሉ ማለት ነው!

“እኔም አየሁ፤ ደግሞም በዙፋኑ . . . ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቁጥራቸውም እልፍ ጊዜ እልፍና ሺዎች ጊዜ ሺዎች ነበር።”—ራእይ 5:11

መላእክት በጥንት ዘመን ምን ነገሮችን አከናውነዋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

መላእክት ብዙ ጊዜ የአምላክ ቃል አቀባዮች ወይም መልእክተኞች ሆነው አገልግለዋል። * እንዲሁም በአምላክ ትእዛዝ ተአምራትን እንደፈጸሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል። አምላክ አብርሃምን የባረከውና ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት እንዳያደርግ የከለከለው መልአኩን በመላክ ነው። (ዘፍጥረት 22:11-18) አንድ መልአክ በሚነድ ቁጥቋጦ ውስጥ ለሙሴ የተገለጠለት ሲሆን ከአምላክ የተቀበለውን ወሳኝ መልእክት ነግሮታል። (ዘፀአት 3:1, 2) ነቢዩ ዳንኤል ወደ አንበሶች ጉድጓድ በተጣለበት ጊዜ ‘አምላክ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘግቷል።’—ዳንኤል 6:22

“ከዚያም የይሖዋ መልአክ በቁጥቋጦ መሃል በሚነድ የእሳት ነበልባል ውስጥ [ለሙሴ] ተገለጠለት።”—ዘፀአት 3:2

መላእክት በአሁኑ ጊዜ ምን እያከናወኑ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

መላእክት በአሁኑ ወቅት ምን እያከናወኑ እንዳሉ ሙሉ በሙሉ ማወቅ አንችልም። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ መላእክት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ስለ አምላክ ይበልጥ ማወቅ እንዲችሉ በመርዳት ረገድ የሚጫወቱት ሚና እንዳለ ይጠቁማል።—የሐዋርያት ሥራ 8:26-35፤ 10:1-22፤ ራእይ 14:6, 7

ይሖዋ አገልጋዩ ያዕቆብ መላእክት በሰማይና በምድር መካከል በአንድ “ደረጃ” ላይ ሲወጡና ሲወርዱ በሕልም እንዲያይ አድርጓል። (ዘፍጥረት 28:10-12) ያዕቆብ ካየው ሕልም በመነሳት፣ ይሖዋ አምላክ የእሱን እርዳታ የሚፈልጉ ታማኝ ሰዎችን ለመርዳት መላእክቱን ወደ ምድር እንደሚልክ መገንዘብ እንችላለን።—ዘፍጥረት 24:40፤ ዘፀአት 14:19፤ መዝሙር 34:7

“በምድር ላይ የተተከለ ደረጃ አየ፤ የደረጃውም ጫፍ እስከ ሰማያት ይደርስ ነበር፤ በላዩም ላይ የአምላክ መላእክት ይወጡና ይወርዱ ነበር።”—ዘፍጥረት 28:12

^ አን.6 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ መናፍስት በአምላክ ሥልጣን ላይ እንዳመፁ የሚናገር ሲሆን እነዚህን ክፉ መላእክት “አጋንንት” በማለት ይጠራቸዋል።—ሉቃስ 10:17-20

^ አን.11 እንዲያውም “መልአክ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት “መልእክተኛ” የሚል ትርጉም አላቸው።