በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማንነትህን በደንብ የምታውቅ ከሆነ እንደ አውሎ ነፋስ ያሉ ነገሮችን መቋቋም ትችላለህ

 ለወጣቶች

9፦ ማንነትን ማወቅ

9፦ ማንነትን ማወቅ

ምን ማለት ነው?

የአንተን ማንነት የሚገልጸው ስምህና ውጪያዊ ገጽታህ ብቻ አይደለም። ማንነትህ የምትመራባቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች፣ የምታምንባቸውን ነገሮችና ባሕርይህን ያጠቃልላል። በእርግጥም ማንነትህ ሰዎች የሚያዩዋቸውም ሆነ የማያዩዋቸው ነገሮች ድምር ውጤት ነው።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ማንነትህን በደንብ የምታውቅ ከሆነ ለምታምንበት ነገር ጥብቅና ትቆማለህ እንጂ እኩዮችህ እንዲቆጣጠሩህ አትፈቅድም።

“ብዙ ሰዎች በሱቅ ውስጥ እንዳሉ የልብስ ማሳያ አሻንጉሊቶች ናቸው። አሻንጉሊቶቹ የሚለብሱትን ልብስ አይመርጡም፤ የሚመርጡላቸው ሌሎች ሰዎች ናቸው።”—አድሪያን

“ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ከባድ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር እንዲህ ማድረግን ተምሬያለሁ። እውነተኛ ጓደኞቼ እንደሆኑ የሚሰማኝ የእኔን አቋም የሚያከብሩልኝ ሰዎች ናቸው፤ እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር በነፃነት መቀራረብ እችላለሁ።”—ኮርትኒ

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ . . . አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:2

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ጠንካራና ደካማ ጎንህን እንዲሁም የምታምንባቸውን ነገሮች ለይተህ ለማወቅ ጥረት በማድረግ የአሁኑ ማንነትህ ምን እንደሚመስልና ወደፊት ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምትፈልግ ቆም ብለህ አስብ። የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመርህ በዚህ ረገድ ይረዳሃል፦

ጠንካራ ጎን፦ ምን ዓይነት ተሰጥኦዎችና ችሎታዎች አሉኝ? ጠንካራ ጎኖቼ ምንድን ናቸው? (ለምሳሌ ያህል፣ ሰዓት አክባሪ፣ ራሴን የምገዛ፣ ታታሪ ወይም ለጋስ ነኝ?) ምን ጠቃሚ ነገሮች እየሠራሁ ነው?

ጠቃሚ ምክር፦ ያከናወንካቸውን መልካም ነገሮች ለይተህ መጥቀስ ይከብድሃል? ከሆነ ወላጆችህ ወይም የምታምናቸው ጓደኞችህ ያሉህን ጠንካራ ጎኖች እንዲነግሩህና እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ለምን እንደሆነ ጠይቃቸው።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

ደካማ ጎን፦ ብዙ ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገኝ በየትኞቹ ባሕርያት ላይ ነው? መጥፎ ነገር ለመፈጸም ይበልጥ የምፈተነው መቼ ነው? ራሴን መግዛት የሚኖርብኝ በተለይ በየትኞቹ ዘርፎች ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “‘ኃጢአት የለብንም’ ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው።”—1 ዮሐንስ 1:8

የምታምንባቸው ነገሮች፦ የምከተላቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምን ዓይነት ናቸው? ለምንስ? በአምላክ አምናለሁ? አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው? ኢፍትሐዊ እንደሆኑ የሚሰሙኝ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? እንዲህ የሚሰማኝስ ለምንድን ነው? ወደፊት ምን ይመጣል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የማመዛዘን ችሎታ ምንጊዜም ይጠብቅሃል፤ ጥልቅ ግንዛቤም ይጋርድሃል።”—ምሳሌ 2:11