በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስታ የሚያስገኝ መንገድ

ይቅር ባይነት

ይቅር ባይነት

“ያደግኩት ብዙ ስድብና ጭቅጭቅ እየሰማሁ ነው” በማለት ፓትሪሲያ የተባለች አንዲት ሴት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በልጅነቴ ይቅር ባይነትን አልተማርኩም። አዋቂ ከሆንኩ በኋላም አንድ ሰው ቅር ሲያሰኘኝ ጉዳዩ ለብዙ ቀናት ከአእምሮዬ ስለማይወጣ እንቅልፍ ይነሳኛል።” በእርግጥም ተበሳጭቶና ቂም ይዞ የሚቆይ ሰው በሕይወቱ ደስታ የሚያጣ ከመሆኑም ሌላ ጤንነቱ ይጎዳል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይቅር ባይ ያልሆኑ ሰዎች . . .

 • በውስጣቸው ንዴት ወይም ቅሬታ ስለሚያድር ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ይበላሻል፤ በዚህም የተነሳ ራሳቸውን ያገላሉ እንዲሁም ብቸኝነት ይሰማቸዋል

 • በቀላሉ ቅር ይሰኛሉ እንዲሁም በጭንቀት ይዋጣሉ፤ አልፎ ተርፎም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሊይዛቸው ይችላል

 • በደረሰባቸው በደል ከልክ በላይ ከመብሰልሰላቸው የተነሳ በሕይወታቸው ደስታ ያጣሉ

 • ይቅር ማለት እንዳለባቸው ቢያውቁም ይህን ባለማድረጋቸው የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል

 • ከፍተኛ ውጥረት የሚሰማቸው ሲሆን እንደ ደም ግፊትና የልብ በሽታ ላሉ የጤና ቀውሶች የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው፤ እንዲሁም አርትራይተስንና ራስ ምታትን ጨምሮ ለተለያዩ ከባድ ሕመሞች ይጋለጣሉ *

ይቅር ባይነት ምንድን ነው? ይቅር ባይነት በደል ለፈጸመብን ሰው ምሕረት ማድረግ እንዲሁም በተፈጸመው በደል ምክንያት ያደረብንን ቅያሜ፣ ብስጭትና የበቀል ስሜት መተው ማለት ነው። ይቅር ባይነት ጥፋትን ችላ ብሎ ማለፍ፣ አቅልሎ መመልከት ወይም ጥፋቱን ጨርሶ እንዳልተፈጠረ አድርጎ ማሰብ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም ከበደለን ሰው ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጠር ወይም ቀድሞ የነበረን መልካም ግንኙነት እንዳይበላሽ ስንል በፍቅር ተነሳስተን የምናደርገው በሚገባ የታሰበበት ውሳኔ ነው።

በተጨማሪም ይቅር ባይ መሆናችን አስተዋይ እንደሆንን ያሳያል። ይቅር ባይ የሆነ ሰው ሁላችንም በቃልም ሆነ በድርጊት እንደምንሳሳት ወይም ኃጢአት እንደምንሠራ ይገነዘባል። (ሮም 3:23) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐቅ ግምት ውስጥ በማስገባት የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 3:13

ከዚህ አንጻር ይቅር ባይነት “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የሆነው የፍቅር ዋነኛ ገጽታ ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። (ቆላስይስ 3:14) የማዮ ክሊኒክ ድረ ገጽ እንደገለጸው ይቅር ባይነት . . .

 • አስተዋይና ሩኅሩኅ እንድንሆን እንዲሁም ራሳችንን በደል በፈጸመብን ግለሰብ ቦታ ላይ እንድናስቀምጥ ስለሚረዳን ከሰዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችላል

 • የተሻለ አእምሯዊና መንፈሳዊ ጤንነት እንዲኖረን ይረዳል

 • ጭንቀትን፣ ውጥረትንና ጥላቻን ለመቀነስ ያስችላል

 • በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ አጋጣሚን ይቀንሳል

ራስህን ይቅር በል። ዲስኤብሊቲ ኤንድ ሪሃቢሊቴሽን የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ራስን ይቅር ማለት “ከሁሉ በላይ ከባድ” ቢሆንም ለአእምሯዊና ለአካላዊ “ጤንነት እጅግ ወሳኝ ነገር” ነው። ታዲያ ራስህን ይቅር ለማለት ምን ሊረዳህ ይችላል?

 • ከራስህ ፍጽምናን አትጠብቅ፤ ከዚህ ይልቅ አንተም እንደ ማንኛውም ሰው ስህተት እንደምትሠራ አምነህ ተቀበል።—መክብብ 7:20

 • ከስህተትህ ተማር፤ ይህም ያንኑ ስህተት ደግመህ የምትሠራበትን አጋጣሚ ይቀንስልሃል

 • በራስህ ተስፋ አትቁረጥ፤ አንዳንድ የባሕርይ ችግሮችና መጥፎ ልማዶች በአንድ ጀምበር ላይወገዱ ይችላሉ።—ኤፌሶን 4:23, 24

 • አበረታች፣ አዎንታዊና ደግ ከሆኑ ሆኖም ጉድለትህን በሐቀኝነት ከሚነግሩህ ሰዎች ጋር ተቀራረብ።—ምሳሌ 13:20

 • አንድን ሰው ከበደልክ ጥፋትህን አምነህ ተቀበል እንዲሁም ወዲያውኑ ይቅርታ ጠይቅ። ካስቀየምከው ሰው ጋር ሰላም ስትፈጥር አንተም ውስጣዊ ሰላም ታገኛለህ።—ማቴዎስ 5:23, 24

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በእርግጥም ጠቃሚ ናቸው!

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰችው ፓትሪሲያ መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናች በኋላ ይቅር ማለትን ተምራለች። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ሕይወቴን መርዞት ከነበረው ንዴት ነፃ እንደወጣሁ ይሰማኛል። አሁን እንደቀድሞው አልሠቃይም፤ ሌሎችም እንዲሠቃዩ አላደርግም። የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አምላክ እንደሚወደንና ከሁሉ የተሻለውን እንደሚመኝልን ያረጋግጣሉ።”

ሮን የሚባል አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “የሌሎችን አስተሳሰብና ድርጊት መቆጣጠር አልችልም። የራሴን ግን መቆጣጠር እችላለሁ። ሰላም እንዲኖረኝ ከፈለግኩ በሌሎች ላይ ያለኝን ቅሬታ መተው አለብኝ። ሰላምና ቅሬታን ልክ እንደ ሰሜንና ደቡብ ጨርሶ የማይገናኙ ነገሮች አድርጌ መመልከት ጀመርኩ። አንድ ሰው በተመሳሳይ ጊዜ ሁለቱም ቦታዎች ላይ ሊገኝ አይችልም። አሁን ጥሩ ሕሊና ሊኖረኝ ችሏል።”

^ አን.8 ምንጭ፦ የማዮ ክሊኒክና የጆን ሆፕኪንስ ሜዲስን ድረ ገጾች እንዲሁም ሶሻል ሳይካትሪ ኤንድ ሳይካትሪክ ኤፒዲሚዮሎጂ የተባለው መጽሔት።