በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰዓት ማክበር

ሰዓት ማክበር

የማርፈድ ልማድ ያላቸው ሰዎችም እንኳ ሰዓት ማክበር አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዓት ስለ ማክበር ጠቃሚ ምክር ይሰጣል።

ሰዓት ማክበር ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

አንዳንዶች ከቀጠሮ ሰዓት ቀደም ብሎ መድረስ፣ ውጥረትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ማስተዋል ችለዋል። በተጨማሪም ሰዓት አክባሪ መሆን ጥሩ ስም ያሰጣል። እንዴት?

ሰዓት አክባሪ መሆን ለአንድ ሥራ ብቁ እንደሆንን ያሳያል። ሰዓት አክባሪ መሆንህ፣ ሁኔታዎች ያሰብከውን ነገር እንዳታከናውን እንቅፋት እንዲፈጥሩብህ ከመፍቀድ ይልቅ ነገሮችን በቁጥጥርህ ሥር ለማድረግ እንደምትሞክር በግልጽ ያሳያል።

ሰዓት አክባሪ መሆን እምነት የሚጣልብን ሰዎች እንደሆንን ያሳያል። የምንኖረው፣ ሰዎች ቃላቸውን በሚያጥፉበትና የተናገሩትን ነገር በማይፈጽሙበት ማኅበረሰብ ውስጥ ከመሆኑ አንጻር ቃላቸውን የሚያከብሩ ሰዎች ከፍ ተደርገው ይታያሉ። እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች በወዳጆቻቸውና በቤተሰባቸው ዘንድ አክብሮት ያተርፋሉ። አሠሪዎችም፣ የሥራ ሰዓት የሚያከብሩና ሥራቸውን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚያከናውኑ ሠራተኞችን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። እምነት የሚጣልባቸው ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ሊያገኙ እንዲሁም ተጨማሪ ኃላፊነት ሊሰጣቸው ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዓት አክባሪ ስለ መሆን የሚናገሩ ጥቅሶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 14:40) ሁለት ሰዎች ከተቀጣጠሩ ሰዓት አክብረው መገኘታቸው ተገቢ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወን ነገር ሁሉ ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1) አክሎም “ለመትከል ጊዜ አለው፤ የተተከለውን ለመንቀልም ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 3:2) ገበሬዎች ጥሩ ምርት ማግኘት ከፈለጉ አንድን ተክል ጊዜውን ጠብቀው በትክክለኛው ወቅት መትከል አለባቸው። በሌላ አባባል፣ የገበሬዎች ውጤታማነት የተመካው ሰዓት አክባሪ በመሆናቸው ላይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዓት አክባሪ ለመሆን የሚያነሳሳንን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሌላ ምክንያት ይገልጻል፤ ሰዓት አክባሪ መሆን ለሌሎች ሰዎችና ውድ ለሆነው ጊዜያቸው አክብሮት እንዳለን ያሳያል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) በአንጻሩ ደግሞ የማርፈድ ልማድ ያላቸው ሰዎች፣ የሌሎችን ጊዜ እየሰረቁ ነው ሊባል ይችላል።

“ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”ፊልጵስዩስ 2:4

 ሰዓት አክባሪ ለመሆን ምን ይረዳሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዕቅድ እንድናወጣ ያበረታታናል። (ምሳሌ 21:5) የማርፈድ ልማድ፣ ፕሮግራምህ ከልክ በላይ የተጣበበ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል። ታዲያ አላስፈላጊ የሆኑና ጊዜ የሚያባክኑ እንቅስቃሴዎችን ለመቀነስ ለምን አትሞክርም? በቀጠሮዎች መካከል ሰፋ ያለ ጊዜ እንዲኖርህ አድርግ፤ እንዲሁም ከቀጠሮው ሰዓት ቀደም ብለህ ለመድረስ ሞክር። ይህም እንደ ትራፊክ መጨናነቅ ወይም መጥፎ የአየር ጸባይ ያሉ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህም እንኳ በሰዓት ለመድረስ ያስችልሃል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ልካችንን እንድናውቅ ያበረታታናል። (ምሳሌ 11:2) በሌላ አባባል የአቅም ገደባችንን ማወቅ አለብን። ቀጠሮ ከመያዝህ ወይም አንድን ነገር ለማከናወን በተሰጠህ የጊዜ ገደብ ከመስማማትህ በፊት ፕሮግራምህ የሚፈቅድልህ መሆን አለመሆኑን ምክንያታዊ ሆነህ አስብ። ሁኔታህ የማይፈቅደውን ነገር ለማድረግ ከተስማማህ፣ በራስህም ሆነ በሌሎች ላይ ውጥረትና ጭንቀት ትጨምራለህ።

መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ መጠቀም እንዳለብንም ይናገራል። (ኤፌሶን 5:15, 16) ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ሥራዎች ቅድሚያ ስጥ። (ፊልጵስዩስ 1:10) ለምሳሌ ያህል፣ በሕዝብ መጓጓዣ ስትጠቀም ወይም የቀጠርካቸውን ሰዎች ስትጠብቅ ጊዜውን ለማንበብ ወይም ስለቀሪው ቀንህ ዕቅድ ለማውጣት ተጠቀምበት።

“የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።”ምሳሌ 21:5