ከዓለም አካባቢ
የዜናው ትኩረት—ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት
ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ ምክር ማግኘት ብትፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ምርጫህ ነው ወይስ የመጨረሻ? በውስጡ የሰፈረው ጥንታዊ ጥበብ በቅርቡ ከተደረሰባቸው የምርምር ውጤቶች ጋር ያለውን ዝምድና ተመልከት።
ሕንድ
በ2014 የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ከ18-25 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች 61 በመቶ የሚሆኑት ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም ወሲብ “ሕንድ ውስጥ መነጋገሪያ ጉዳይ መሆኑ ቀርቷል” የሚል እምነት አላቸው። በሙምባይ የሚኖር አንድ ሐኪም ለሂንዱስታን ታይምስ እንደገለጸው ከሆነ በእሱ አመለካከት “ወጣቶች የፍቅር ግንኙነት ጀመሩ ማለት ትዳር ለመመሥረት አስበዋል ማለት አይደለም።” ግንኙነታቸው የአንድ ቀን አዳርም ሆነ የፍቅር ግንኙነት አሊያም አብሮ መኖር፣ ዓላማቸው ጥምረቱን ለቁም ነገር ማብቃት አይደለም።
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ለአባለዘር በሽታዎችና ለስሜት ቀውስ የሚዳርገው፣ የፆታ ግንኙነት ከጋብቻ በፊት መፈጸም ነው ወይስ ከጋብቻ በኋላ?—1 ቆሮንቶስ 6:18
ዴንማርክ
ከቤተሰብ አባላት ጋር በተደጋጋሚ የሚፈጠር ጭቅጭቅ በመካከለኛው ዕድሜ ላይ የመሞት አጋጣሚን በእጥፍ ይጨምራል። በኮፐንሃገን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች 10,000 ገደማ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ያደረጉት ለ11 ዓመት የዘለቀ ጥናት እንዳሳየው፣ በጣም ከሚቀርቡት ሰው ጋር በተደጋጋሚ የሚጨቃጨቁ በመካከለኛው ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች አልፎ አልፎ ከሚጋጩ ሰዎች አንጻር ሲታይ ያለዕድሜያቸው የመሞታቸው አጋጣሚ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ጥናቱን በጽሑፍ ያወጣችው ሴት እንደተናገረችው የሚያስጨንቁ ነገሮችን መቋቋም፣ አስፈላጊ ነገሮችን ማሟላት መቻልና አለመግባባቶችን በአግባቡ መያዝ “ያለዕድሜ የሚከሰትን ሞት ለመቀነስ የሚረዱ ፍቱን ዘዴዎች እንደሆኑ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው።”—ምሳሌ 17:27
ዩናይትድ ስቴትስ
በሉዊዚያና ውስጥ በሚገኙ 564 አዲስ ተጋቢዎች ላይ በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው ግንኙነታቸው ያዝ ለቀቅ የሆነ ጥንዶች ማለትም ግንኙነታቸውን አቋርጠው እንደገና የሚቀጥሉ ፍቅረኛሞች በተጋቡ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የመለያየት አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ብዙ ጊዜ ሊጋጩና ከትዳራቸው ደስታ ሊያጡ ይችላሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አምላክ [በትዳር] ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማቴዎስ 19:6