በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 43

“ያጠነክራችኋል”—እንዴት?

“ያጠነክራችኋል”—እንዴት?

[ይሖዋ] ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።”1 ጴጥ. 5:10

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

ማስተዋወቂያ a

1. በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ጠንካራ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?

 የአምላክ ቃል ታማኝ ሰዎች ጠንካራ እንደሆኑ ይናገራል። ይሁንና በጣም ጠንካራ የሆኑት የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ጠንካራ እንዳልሆኑ የተሰማቸው ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ‘እንደ ተራራ ጠንካራ’ እንደሆነ ተሰምቶት ያውቃል፤ ሆኖም ‘የተሸበረበት’ ጊዜም አለ። (መዝ. 30:7) መንፈስ ቅዱስ ለሳምሶን ለየት ያለ ጥንካሬ ሰጥቶታል፤ ያም ቢሆን አምላክ ኃይል ባይሰጠው ኖሮ ‘አቅም እንደማይኖረውና እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እንደሚሆን’ ያውቅ ነበር። (መሳ. 14:5, 6፤ 16:17) እነዚህ ታማኝ ሰዎች ጠንካራ ሊሆኑ የቻሉት ይሖዋ ኃይል ስለሰጣቸው ብቻ ነው።

2. ጳውሎስ ደካማም ብርቱም እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው? (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10)

2 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እሱም ከይሖዋ ኃይል ማግኘት እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10ን አንብብ።) እንደ ብዙዎቻችን ሁሉ ጳውሎስም ከጤና ችግሮች ጋር ይታገል ነበር። (ገላ. 4:13, 14) ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የከበደው ጊዜም አለ። (ሮም 7:18, 19) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይጨነቅና ስጋት ያድርበት ነበር። (2 ቆሮ. 1:8, 9) ያም ቢሆን ጳውሎስ ሲደክም ያን ጊዜ ብርቱ ሆኗል። እንዴት? ይሖዋ ለጳውሎስ የጎደለውን ኃይል ስለሰጠው ነው። ጳውሎስን አጠንክሮታል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

3 ይሖዋ እኛንም እንደሚያጠነክረን ቃል ገብቶልናል። (1 ጴጥ. 5:10) ሆኖም እኛ የበኩላችንን ጥረት ሳናደርግ የእሱን እርዳታ አገኛለሁ ብለን መጠበቅ አንችልም። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ መኪና ወደ ፊት እንዲሄድ ሞተሩ ኃይል ይሰጠዋል። ያም ቢሆን ሹፌሩ ወደ ፊት መሄድ ከፈለገ ነዳጅ መስጠት አለበት። በተመሳሳይም፣ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ኃይል ሊሰጠን ፈቃደኛ ነው። ይሁንና የእሱን እርዳታ ለማግኘት በእኛ በኩል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልገናል። ይሖዋ እኛን ለማጠንከር ሲል ምን ዝግጅት አድርጓል? ከእሱ ኃይል ለማግኘትስ ምን ማድረግ ያስፈልገናል? ይሖዋ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮችን ያጠነከራቸው እንዴት እንደሆነ በመመርመር እነዚህን ጥያቄዎች እንመልሳለን፤ እነሱም ነቢዩ ዮናስ፣ የኢየሱስ እናት ማርያም እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ ናቸው። በተጨማሪም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉ አገልጋዮቹን በተመሳሳይ መንገዶች የሚያጠነክራቸው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ከጸሎትና ከጥናት ጥንካሬ ማግኘት

4. ከይሖዋ ኃይል ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

4 ከይሖዋ ኃይል ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ወደ እሱ በጸሎት መቅረብ ነው። ይሖዋም ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ በመስጠት ጸሎታችንን ይመልስልናል። (2 ቆሮ. 4:7) ቃሉን ማንበባችንና ማሰላሰላችንም ሊያጠነክረን ይችላል። (መዝ. 86:11) አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያስተላለፈልን መልእክት “ኃይለኛ ነው።” (ዕብ. 4:12) ወደ ይሖዋ ስትጸልይና ቃሉን ስታነብ ለመጽናት፣ ደስታህን ለመጠበቅ ወይም የተሰጠህን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልግህን ጥንካሬ ታገኛለህ። ይሖዋ ነቢዩ ዮናስን ያጠነከረው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

5. ነቢዩ ዮናስ ጥንካሬ ያስፈለገው ለምን ነበር?

5 ነቢዩ ዮናስ ጥንካሬ አስፈልጎት ነበር። ይሖዋ ከሰጠው ከባድ ኃላፊነት ለመሸሽ ሞክሯል። በዚህም ምክንያት እሱም ሆነ አብረውት በመርከብ ላይ የተሳፈሩት ሰዎች በኃይለኛ ማዕበል የተነሳ ሊሞቱ ተቃርበው ነበር። ከዚያም መርከበኞቹ ወደ ባሕሩ ሲወረውሩት አንድ ዓሣ ነባሪ ዋጠው። ዮናስ ጨለማና አስፈሪ በሆነው የዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሳለ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ? እዚያው እንደሚሞት አስቦ ይሆን? ይሖዋ እንደተወው ተሰምቶት ይሆን? መቼም ዮናስ በጣም ተጨንቆ መሆን አለበት።

ፈተና ሲያጋጥመን እንደ ነቢዩ ዮናስ ጥንካሬ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 6-9⁠ን ተመልከት)

6. በዮናስ 2:1, 2, 7 መሠረት ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ በነበረበት ወቅት ጥንካሬ የሰጠው ምንድን ነው?

6 ዮናስ ብቻውን በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሳለ ጥንካሬ ለማግኘት ምን አደረገ? በመጀመሪያ ደረጃ ጸለየ። (ዮናስ 2:1, 2, 7ን አንብብ።) የይሖዋን ትእዛዝ የጣሰ ቢሆንም በትሕትና የሚያቀርበውን የንስሐ ጸሎት ይሖዋ እንደሚሰማው እርግጠኛ ነበር። በተጨማሪም ዮናስ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አሰላስሏል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በዮናስ ምዕራፍ 2 ላይ እንደምናነበው በጸሎቱ ላይ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቃላትና ሐረጎችን ተጠቅሟል። (ለምሳሌ ዮናስ 2:2, 5⁠ን ከመዝሙር 69:1፤ 86:7 ጋር አወዳድር።) ዮናስ እነዚህን ጥቅሶች በደንብ እንደሚያውቃቸው ግልጽ ነው። በመከራ ውስጥ በነበረበት ወቅት በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰሉ ይሖዋ እንደሚረዳው እንዲተማመን ረድቶታል። በኋላም ዓሣ ነባሪው በደረቅ መሬት ላይ ሲተፋው ቀጥሎ የሚሰጠውን ኃላፊነት ለመቀበልና ለመወጣት ዝግጁ ነበር።—ዮናስ 2:10–3:4

7-8. በታይዋን የሚኖር አንድ ወንድም በፈተና ውስጥ በነበረበት ወቅት ጥንካሬ ያገኘው እንዴት ነው?

7 የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የዮናስ ምሳሌ ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ በታይዋን የሚኖረው ጅሚንግ b ከባድ የጤና እክሎች አሉበት። ከዚህም ሌላ በይሖዋ ላይ ባለው እምነት የተነሳ ቤተሰቦቹ ክፉኛ ይቃወሙታል። ሆኖም በጸሎትና በጥናት አማካኝነት ከይሖዋ ጥንካሬ አግኝቷል። እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ሲያጋጥሙኝ በጭንቀት ከመዋጤ የተነሳ የግል ጥናት ለማድረግ የሚያስችል መረጋጋት አይኖረኝም።” ያም ቢሆን ወንድማችን ተስፋ አልቆረጠም። እንዲህ ብሏል፦ “በመጀመሪያ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ከዚያም የጆሮ ማዳመጫዬን አድርጌ የመንግሥቱን መዝሙሮች እሰማለሁ። አንዳንድ ጊዜም መረጋጋት እስክችል ድረስ መዝሙሮቹን ዝግ ባለ ድምፅ እዘምራቸዋለሁ። ከዚያም ማጥናት እጀምራለሁ።”

8 ጅሚንግ የግል ጥናት ማድረጉ በአስደናቂ ሁኔታ ጥንካሬ ሰጥቶታል። ለምሳሌ ከባድ ቀዶ ሕክምና አድርጎ እያገገመ በነበረበት ወቅት አንዲት ነርስ የቀይ የደም ሴሉ መጠን ዝቅ ስላለ ደም መውሰድ እንደሚያስፈልገው ነገረችው። ጅሚንግ ቀዶ ሕክምና ከማድረጉ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የእሱን ዓይነት ቀዶ ሕክምና ስላደረገች እህት የሚገልጽ ተሞክሮ አንብቦ ነበር። ይህች እህት የቀይ የደም ሴሏ መጠን ከእሱ ይበልጥ ዝቅ ብሎ የነበረ ቢሆንም ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆነችም፤ ነገር ግን ማገገም ችላለች። ይህ ተሞክሮ ጅሚንግ ታማኝነቱን እንዲጠብቅ ጥንካሬ ሰጥቶታል።

9. ያጋጠመህ ፈተና አቅምህን ካሟጠጠው ምን ማድረግ ትችላለህ? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 በፈተና ውስጥ ስትሆን በጭንቀት ከመዋጥህ የተነሳ ሐሳብህን አቀናብረህ መጸለይ እንደማትችል ይሰማሃል? ወይም ደግሞ አቅምህ ከመሟጠጡ የተነሳ ማጥናት እንደማትችል ይሰማሃል? ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልህ አስታውስ። በመሆኑም የምታቀርበው ጸሎት በጣም አጭር ቢሆንም እንኳ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ኤፌ. 3:20) ያጋጠመህ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሥቃይ ማንበብና ማጥናት ከባድ እንዲሆንብህ ካደረገ የመጽሐፍ ቅዱስን ወይም የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን የድምፅ ቅጂ ማዳመጥ ትችላለህ። jw.org ላይ የሚገኙትን መዝሙሮቻችንን ማዳመጥ ወይም ቪዲዮዎቻችንን መመልከትም ሊረዳህ ይችላል። ወደ ይሖዋ ስትጸልይ እንዲሁም እሱ ባደረጋቸው ዝግጅቶች አማካኝነት የጸሎትህን መልስ ለማግኘት ጥረት ስታደርግ እሱ እንዲያጠነክርህ እየጋበዝከው ነው ሊባል ይችላል።

ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጥንካሬ ማግኘት

10. ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያጠነክሩን እንዴት ነው?

10 ይሖዋ እኛን ለማጠንከር በክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሊጠቀም ይችላል። አንድ ፈተና ሲያጋጥመን ወይም የተሰጠንን አስቸጋሪ ኃላፊነት መወጣት ሲከብደን ወንድሞቻችን “የብርታት ምንጭ” ሊሆኑልን ይችላሉ። (ቆላ. 4:10, 11) በተለይ ‘በመከራ ቀን’ ጓደኞች ያስፈልጉናል። (ምሳሌ 17:17) ስንደክም የእምነት አጋሮቻችን ቁሳዊ፣ ስሜታዊ ወይም መንፈሳዊ እርዳታ ሊሰጡን ይችላሉ። የኢየሱስ እናት ማርያም ከሌሎች ጥንካሬ ያገኘችው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

11. ማርያም ጥንካሬ ያስፈለጋት ለምንድን ነው?

11 ማርያም ጥንካሬ አስፈልጓት ነበር። መልአኩ ገብርኤል ከባድ ኃላፊነት በሰጣት ወቅት ሁኔታው ምን ያህል አሳስቧት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው። በወቅቱ ማርያም አላገባችም፤ ሆኖም እንደምትፀንስ ተነገራት። የራሷን ልጆች አሳድጋ አታውቅም፤ ሆኖም መሲሑን ማሳደግ ሊኖርባት ነው። ደግሞም ከወንድ ጋር ግንኙነት ሳትፈጽም ስላረገዘች ሁኔታውን ለእጮኛዋ ለዮሴፍ እንዴት ልታብራራለት ትችላለች?—ሉቃስ 1:26-33

12. በሉቃስ 1:39-45 መሠረት ማርያም የሚያስፈልጋትን ጥንካሬ ያገኘችው እንዴት ነው?

12 ማርያም የተሰጣትን እንግዳና ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ ያገኘችው እንዴት ነው? የሌሎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርጋለች። ለምሳሌ የተሰጣትን ኃላፊነት አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጣት ገብርኤልን ጠይቃዋለች። (ሉቃስ 1:34) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ረጅም መንገድ ተጉዛ “በተራራማው አገር” ወደምትገኝ አንዲት የይሁዳ ከተማ ሄዳለች። እንዲህ በማድረጓም በእጅጉ ተጠቅማለች። ኤልሳቤጥ ማርያምን አመሰገነቻት፤ እንዲሁም በይሖዋ መንፈስ ተመርታ በማርያም ማኅፀን ውስጥ ያለውን ልጅ በተመለከተ የሚያበረታታ ትንቢት ተናገረች። (ሉቃስ 1:39-45ን አንብብ።) ማርያም፣ ይሖዋ ‘በክንዱ ታላላቅ ሥራዎች እንዳከናወነ’ ገልጻለች። (ሉቃስ 1:46-51) ይሖዋ በገብርኤልና በኤልሳቤጥ አማካኝነት ማርያምን አጠንክሯታል።

13. በቦሊቪያ የምትኖር አንዲት እህት የእምነት ባልንጀሮቿን እርዳታ በመጠየቋ የተጠቀመችው እንዴት ነው?

13 አንተም እንደ ማርያም ከእምነት ባልንጀሮችህ ጥንካሬ ማግኘት ትችላለህ። በቦሊቪያ የምትኖር ዳሱሪ የተባለች እህት እንዲህ ያለ ጥንካሬ አስፈልጓት ነበር። አባቷ በማይድን በሽታ ተይዞ ሆስፒታል በገባበት ወቅት ዳሱሪ እሱን ለመንከባከብ ራሷን በፈቃደኝነት አቀረበች። (1 ጢሞ. 5:4) እርግጥ ሁኔታው ቀላል አልነበረም። ዳሱሪ “በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማልችል ብዙ ጊዜ ይሰማኝ ነበር” ብላለች። ታዲያ የሌሎችን እርዳታ ጠየቀች? መጀመሪያ ላይ አልጠየቀችም ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞችን ማስቸገር አልፈለግኩም። የሚያስፈልገኝን እርዳታ የሚሰጠኝ ይሖዋ ራሱ ነው ብዬ አስቤ ነበር። በኋላ ግን፣ ራሴን ከሌሎች ካገለልኩ ችግሬን ብቻዬን ለመወጣት እየሞከርኩ እንደሆነ ገባኝ።” (ምሳሌ 18:1) ዳሱሪ ያለችበትን ሁኔታ በተመለከተ ለአንዳንድ ጓደኞቿ ለመጻፍ ወሰነች። እንዲህ ብላለች፦ “ከውድ ወንድሞቼና እህቶቼ ምን ያህል ጥንካሬ እንዳገኘሁ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። ምግብ ይዘው ወደ ሆስፒታሉ ይመጡ እንዲሁም የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያካፍሉኝ ነበር። ብቻችንን እንዳልሆንን ማወቅ በራሱ ልዩ ስሜት ይፈጥራል። ሰፊ የሆነው የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ነን። ቤተሰቦቻችን የእርዳታ እጃቸውን ሊዘረጉልን፣ አብረውን ሊያለቅሱ እንዲሁም ያጋጠመንን ችግር አብረውን ሊጋፈጡ ፈቃደኞች ናቸው።”

14. የሽማግሌዎችን እርዳታ መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ ለእኛ ኃይል የሚሰጥበት አንዱ መንገድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ነው። ሽማግሌዎች፣ ይሖዋ እኛን ለማጠንከርና መንፈሳችንን ለማደስ የሚጠቀምባቸው ስጦታዎች ናቸው። (ኢሳ. 32:1, 2) እንግዲያው በጭንቀት ስትዋጥ ያሳሰበህን ነገር ለሽማግሌዎች ንገራቸው። ሊረዱህ ሲሞክሩ እርዳታቸውን በአመስጋኝነት ተቀበል። ይሖዋ በእነሱ አማካኝነት ሊያጠነክርህ ይችላል።

ከወደፊቱ ተስፋችን ጥንካሬ ማግኘት

15. ሁሉም ክርስቲያኖች የትኛውን ተስፋ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል?

15 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችን ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል። (ሮም 4:3, 18-20) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን፣ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ወይም በሰማያዊው መንግሥት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ውድ ተስፋ አለን። ተስፋችን ፈተናዎችን በጽናት እንድንቋቋም፣ ምሥራቹን እንድንሰብክ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉንን የተለያዩ ኃላፊነቶች እንድንወጣ ጥንካሬ ይሰጠናል። (1 ተሰ. 1:3) ሐዋርያው ጳውሎስንም ያጠነከረው ይኸው ተስፋ ነው።

16. ሐዋርያው ጳውሎስ ጥንካሬ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

16 ጳውሎስ ጥንካሬ አስፈልጎት ነበር። ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ራሱን ደካማ ከሆነ የሸክላ ዕቃ ጋር አወዳድሯል። ‘ተደቁሶ፣ ግራ ተጋብቶ፣ ስደት ደርሶበት እንዲሁም በጭንቀት ተውጦ’ ነበር። ይባስ ብሎም ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቋል። (2 ቆሮ. 4:8-10) ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ላይ በነበረበት ወቅት ነው። ጳውሎስ በወቅቱ ባያውቀውም ገና ብዙ መከራ ይጠብቀው ነበር። የዓመፀኞች ጥቃት፣ የመርከብ መሰበር አደጋ እንዲሁም እስራት ያጋጥመዋል።

17. በ2 ቆሮንቶስ 4:16-18 መሠረት ጳውሎስ ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋም ጥንካሬ የሰጠው ምንድን ነው?

17 ጳውሎስ በተስፋው ላይ ትኩረት ማድረጉ ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬ ሰጥቶታል። (2 ቆሮንቶስ 4:16-18ን አንብብ።) ውጫዊ ሰውነቱ “እየመነመነ ቢሄድም” እንኳ ይህ ሁኔታ ተስፋ እንዲያስቆርጠው እንደማይፈቅድ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ነግሯቸዋል። ጳውሎስ በወደፊቱ ጊዜ ላይ ትኩረት አድርጓል። በሰማይ ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋው “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድና ዘላለማዊ የሆነ ክብር” የሚያስገኝ ነው፤ ጳውሎስ ይህን ሽልማት ለማግኘት ሲል ማንኛውንም መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። ጳውሎስ በዚህ ተስፋ ላይ አሰላስሏል። ይህም “ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ” እንዲሄድ ረድቶታል።

18. የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለቲሆሚርና ለቤተሰቡ ጥንካሬ የሰጣቸው እንዴት ነው?

18 በቡልጋሪያ የሚኖር ቲሆሚር የተባለ ወንድም በተስፋው ጥንካሬ አግኝቷል። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት፣ ታናሽ ወንድሙ ስትራቭኮ በመኪና አደጋ ሞተ። ከዚያ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቲሆሚር በከባድ ሐዘን ተውጦ ነበር። እሱና ቤተሰቡ ሐዘናቸውን ለመቋቋም ሲሉ፣ የትንሣኤ ተስፋ ሲፈጸም የሚኖረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናቸው ለመሣል ጥረት ያደርጋሉ። ቲሆሚር እንዲህ ብሏል፦ “ለምሳሌ ስትራቭኮን የት እንደምናገኘው፣ ምን ዓይነት ምግብ እንደምንሠራለት፣ እሱን ለመቀበል በምናዘጋጀው የመጀመሪያ ግብዣ ላይ እነማንን እንደምንጋብዝ እንዲሁም ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ምን እንደምንነግረው እንወያያለን።” ቲሆሚር፣ እሱና ቤተሰቡ በዚህ ተስፋ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው እንዲጸኑ ጥንካሬ እንደሰጣቸው እንዲሁም ይሖዋ ወንድሙን የሚያስነሳበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት እንዲጠብቁ እንደረዳቸው ተናግሯል።

በአዲሱ ዓለም ስለሚኖርህ ሕይወት ስታስብ ምን ይታይሃል? (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት) c

19. ተስፋህን ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

19 ተስፋህን ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ተስፋህ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገነት የሚሰጠውን መግለጫ አንብበህ አሰላስልበት። (ኢሳ. 25:8፤ 32:16-18) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናህ ሣል። በዚያ ስትኖር ይታይህ። በአካባቢህ ማን አለ? ምን ዓይነት ድምፆች አሉ? አንተስ ምን ይሰማሃል? ተስፋህ ሕያው ሆኖ እንዲታይህ በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ ገነትን የሚያሳዩ ሥዕሎችን ወይም የሙዚቃ ቪዲዮዎችን ተመልከት። ከእነዚህ የሙዚቃ ቪዲዮዎች መካከል ያ አዲስ ዘመን ሩቅ አይደለም ያ ጊዜ እና ያ ቀን ይታይህ የሚሉት መዝሙሮች ይገኙበታል። አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ባለን ተስፋ ላይ ካተኮርን አሁን ያሉብን ችግሮች “ጊዜያዊና ቀላል” ይሆኑልናል። (2 ቆሮ. 4:17) ይሖዋ በተስፋው አማካኝነት ጥንካሬ ይሰጥሃል።

20. እንደደከምን በሚሰማን ጊዜም እንኳ ኃይል ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

20 እንደደከምን በሚሰማን ጊዜም እንኳ “አምላክ ኃይል ይሰጠናል።” (መዝ. 108:13) ይሖዋ ከእሱ ጥንካሬ ማግኘት የምንችልባቸውን ዝግጅቶች አድርጎልናል። እንግዲያው አንድን ኃላፊነት ለመወጣት፣ አንድን ፈተና በጽናት ለመቋቋም ወይም ደስታህን ለመጠበቅ እርዳታ ሲያስፈልግህ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቅርብ። እንዲሁም በግል ጥናት አማካኝነት የእሱን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርግ። ክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ የሚሰጡህን ማበረታቻ ተቀበል። ተስፋህ ምንጊዜም ብሩህ እንዲሆን አድርግ። እንዲህ ካደረግክ ‘በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት እንድትቋቋም የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልግህን ብርታት ሁሉ ይሰጥሃል።’—ቆላ. 1:11

መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ

a ይህ ርዕስ፣ ያጋጠማቸው ፈተና ወይም የተሰጣቸው ኃላፊነት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው የሚሰማቸውን ሰዎች የሚረዱ ሐሳቦችን ይዟል። ይሖዋ የሚያጠነክረን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የእሱን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ መስማት የተሳናት አንዲት እህት በመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ላይ ስታሰላስልና በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖራትን ሕይወት በዓይነ ሕሊናዋ ለመሣል እንዲረዳት የሙዚቃ ቪዲዮ ስትመለከት።