የሕይወት ታሪክ
በግል ትኩረት መስጠት የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል
“የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን እውነትን አያስተምርም። እውነትን በራስሽ ፈልጊ።” ይህን ያለችው የአንግሊካን እምነት ተከታይ የሆነችው አያቴ ናት፤ እናቴም ይህን ሰምታ እውነተኛውን ሃይማኖት መፈለግ ጀመረች። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መነጋገር ግን አልፈለገችም፤ ቤታችን ከመጡ እንድደበቅ ነግራኝ ነበር፤ ያኔ የምንኖረው ቶሮንቶ፣ ካናዳ ነበር። በኋላ ግን በ1950 የእናቴ ታናሽ እህት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረች፤ እናቴም ጥናቱን ተቀላቀለች። የሚያጠኑት አክስቴ ቤት ነበር፤ በኋላም ተጠመቁ።
አባቴ በአካባቢው ባለው የካናዳ የተባበሩት አብያተ ክርስቲያናት አጥቢያ ሽማግሌ ነበር፤ ስለዚህ በየሳምንቱ ከእህቴ ጋር ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ይልከናል፤ ከዚያ ደግሞ ከረፋዱ 5:00 ላይ የቤተ ክርስቲያን ፕሮግራም ሲጀምር አብረነው እንቀጥላለን። ከሰዓት በኋላ ከእናቴ ጋር ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ እንሄዳለን። ሁለቱ ሃይማኖቶች ምን ያህል እንደሚለያዩ ለማየት ጊዜ አልፈጀብንም።
እናቴ፣ ቦብ እና ማርየን ሃችሰን የተባሉ የረጅም ጊዜ ወዳጆች ነበሯት፤ አዲስ የተማረችውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስትነግራቸው ባልና ሚስቱ እውነትን ተቀበሉ። በ1958 ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ “መለኮታዊ ፈቃድ” የተሰኘ የስምንት ቀን ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፤ እነዚህ የእናቴ ወዳጆች ከሦስት ወንዶች ልጆቻቸው ጋር ወደዚህ ስብሰባ ይዘውኝ ሄዱ። እኔን ለመውሰድ ሲሉ ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደከፈሉ የገባኝ በኋላ ነው። ሆኖም ይህ ስብሰባ በሕይወቴ ውስጥ ከማልረሳቸው ክንውኖች አንዱ ነው።
በግል የሰጡኝ ትኩረት የወደፊት ሕይወቴን ቀርጾታል
በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ እንስሳት እናረባ ነበር፤ እኔም እዚያው ስሠራ እንስሳትን የመንከባከብ ፍላጎት አደረብኝ። እንዲያውም የእንስሳት ሐኪም ስለ መሆን በቁም ነገር ማሰብ ጀመርኩ። እናቴ ስለ ግቤ ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ነገረችው። እሱም የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” እንደሆነ በደግነት ነገረኝ፤ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለብዙ ዓመታት ትምህርት መከታተል ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና እንዴት እንደሚነካብኝ 2 ጢሞ. 3:1) እኔም አሰብኩበትና ዩኒቨርሲቲ ላለመግባት ወሰንኩ።
ቆም ብዬ እንዳስብበት ጠየቀኝ። (ያም ቢሆን፣ ‘የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ምን አደርጋለሁ?’ የሚለው ነገር ግራ አጋብቶኝ ነበር። በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ አገልግሎት ብወጣም ያን ያህል የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም፤ አቅኚ እሆናለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም። አማኝ ያልሆነው አባቴና አጎቴ ደግሞ ቶሮንቶ ውስጥ ባለ ስመ ጥር የመድን ድርጅት ውስጥ ሙሉ ቀን ተቀጥሬ እንድሠራ አበረታቱኝ። አጎቴ በዚህ ድርጅት ውስጥ ሥልጣን ስለነበረው እዚያው ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ።
የቶሮንቶ ሕይወቴ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚመች አልነበረም፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ተጨማሪ ሰዓት እሠራለሁ፤ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፋለሁ። መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ አያቴ ጋር እኖር ነበር፤ እሱ ከሞተ በኋላ ግን ቤት መፈለግ ነበረብኝ።
በ1958 ወደተካሄደው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የወሰዱኝን እነዚያን ባልና ሚስት እንደ ወላጆቼ ነበር የማያቸው። አብሬያቸው እንድኖር ጋበዙኝ፤ ከዚያም በእነሱ እርዳታ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ቻልኩ። በ1960 እኔና ጆን የተባለው ልጃቸው አብረን ተጠመቅን። ጆን በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ፤ እኔም ይህን ሳይ በአገልግሎት የማደርገውን ተሳትፎ ለመጨመር ተነሳሳሁ። የጉባኤያችን ወንድሞች የማደርገውን መንፈሳዊ እድገት ማስተዋላቸው አልቀረም፤ ብዙም ሳይቆይ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። a
ውድ አጋርና አዲስ የሕይወት መንገድ
በ1966 ራንዲ በርግ ከተባለች ቀናተኛ አቅኚ ጋር ተጋባን፤ ራንዲ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄዳ የማገልገል ጉጉት ነበራት። ተጓዥ የበላይ ተመልካቻችን በግል ትኩረት ሰጥቶ ያበረታታን ጀመር፤ በኦሪሊያ፣ ኦንታሪዮ ወደሚገኘው ጉባኤ ተዛውረን እንድንረዳ ጠየቀን። ወዲያውኑ ዕቃችንን ሸክፈን ወደዚያ ሄድን።
ኦሪሊያ ከሄድን ብዙም ሳይቆይ እኔም እንደ ራንዲ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። ቅንዓቷ ወደ እኔም ተጋብቶ ነበር! በሙሉ ልቤ በአቅኚነት መሳተፍ ስጀምር ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ አየሁ፤ አገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም እንዲሁም ሰዎች እውነትን ሲቀበሉ ማየት እንዴት ደስ የሚል ነው!
ሌላም በረከት አግኝተናል፤ በኦሪሊያ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት በሕይወታቸው ላይ ለውጥ እንዲያደርጉና የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት ችለናል።የቋንቋና የአመለካከት ለውጥ
ለተወሰነ ጊዜ ቶሮንቶ በሄድንበት ወቅት አርኖልድ ማክናማራ ከተባለ ወንድም ጋር ተገናኘን፤ ይህ ወንድም በቤቴል አመራር ይሰጡ ከነበሩት ወንድሞች አንዱ ነው። “ልዩ አቅኚ መሆን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቀን። ወዲያውኑ መልስ ሰጠሁ፤ “በሚገባ! ኩዊቤክ አይሁን እንጂ የትም ቦታ!” አልኩት። ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ባሉበት የኩዊቤክ ግዛት ውስጥ በወቅቱ አለመረጋጋት ነበር። ኩዊቤክ ከቀረው የካናዳ ክፍል እንድትገነጠል የሚደረግ የፖለቲካ ንቅናቄም ነበር። በዚህም የተነሳ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ባሉበት የካናዳ ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ለኩዊቤክ አሉታዊ አመለካከት ነበራቸው፤ እኔም ይህ አመለካከት ተጽዕኖ አሳድሮብኝ እንደነበር አልክድም።
አርኖልድ “በአሁኑ ወቅት ቅርንጫፍ ቢሮው ልዩ አቅኚዎችን የሚልከው ወደ ኩዊቤክ ብቻ ነው” አለኝ። እኔም ሳላቅማማ እሺ አልኩ። ራንዲ እዚያ ሄደሽ አገልግዪ ብትባል ደስ እንደሚላት ቀድሞውኑም አውቃለሁ። ይህ ውሳኔ በሕይወታችን ካደረግናቸው ምርጥ ውሳኔዎች አንዱ እንደሆነ የገባኝ በኋላ ላይ ነው።
የአምስት ሳምንት የፈረንሳይኛ ሥልጠና ወሰድን። ከዚያም እኔና ራንዲ ከሌላ ባልና ሚስት ጋር ወደ ሪሙስኪ ሄድን፤ ሪሙስኪ ከሞንትሪያል በስተ ሰሜን ምሥራቅ 540 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። የቋንቋ ችሎታችን ገና ብዙ ይቀረው ነበር፤ ለምሳሌ በአንድ ስብሰባ ላይ ማስታወቂያ ሳነብ የሠራሁትን ስህተት ልንገራችሁ። በቀጣዩ ትልቅ ስብሰባ ላይ “የኦስትሪያ ልዑካን ይመጣሉ” ማለት ፈልጌ “የኦስትሪች (የሰጎን) ልዑካን ይመጣሉ” አልኩ።
ሪሙስኪ ውስጥ ከእኛ ከአራታችን በተጨማሪ አራት ቀናተኛ ያላገቡ እህቶች ነበሩ፤ ወንድም ሂውበርዶና ባለቤቱ እንዲሁም ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውም እዚያ ነበሩ። ወንድም ሂውበርዶና ባለቤቱ ሰባት መኝታ ክፍሎች ያሉት ትልቅ ቤት ተከራዩና እኛ አቅኚዎቹ አብረናቸው እንድንኖር ጋበዙን፤ ኪራዩን ለመሸፈን እኛም እናዋጣ ነበር። የቤቱ ዓምዶችና ፊት ለፊቱ ነጭ ቅብ ስለነበራቸው “ነጩ ቤት” (ዃይት ሃውስ) ብለን እንጠራው ነበር። በአብዛኛው ከ12 እስከ 14 ሰዎች ሆነን እንኖር ነበር፤ እኔና ራንዲ ልዩ አቅኚዎች ስለሆንን ሁልጊዜ ጠዋት፣ ከሰዓት በኋላና ምሽት ላይ አገልግሎት እንወጣለን። ሁልጊዜም በተለይ ክረምቱን አመሻሽ ላይ አብሮን የሚወጣ ሰው አጥተን ስለማናውቅ በጣም አመስጋኞች ነን።
ከእነዚያ ታማኝ አቅኚዎች ጋር በጣም ተቀራርበናል፤ የቤተሰብ ያህል ነው የሆኑልን። አንዳንዴ እሳት እናነድና ዙሪያውን እንቀመጣለን፤ ከዚያም እዚያው የሚጠባበሱ ምግቦች አዘጋጅተን እንበላለን። አንደኛው ወንድም ሙዚቀኛ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ቅዳሜ ቅዳሜ ማታ አብረን እንዘምራለን እንዲሁም እንደንሳለን።
በሪሙስኪ ክልል ያከናወንነው አገልግሎት ፍሬያማ ሆነ! በአምስት ዓመት ውስጥ በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት አድርገው ሲጠመቁ አይተናል። የጉባኤው አስፋፊዎች ብዛትም 35 ደረሰ።
በኩዊቤክ ያሳለፍነው ጊዜ ጥሩ የወንጌላዊነት ሥልጠና ያገኘንበት ነው። ይሖዋ በአገልግሎት እንዲሁም የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች በማሟላት ሲረዳን ተመልክተናል። ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆኑትን ሰዎች፣ ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውንም እየወደድነው መጣን። ይህም ለሌሎች ባሕሎች ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖረን ረድቶናል።—2 ቆሮ. 6:13
በኋላ ግን ያልጠበቅነው ለውጥ መጣ፤ ቅርንጫፍ ቢሮው ትራከዲ ወደተባለች ትንሽ ከተማ እንድንዛወር ጠየቀን። ትራከዲ በኒው ብረንስዊክ ምሥራቃዊ ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ይህን ውሳኔ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ምክንያቱም በአንድ አፓርታማ ላይ ቤት አግኝተን ገና የኪራይ ውል መፈጸማችን ነበር፤ ከዚህም ሌላ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ በሳምንት ለተወሰኑ ሰዓታት በአስተማሪነት መሥራት ጀምሬያለሁ። ይህ ብቻ አይደለም፤ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ
ጥናቶቻችን ገና አስፋፊዎች መሆናቸው ነው፤ የስብሰባ አዳራሻችን ግንባታም በሂደት ላይ ነበር።ያን ቅዳሜና እሁድ በሙሉ ስለ ጉዳዩ ስንጸልይ ቆየን። ከዚያም ለጉብኝት ወደ ትራከዲ ሄድን፤ ትራከዲ አሁን ካለንበት ከሪሙስኪ ከተማ ብዙ እንደምትለይ ገባን። ይሖዋ እዚያ እስከፈለገን ድረስ ግን ለመሄድ ቆረጥን። ይሖዋን ለመፈተን ወሰንን፤ እሱም መሰናክሎቹን አንድ በአንድ ሲያነሳልን ተመልክተናል። (ሚል. 3:10) ዕቃ ሸክፎ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው መዛወር የራሱ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት፤ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የራንዲ ጠንካራ መንፈሳዊነት፣ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስና ተጫዋችነቷ ሁኔታውን አቅልሎታል።
በአዲሱ ጉባኤያችን ውስጥ ያለው ብቸኛ ሽማግሌ ሮበርት ሮስ ነበር። እሱና ባለቤቱ ሊንዳ ወደዚህ አካባቢ የመጡት ለአቅኚነት ነበር። በኋላ ግን ልጅ ሲመጣ እዚያው ለመቀጠል ወሰኑ። ልጅ ማሳደግ በራሱ ትልቅ ኃላፊነት ቢሆንም ሮበርትና ሊንዳ እኛን ለማበረታታት ብዙ ነገር አድርገዋል። እንግዳ ተቀባዮች እንዲሁም ቆራጥና ቀናተኛ ሰባኪዎች ነበሩ።
በተፈለጉበት ቦታ ማገልገል የሚያስገኘው በረከት
ትራከዲ ውስጥ ለሁለት ዓመታት በአቅኚነት ካገለገልን በኋላ ሌላ ያልጠበቅነው ለውጥ መጣ፤ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነን እንድናገለግል ተጠየቅን። ለሰባት ዓመት ያህል እንግሊዝኛ ወረዳዎች ውስጥ ስናገለግል ቆየን፤ ከዚያም ኩዊቤክ ውስጥ በሚገኝ የፈረንሳይኛ ወረዳ እንድናገለግል ተመደብን። የኩዊቤክ የአውራጃ የበላይ ተመልካቻችን ሊዮንስ ክሪፖ ነበር። ንግግር ካቀረብኩ በኋላ ሁሌም በመጀመሪያ ያመሰግነኛል፤ ከዚያ ግን “ወንድሞች ይበልጥ እንዲጠቀሙ ምን ማድረግ ትችል ነበር?” ብሎ ይጠይቀኛል። b በግል ትኩረት ሰጥቶ ያደረገልኝ እርዳታ በማስተማር ችሎታዬ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፤ የማስተምርበት መንገድ ይበልጥ ግልጽና በቀላሉ የሚገባ እንዲሆን ረድቶኛል።
በ1978 ሞንትሪያል ውስጥ “ድል አድራጊ እምነት” የተሰኘ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የተሰጠኝ ኃላፊነት በሕይወቴ ውስጥ ልዩ ትዝታ ጥለውብኝ ካለፉ የሥራ ምድቦች አንዱ ነው። የተመደብኩት የምግብ አገልግሎት ክፍል ውስጥ ነው። በስብሰባው ላይ 80,000 ሰዎች እንደሚገኙ ጠብቀናል፤ በመሆኑም አዲስ ዓይነት የምገባ ዝግጅት ለማድረግ ተወሰነ። የምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች፣ የሚቀርበው ምግብ፣ የምግብ አዘገጃጀታችን ብቻ ሁሉ ነገር አዲስ ነው። ቀደም ሲል 20 ትላልቅ ተጎታች ማቀዝቀዣዎች ነበሩን፤ ሆኖም ብልሽት የሚያጋጥማቸው ጊዜ አለ። ከስብሰባው በፊት ባለው ቀን ደግሞ ስታዲየሙ ውስጥ አንድ ስፖርታዊ ውድድር ይካሄድ ነበር፤ በመሆኑም ወደ ስታዲየሙ መግባትና ዕቃዎቻችንን ማዘጋጀት የቻልነው እኩለ ሌሊት ላይ ነው። ጎህ ሳይቀድ ተነስተን ደግሞ ቁርስ ለመሥራት ምድጃዎቻችንን ለኮስን! አድካሚ ነበር፤ ሆኖም
አብረውኝ የተመደቡት ፈቃደኛ ሠራተኞች ትጉ፣ በሳልና ተጫዋች ናቸው። ከእነሱ ብዙ ተምሬያለሁ፤ ሥራው አቀራርቦናል፤ አሁንም ድረስ ጥሩ ወዳጆች ነን። ኩዊቤክ በ1940ዎቹና በ1950ዎቹ ዓመታት መራራ ተቃውሞ የነበረበት ግዛት ነው፤ በዚህ ቦታ ይህን ታሪካዊ ስብሰባ ማድረግ ምንኛ የሚያስደስት ነው!ሞንትሪያል ውስጥ በተካሄዱ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንደ እኔው የበላይ ተመልካች ሆነው ካገለገሉ ወንድሞች ብዙ ተምሬያለሁ። አሁን የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን በአንደኛው ዓመት ላይ የስብሰባው ቢሮ የበላይ ተመልካች ነበር። በሌላኛው ዓመት ግን በዚህ ሥራ ላይ እኔ ተመደብኩ። ዴቪድ ለውጡን በደስታ ተቀብሎ አግዞኛል።
ለ36 ዓመታት በወረዳ ሥራ ላይ ከቆየን በኋላ በ2011 የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤት ላይ አስተማሪ እንድሆን ተመደብኩ። እኔና ራንዲ በሁለት ዓመት ውስጥ 75 የተለያዩ ቦታዎች ለማደር ተገድደናል። መሥዋዕትነቱ ግን የሚክስ ነው፤ በሳምንቱ መጨረሻ ትምህርት ቤቱ ሲጠናቀቅ ሽማግሌዎቹ በአድናቆት ስሜት ይሞላሉ፤ ምክንያቱም የበላይ አካሉ ለሽማግሌዎች መንፈሳዊነት ምን ያህል እንደሚጨነቅ ይረዳሉ።
ከጊዜ በኋላ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ላይም አስተምሬያለሁ። መጀመሪያ ላይ ተማሪዎቹ ፕሮግራማቸው ምን ያህል የተጣበበ እንደሆነ ሲያስቡት ውጥረት ውስጥ ይገባሉ። ቀን ላይ ለሰባት ሰዓት ገደማ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ይማራሉ፤ ምሽት ላይ የቤት ሥራ ሲሠሩ ሦስት ሰዓት ያሳልፋሉ፤ በየሳምንቱ ደግሞ አራት ወይም አምስት ክፍል ሊሰጣቸው ይችላል። ስለዚህ እኔና ሌላኛው አስተማሪ ይህ ሊሳካ የሚችለው በይሖዋ እርዳታ ብቻ እንደሆነ እንነግራቸዋለን። ተማሪዎቹ በይሖዋ እርዳታ ካሰቡት በላይ ማሳካት እንደቻሉ ሲያውቁ የሚሰማቸው የግርምት ስሜት ሁሌም ትዝ ይለኛል።
በግል ትኩረት ሰጥቶ መርዳት በረከቱ ዘላለማዊ ነው
እናቴ ሌሎችን ትኩረት ሰጥታ የምትረዳ ሴት ነበረች፤ ይህ ባሕርይዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቿ እድገት እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። አባቴ እንኳ ለእውነት ያለው አቋም የተቀየረው በዚህ የተነሳ ነው። እናቴ ካረፈች ከሦስት ቀናት በኋላ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ የሕዝብ ንግግር ላይ ተገኝቶ አስገረመን፤ ከዚያ በኋላ ለ26 ዓመታት በስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ቀጥሏል። አባቴ ባይጠመቅም በየሳምንቱ ስብሰባዎች ላይ ሁልጊዜ ቀድሞ እንደሚደርስ ሽማግሌዎቹ ነግረውኛል።
እናቴ በእኛ በልጆቿ ላይም የማይፋቅ አሻራ ትታ አልፋለች። ሦስቱም እህቶቼ ከነባሎቻቸው ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው። ሁለቱ እህቶቼ የሚያገለግሉት ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነው፤ አንደኛዋ ፖርቱጋል፣ ሌላኛዋ ደግሞ ሄይቲ።
እኔና ራንዲ በአሁኑ ወቅት ሃሚልተን፣ ኦንታሪዮ ውስጥ በልዩ አቅኚነት እያገለገልን ነው። የወረዳ ሥራ ላይ በነበርንበት ወቅት ወንድሞችና እህቶች ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉና ጥናት ሲመሩ አብረናቸው መገኘት ያስደስተን ነበር። አሁን ደግሞ የራሳችንን ጥናቶች መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ እያጣጣምን ነው። በአዲሱ ጉባኤያችን ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋርም ተቀራርበናል፤ ይሖዋ በክፉም ሆነ በደጉ እንዴት እንደሚደግፋቸው ማየታችን በጣም ያበረታታናል።
መለስ ብለን ስናስበው ብዙዎች በግል ትኩረት ሰጥተው ላደረጉልን እርዳታ በጣም አመስጋኝ ነን። እኛም ለሌሎች “ልባዊ አሳቢነት” ለማሳየት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል። (2 ቆሮ. 7:6, 7) በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙበት አበረታተናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የምናውቀው ቤተሰብ አለ፤ ሚስትየው፣ ወንዱ ልጅና ሴቷ ልጅ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ናቸው። ባልየውን “አቅኚ ስለመሆን አስበህ ታውቃለህ?” ብዬ ጠየቅሁት። “እኔማ ሦስት አቅኚዎችን እየደገፍኩ ነው” አለኝ። እኔም “ከይሖዋ በተሻለ ልትደግፋቸው እንደምትችል ይሰማሃል?” አልኩት። ልክ እንደ እነሱ የአቅኚነትን ደስታ እንዲቀምስ አበረታታሁት። በስድስት ወር ውስጥ አቅኚ ሆነ።
የእኔና የራንዲ ምኞት የይሖዋን “ድንቅ ሥራዎች . . . ለቀጣዩ ትውልድ” መንገራችንን መቀጠል ነው፤ እንደ እኛ በይሖዋ አገልግሎት እጅግ እንዲደሰቱ እንመኝላቸዋለን።—መዝ. 71:17, 18
a አሁን የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካች ተብሎ ይጠራል።
b የሊዮንስ ክሪፖ የሕይወት ታሪክ በየካቲት 2020 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 26-30 ላይ ወጥቷል።