በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 29

ለታላቁ መከራ ተዘጋጅተሃል?

ለታላቁ መከራ ተዘጋጅተሃል?

“ዝግጁ ሁኑ።”—ማቴ. 24:44

መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

ማስተዋወቂያ a

1. ለአደጋ መዘጋጀት የጥበብ እርምጃ የሆነው ለምንድን ነው?

 መዘጋጀት ሕይወት ያድናል። ለምሳሌ አደጋ ሲከሰት ቀድሞ የተዘጋጁ ሰዎች የመትረፍ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው፤ ከራሳቸውም አልፈው ሌሎችን ይረዳሉ። በአውሮፓ የሚገኝ አንድ የእርዳታ ድርጅት እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ ዝግጅት የሕይወትና የሞት ያህል ለውጥ ያመጣል።”

2. ለታላቁ መከራ መዘጋጀት ያለብን ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 24:44)

2 ‘ታላቁ መከራ’ የሚጀምረው በድንገት ነው። (ማቴ. 24:21) ከሌሎቹ አደጋዎች በተለየ ግን ታላቁ መከራ ድንገተኛ የሚሆነው ለሁሉም ሰው አይደለም። ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ተከታዮቹን ለዚህ ቀን እንዲዘጋጁ አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 24:44ን አንብብ።) ዝግጁ ከሆንን ይህን የመከራ ጊዜ ማለፍ ያን ያህል አይከብደንም፤ እንዲያውም ከራሳችን አልፈን ሌሎችን ለመርዳት እንበቃለን።—ሉቃስ 21:36

3. ጽናት፣ ርኅራኄና ፍቅር ለታላቁ መከራ እንድንዘጋጅ የሚረዱን እንዴት ነው?

3 ለታላቁ መከራ ለመዘጋጀት የሚረዱን ሦስት ባሕርያት አሉ። ለምሳሌ፣ አምርረው ለሚቃወሙን ሰዎች ኃይለኛ የፍርድ መልእክት እንድናውጅ እንጠየቅ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ምን እናደርጋለን? (ራእይ 16:21) ይሖዋ እንደሚጠብቀን ተማምነን ትእዛዙን መፈጸም ጽናት ይጠይቃል። ወንድሞቻችን ንብረታቸውን ቢያጡ አልፎም ባዷቸውን ቢቀሩ ምን እናደርጋለን? (ዕን. 3:17, 18) ርኅራኄ በችግራቸው እንድንደርስላቸው ያነሳሳናል። ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በሰነዘሩት ጥቃት የተነሳ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በአንድ ቦታ እፍግፍግ ብለን ለመኖር ብንገደድስ? (ሕዝ. 38:10-12) ያንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ለእነሱ ጥልቅ ፍቅር ሊኖረን ይገባል።

4. መጽሐፍ ቅዱስ ጽናት፣ ርኅራኄና ፍቅር ማዳበራችንን መቀጠል እንዳለብን የሚያሳየው እንዴት ነው?

4 የአምላክ ቃል ጽናት፣ ርኅራኄና ፍቅር ማዳበራችንን እንድንቀጥል ያበረታታናል። ሉቃስ 21:19 “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” ይላል። ቆላስይስ 3:12 “ርኅራኄን . . . ልበሱ” ይላል። አንደኛ ተሰሎንቄ 4:9, 10 ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ ራሳችሁ እርስ በርስ እንድትዋደዱ ከአምላክ [ተምራችኋል]። . . . ሆኖም ወንድሞች፣ ይህን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ እናሳስባችኋለን።” እነዚህ ሦስቱም ምክሮች የተሰጡት ቀድሞውንም ቢሆን ጽናት፣ ርኅራኄና ፍቅር ያሳዩ ለነበሩ ደቀ መዛሙርት ነው። ሆኖም እነዚህን ባሕርያት ማዳበራቸውን መቀጠል ያስፈልጋቸው ነበር፤ እኛም እንደዛው። ለዚህ እንዲያግዘን የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እያንዳንዱን ባሕርይ እንዴት እንዳሳዩ እንመልከት። ከዚያም የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን፤ ይህም ለታላቁ መከራ ያዘጋጀናል።

ጽናት አዳብር

5. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ፈተናዎችን በጽናት ለመወጣት የረዳቸው ምንድን ነው?

5 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች መጽናት ያስፈልጋቸው ነበር። (ዕብ. 10:36) በሁሉም ሰው ላይ ከሚደርሰው ችግር በተጨማሪ ሌላም ፈተና ነበረባቸው። ብዙዎቹ ስደት ደርሶባቸዋል፤ ከአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችና ከሮም ባለሥልጣናት በተጨማሪ የገዛ ቤተሰቦቻቸው ይቃወሟቸው ነበር። (ማቴ. 10:21) በጉባኤው ውስጥ ደግሞ ከሃዲዎችንና የእነሱ ከፋፋይ ትምህርት የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መፋለም ነበረባቸው። (ሥራ 20:29, 30) ያም ቢሆን እነዚያ ክርስቲያኖች ይህን ሁሉ በጽናት ተቋቁመዋል። (ራእይ 2:3) ለመጽናት የረዳቸው ምንድን ነው? እንደ ኢዮብ ባሉ የጽናት ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላቸው ጠቅሟቸዋል። (ያዕ. 5:10, 11) ኃይል ለማግኘት ጸልየዋል። (ሥራ 4:29-31) ጽናታቸው ያስገኘው ግሩም ውጤት ላይ ማተኮራቸውም ረድቷቸዋል።—ሥራ 5:41

6. ሜሪታ ተቃውሞን በጽናት ለመቋቋም ከረዳት ነገር ምን ትማራለህ?

6 እኛም በአምላክ ቃልና በጽሑፎቻችን ላይ ስለተጠቀሱ የጽናት ምሳሌዎች አዘውትረን የምናጠናና የምናሰላስል ከሆነ መጽናት እንችላለን። በአልባኒያ የምትኖረው ሜሪታ እንዲህ ታደርግ ነበር፤ ይህም ከቤተሰቧ የገጠማትን ከባድ ተቃውሞ ለመቋቋም ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ኢዮብ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሳጠና ልቤ በጥልቅ ተነካ። ኢዮብ በጣም ተሠቃይቷል፤ ፈተናውን የሚያደርስበት ማን እንደሆነ ባያውቅም ‘እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!’ ብሏል። (ኢዮብ 27:5) ኢዮብ ከደረሰበት ነገር አንጻር ሲታይ ‘እኔ መች ተነካሁ?’ ብዬ አሰብኩ። ቢያንስ እኔ ከፈተናው በስተ ጀርባ ማን እንዳለ አውቃለሁ።”

7. ለጊዜው ከባድ መከራ ባያጋጥመንም ከአሁኑ ምን ማድረግን መማር ይኖርብናል?

7 በተጨማሪም ወደ ይሖዋ አዘውትረን በመጸለይና የልባችንን ጭንቀት በማፍሰስ ጽናት ማዳበር እንችላለን። (ፊልጵ. 4:6፤ 1 ተሰ. 5:17) እርግጥ በአሁኑ ወቅት ከባድ መከራ አልደረሰብህ ይሆናል። ያም ቢሆን ስትበሳጭ፣ ግራ ስትጋባ ወይም ነገሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ሲሰማህ የይሖዋን መመሪያ የመፈለግ ልማድ አለህ? ዛሬ በዕለት ተዕለት የሕይወት ውጣ ውረድ የይሖዋን እርዳታ አዘውትረህ የምትጠይቅ ከሆነ ወደፊት ከበድ ያለ ነገር ሲያጋጥምህ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትልም። ይሖዋ እሱ የተሻለ ነው ብሎ በሚያስበው ጊዜና መንገድ እንደሚረዳህ ያለህ እምነትም ጠንካራ ይሆናል።—መዝ. 27:1, 3

ጽናት

በጽናት የምንወጣው እያንዳንዱ ፈተና ለቀጣዩ ያዘጋጀናል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8. ዛሬ መጽናታችን ወደፊት ለሚያጋጥመን መከራ እንደሚያዘጋጀን የሚራ ተሞክሮ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ያዕቆብ 1:2-4) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት የምንወጣ ከሆነ መጪውን ታላቅ መከራ በጽናት የማለፍ አጋጣሚያችን ሰፊ ይሆናል። (ሮም 5:3) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ብዙ ወንድሞቻችን ከራሳቸው ተሞክሮ እንደተረዱት በጽናት የተወጡት እያንዳንዱ ፈተና ለቀጣዩ መከራ አዘጋጅቷቸዋል። በፈተና መጽናት ማንነታቸውን እንደሚያጠራው አስተውለዋል። ይሖዋ እነሱን ለመርዳት ፍላጎቱ እንዳለውና በችግራቸው ፈጥኖ እንደሚደርስላቸው ያላቸው እምነት ተጠናክሯል። ይህ እምነታቸው ደግሞ ቀጣዩን ፈተና በጽናት ለመወጣት ረድቷቸዋል። (ያዕቆብ 1:2-4ን አንብብ።) በአልባኒያ በአቅኚነት የምታገለግለውን የሚራን ምሳሌ እንመልከት፤ የዛሬ መከራዋን በጽናት እንድትቋቋም እየረዳት ያለው የቀድሞ ጽናቷ እንደሆነ ይሰማታል። እርግጥ ነው፣ እሷ ራሷም በሐቀኝነት እንደተናገረችው የእሷን ያህል ፈተና የተደራረበበት እንደሌለ የሚሰማት ጊዜ አለ። ከዚያ ግን ይሖዋ ባለፉት 20 ዓመታት እሷን ለመርዳት ስላደረጋቸው ነገሮች ማሰብ ትጀምራለች፤ ቀጥላም ራሷን እንዲህ ትለዋለች፦ ‘ታማኝ ሁኚ። በይሖዋ እርዳታ ያለፍሻቸውን እነዚያን ሁሉ ዓመታትና በድል የተወጣሻቸውን እነዚያን ሁሉ ፍልሚያዎች ከንቱ አታድርጊ።’ አንተም ይሖዋ ከዚህ ቀደም ለመጽናት የረዳህ እንዴት እንደሆነ ማሰላሰል ትችላለህ። ይህም እያንዳንዱን ፈተና በጽናት ስትወጣ ይሖዋ እንደሚያስተውልና ለዚህም እንደሚክስህ እርግጠኛ እንድትሆን ይረዳሃል። (ማቴ. 5:10-12) ታላቁ መከራ ሲጀምር ደግሞ አስቀድመህ ጽናትን ስለተማርክ ፈተናውን ለማለፍ ቁርጠኝነት ይኖርሃል።

ርኅራኄ አሳይ

9. የአንጾኪያ ክርስቲያኖች ርኅራኄ ያሳዩት እንዴት ነው?

9 በይሁዳ ታላቅ ረሃብ ተከስቶ ክርስቲያኖች በተቸገሩበት ወቅት የተፈጸመውን እንመልከት። በሶርያዋ አንጾኪያ ያሉ ክርስቲያኖች ስለ ረሃቡ ሲሰሙ በይሁዳ ላሉ ወንድሞቻቸው አዝነው መሆን አለበት። ሆኖም ርኅራኄያቸው ከስሜት ባለፈ ለተግባር አነሳስቷቸዋል። “እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ።” (ሥራ 11:27-30) በረሃብ የተጎዱት ወንድሞቻቸው የሚኖሩት ርቀው ቢሆንም የአንጾኪያ ክርስቲያኖች እነሱን ለመርዳት ቆርጠው ነበር።—1 ዮሐንስ 3:17, 18

ርኅራኄ

የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ርኅራኄ ለማሳየት አጋጣሚ እናገኛለን (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. የእምነት ባልንጀሮቻችን አደጋ ሲደርስባቸው ርኅራኄ ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 እኛም የእምነት አጋሮቻችን በአደጋ እንደተጎዱ ስንሰማ ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። ቶሎ ልንደርስላቸው እንፈልጋለን፤ ለምሳሌ በእርዳታ እንቅስቃሴው መካፈል እንችል እንደሆነ ሽማግሌዎችን መጠየቅ፣ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ ወይም በአደጋው ለተጎዱት መጸለይ እንችላለን። b (ምሳሌ 17:17) በ2020 የተከናወነውን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጎዱትን ለመርዳት በዓለም ዙሪያ ከ950 በላይ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ነበር። በእነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞች ልባዊ ምስጋናችን ይገባቸዋል። ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ባላቸው ርኅራኄ ተነሳስተው ብዙ ሥራ አከናውነዋል። የእርዳታ ቁሳቁሶችን አከፋፍለዋል፤ መንፈሳዊ እገዛ ሰጥተዋል፤ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የአምልኮ ቦታዎችንና መኖሪያ ቤቶችን አድሰዋል ወይም እንደገና ገንብተዋል።—ከ2 ቆሮንቶስ 8:1-4 ጋር አወዳድር።

11. የምናሳየው ርኅራኄ በሰማይ ያለውን አባታችንን የሚያስከብረው እንዴት ነው?

11 በአደጋ ጊዜ ርኅራኄ ስናሳይ ሌሎችም የምንከፍለውን መሥዋዕትነት ማስተዋላቸው አይቀርም። ለምሳሌ በ2019 ዶሪያን የተባለው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በባሃማስ የሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ አውድሞ ነበር። ወንድሞች አዳራሹን መልሰው በሚገነቡበት ወቅት የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የሥራ ተቋራጭ በአንድ ሥራ እንዲያግዛቸው ስለፈለጉ ክፍያውን ጠየቁት። እንዲህ አላቸው፦ “በመሣሪያም፣ በጉልበትም፣ በቁሳቁስም . . . በራሴ ወጪ ማገዝ እፈልጋለሁ። . . . ለድርጅታችሁ አንድ ነገር ማድረግ ስለምፈልግ ነው። ለጓደኞቻችሁ የምታሳዩት ርኅራኄ በጣም አስደንቆኛል።” በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ አያውቁም። የይሖዋ ምሥክሮችን ግን ያውቃሉ፤ የሚያከናውኑትን ሥራም ያያሉ። በርኅራኄ ተነሳስተን የምናከናውነው ሥራ “ምሕረቱ ብዙ” ወደሆነው አምላክ ሰዎችን እንደሚስብ ማወቅ ታላቅ መብት አይደል!—ኤፌ. 2:4

12. በአሁኑ ጊዜ ርኅራኄ ማዳበራችን ለታላቁ መከራ የሚያዘጋጀን እንዴት ነው? (ራእይ 13:16, 17)

12 በታላቁ መከራ ወቅት ርኅራኄ ማሳየት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቁመው አሁንም ሆነ በታላቁ መከራ ወቅት ለፖለቲካው ሥርዓት ድጋፍ የማይሰጡ ሰዎች የሚቸገሩበት ጊዜ ይኖራል። (ራእይ 13:16, 17ን አንብብ።) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ ለማግኘት እገዛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ ለፍርድ ሲመጣ ርኅራኄ ስናሳይ እንዲያገኘን እንፈልጋለን፤ ምኞታችን ‘መንግሥቱን እንዲወርሱ’ ከሚጋብዛቸው ሰዎች መካከል መሆን ነው።—ማቴ. 25:34-40

ፍቅርህን አሳድግ

13. በሮም 15:7 መሠረት የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የፍቅር ሰንሰለታቸውን ያጠናከሩት እንዴት ነው?

13 ፍቅር የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዋነኛ መለያ ነበር። ሆኖም ፍቅር ማሳየት ቀላል ሆኖላቸው ነበር? በሮም ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሰዎች ምን ያህል የተለያዩ እንደነበሩ ለማሰብ ሞክር። አንዳንዶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ የተማሩ አይሁዳውያን ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ከዚህ የተለየ አስተዳደግ ያላቸው አሕዛብ ናቸው። አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ባሪያዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ሌሎቹ ደግሞ ነፃ ሰዎች ናቸው፤ እንዲያውም ባሪያ አሳዳሪዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ልዩነታቸው ጋሬጣ ሳይሆንባቸው ከልብ መዋደድ የቻሉት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ” ብሏቸዋል። (ሮም 15:7ን አንብብ።) ምን ማለቱ ነበር? “ተቀበሉ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አንድን ሰው ማስተናገድ፣ ወደ ቤት አሊያም ወደ ጓደኛሞች ቡድን እንዲገባ በደግነት መጋበዝ ማለትም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ጳውሎስ፣ የኮበለለውን ባሪያውን አናሲሞስን እንዲቀበለው ለፊልሞና ሲነግረው “በደግነት ተቀበለው” ብሎታል። (ፊልሞና 17) ጵርስቅላና አቂላም ስለ ክርስትና በቂ ግንዛቤ ያልነበረውን አጵሎስን “ይዘውት በመሄድ” በደግነት ተቀብለውታል። (ሥራ 18:26) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ልዩነታቸው እንዲከፋፍላቸው ከመፍቀድ ይልቅ አንዳቸው ሌላውን ተቀብለዋል።

ፍቅር

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያሳዩን ፍቅር ያስፈልገናል (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

14. አና እና ባለቤቷ ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

14 እኛም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጓደኞቻችን እንዲሆኑ በመፍቀድ ፍቅር ማሳየት እንችላለን። እነሱም ይህን ሲያዩ በአብዛኛው ፍቅር ለማሳየት ይነሳሳሉ። (2 ቆሮ. 6:11-13) የአና እና የባለቤቷን ምሳሌ እንመልከት። በምዕራብ አፍሪካ አዲስ የሚስዮናዊ ምድብ ተሰጣቸው፤ ከሄዱ ብዙም ሳይቆይ ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጀመረ። ከወቅቱ አንጻር የጉባኤያቸውን ወንድሞችና እህቶች በአካል ማግኘት አልቻሉም። ታዲያ ፍቅር ለማሳየት ምን አደረጉ? በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተጠቅመው ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ለመገናኘት ጥረት አደረጉ፤ ከእነሱ ጋር ይበልጥ መተዋወቅ እንደሚፈልጉም ነገሯቸው። የጉባኤያቸው ወንድሞች በዚህ ስለተደሰቱ አዘውትረው ይደውሉላቸውና መልእክት ይልኩላቸው ጀመር። እነዚህ ባልና ሚስት ወንድሞቻቸውን ለመተዋወቅ ይህን ያህል ጥረት ያደረጉት ለምንድን ነው? አና እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞች በደጉም ሆነ በክፉው ጊዜ ለእኔና ለቤተሰቤ ያሳዩን ፍቅር ከልቤና ከአእምሮዬ አይፋቅም። እኔም ፍቅር እንዳሳይ የሚያነሳሳኝ ይህ ነው።”

15. ሁሉንም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በመውደድ ረገድ ከቫኔሳ ምን እንማራለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 በብዙዎቹ ጉባኤዎች ውስጥ የተለያየ አስተዳደግና ባሕርይ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ይገኛሉ። ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ በማተኮር ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። ቫኔሳ የተባለች በኒው ዚላንድ የምትኖር እህት ምን እንዳደረገች እንመልከት፤ በጉባኤዋ ካሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጋር መግባባት ተቸግራ ነበር። በኋላ ግን ብዙም የማይጥማት ባሕርይ ካላቸው ክርስቲያኖች ከመራቅ ይልቅ ከእነሱ ጋር ይበልጥ ጊዜ ለማሳለፍ ወሰነች። ይህን ማድረጓ ይሖዋ ለምን እንደሚወዳቸው እንድታስተውል ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ከሆነ ወዲህ አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው የተለያየ ባሕርይ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር ነው። አሁን ከእነሱ ጋር መግባባት አይቸግረኝም። እንዲያውም ልዩነታችንን ወድጄዋለሁ። ይሖዋም እንደሚወደው ይሰማኛል፤ ምክንያቱም እሱን እንዲያመልኩ የፈቀደላቸው ሰዎች ልዩ ልዩ ናቸው።” ሌሎችን በይሖዋ ዓይን በማየት እንደምንወዳቸው እናስመሠክራለን።—2 ቆሮ. 8:24

በታላቁ መከራ ወቅት፣ ይሖዋ ቃል የገባውን ጥበቃ የምናገኘው ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነት ካለን ነው (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. በታላቁ መከራ ወቅት ፍቅር በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 በታላቁ መከራ ወቅት ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነገር ይሆናል። መከራው ሲጀምር ጥበቃ ማግኘት የምንችለው የት ነው? ይሖዋ በጥንቷ ባቢሎን ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ለሕዝቡ ምን መመሪያ እንደሰጠ እንመልከት፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ከኋላህ ዝጋ። ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።” (ኢሳ. 26:20) እነዚህ ቃላት ታላቁን መከራ ለምንጋፈጥ ክርስቲያኖችም የሚሠሩ ይመስላል። “ውስጠኛው ክፍል” የተባለው ጉባኤዎቻችንን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ ቃል የገባውን ጥበቃ የምናገኘው ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነት ካለን ነው። እንግዲያው ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መቻል ብቻ በቂ አይደለም፤ ከአሁኑ ከልብ ለመዋደድም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው!

ከአሁኑ ተዘጋጅ

17. ከአሁኑ ከተዘጋጀን በታላቁ መከራ ወቅት ምን ማድረግ እንችላለን?

17 “ታላቁ የይሖዋ ቀን” ለመላው የሰው ዘር አስጨናቂ ጊዜ ይሆናል። (ሶፎ. 1:14, 15) የይሖዋ አገልጋዮችም ፈተናዎች እንደሚያጋጥሟቸው ግልጽ ነው። ከአሁኑ ከተዘጋጀን ግን ያን ጊዜ አንረበሽም፤ እንዲያውም ሌሎችን ለመርዳት እንበቃለን። ምንም ዓይነት ፈተና ቢመጣ እንጸናለን። የእምነት ባልንጀሮቻችን ሲቸገሩ ርኅራኄ እናሳያለን፤ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። ደግሞም ከአሁኑ ፍቅርን ካዳበርን ያን ጊዜ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ተቀራርበን መኖር አይቸግረንም። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል፤ ያን ጊዜ አደጋና መከራ ታሪክ ይሆናሉ!—ኢሳ. 65:17

መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!

a ታላቁ መከራ በቅርቡ ይጀምራል። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ ለማይታወቀው የመከራ ጊዜ እንድንዘጋጅ ከሚረዱን ባሕርያት መካከል ጽናት፣ ርኅራኄና ፍቅር ይገኙበታል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እነዚህን ባሕርያት ያዳበሩት እንዴት ነው? እኛስ እነዚህን ባሕርያት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህ ባሕርያት ለታላቁ መከራ ለመዘጋጀት የሚረዱንስ እንዴት ነው?

b በእርዳታ እንቅስቃሴ ማገዝ የሚፈልጉ ክርስቲያኖች በቅድሚያ የአካባቢ የንድፍ/ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ማመልከቻ (DC-50) ወይም የፈቃደኛ ሠራተኞች ፕሮግራም ማመልከቻ (A-19) መሙላት ያስፈልጋቸዋል፤ ከዚያም እስኪጋበዙ ይጠብቃሉ።