በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ለአንድ ዓመት ሰላምና ደስታ እንዲሰጠኝ ጸለይኩ

ለአንድ ዓመት ሰላምና ደስታ እንዲሰጠኝ ጸለይኩ
  • የትውልድ ዘመን፦ 1971

  • የትውልድ አገር፦ ፈረንሳይ

  • የኋላ ታሪክ፦ ዓመፀኛ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር የነበረው እንዲሁም ዕፅ ይወስድ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ቤተሰቦቼ በሰሜን ምሥራቅ ፈረንሳይ በምትገኝ ቴላንኮር በተባለች መንደር ይኖሩ ነበር። አባቴ ፈረንሳዊ ሲሆን እናቴ ጣሊያናዊ ናት። ስምንት ዓመት ሲሆነኝ ወደ ሮም፣ ጣሊያን የሄድን ሲሆን በዚያም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሠራተኞች በሚኖሩበት ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ስፍራ መኖር ጀመርን። በዚህ ቦታ ስንኖር ቤተሰባችን ሰላም አልነበረውም። ወላጆቼ፣ በነበረባቸው የኢኮኖሚ ችግር የተነሳ በጣም ይጨቃጨቁ ነበር።

አሥራ አምስት ዓመት ሲሆነኝ እናቴ፣ ከቤት ወጥቼ ጓደኞች እንዳፈራ አበረታታችኝ። በመሆኑም ከቤት ርቄ ረጅም ጊዜ ማሳለፍ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ መጥፎ ጓደኞችን አፈራሁ። አንድ ቀን፣ የሆነ ሰው መጥቶ ሊግባባኝ ሞከረ። ከዚያም ዕፅ እንድወስድ ጋበዘኝ፤ እኔም ትልቅ ሰው ሆኜ መታየት ስለፈለግሁ ግብዣውን ተቀበልኩ። ብዙም ሳይቆይ ዕፅ መውሰድና ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር መኖር ጀመርኩ። በተደጋጋሚ ጊዜያት ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብኛል። ሕይወት ትርጉም አልባ ስለሆነብኝ ብኖርም ሆነ ብሞት ምንም ግድ አልነበረኝም። ብቸኝነት በጣም ያጠቃኝ ነበር። በ16 ዓመቴ፣ አንድ ጠርሙስ ሙሉ ውስኪ ጠጥቼ ሐይቅ ውስጥ ዘልዬ በመግባት ራሴን ለማጥፋት ሞከርኩ። በዚህም የተነሳ ለሦስት ቀናት ራሴን ስቼ ቆየሁ።

በኋላ ላይ ለሕይወት ጥሩ አመለካከት ማዳበር ጀመርኩ፤ ሆኖም ዓመፀኛና መጥፎ ሰው ሆንኩ። ሰዎች ከእኔ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ በመጠየቅ ወደ ቤታቸው እንዲወስዱኝ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በዕፅ አደነዝዛቸውና ያላቸውን ውድ ነገር ሁሉ እዘርፋለሁ። ወንጀል የሚፈጽሙ ቡድኖች፣ በመላው ጣሊያን ዕፅ እንዳዘዋውርላቸው ያደርጉኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ፖሊሶች ያሳድዱኝ ነበር። የተፈጠርኩበት ምክንያት እንዳለ ቢሰማኝም ሕይወቴ ትርጉም የለሽና ከእኔ ቁጥጥር ውጭ ሆነ። አምላክ፣ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ሰላምና ደስታ እንዲሰጠኝ ጸለይኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ሃያ አራት ዓመት ሲሆነኝ ወደ እንግሊዝ ሄጄ ለመኖር ወሰንኩ። ከዕፅ አዘዋዋሪዎች ጋር በነበረኝ ግንኙነት የተነሳ ሕይወቴ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ወደ እንግሊዝ ከመሄዴ በፊት እናቴን ለመጠየቅ ሄድኩ፤ በዚያም አኑንሲያቶ ሉጋራ የተባለ ሰው ለእናቴ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግራት አይቼ በጣም ተገረምኩ። * ይህ ሰው በወንጀለኛነቱ የሚታወቅ ሰው ስለነበር ፈራሁ፤ ከዚያም ምን ሊሠራ እንደመጣ ጠየቅኩት። እሱም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በሕይወቱ ውስጥ ያደረገውን ትልቅ ለውጥ የነገረኝ ከመሆኑም ሌላ ወደ እንግሊዝ ስሄድ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዳነጋግር ቃል እንድገባለት ጠየቀኝ። እኔም ይህን ለማድረግ ተስማማሁ። እዚያ ከደረስኩ በኋላ ግን ወዲያውኑ ቀድሞ የነበረኝ ዓይነት ሕይወት መምራት ጀመርኩ።

አንድ ቀን፣ ለንደን ውስጥ በሚገኝ ሕዝብ የሚበዛበት መንገድ ላይ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ለሰዎች ሲሰጥ አየሁ። ለአኑንሲያቶ የገባሁትን ቃል በማስታወስ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስተምረኝ ይህን የይሖዋ ምሥክር ጠየቅኩት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩት ነገር በጣም አስደነቀኝ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንደኛ ዮሐንስ 1:9 ላይ የሚገኘው “ኃጢአታችንን የምንናዘዝ ከሆነ እሱ ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፤ እንዲሁም . . . ያነጻናል” የሚለው ሐሳብ ልቤን ነካው። ይህ ጥቅስ በሕይወቴ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ምክንያቱም ከነበረኝ ሕይወት የተነሳ በጣም እንደቆሸሽኩ ይሰማኝ ነበር። ወዲያውኑ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች በፍቅር ተቀበሉኝ። በመካከላቸው ያለው ቅርርብ በሕይወቴ እፈልገው የነበረው ነገር ነበር፤ በመሆኑም ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ የሆነው የዚህ ጉባኤ አባል መሆን ፈለግኩ።

ዕፅ መውሰዴንና ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት መምራቴን ማቆም ብዙ ባይከብደኝም ባሕሪዬን ማሻሻል ግን ቀላል አልሆነልኝም። ለሰዎች አክብሮት እና አሳቢነት ማሳየት እንዳለብኝ አስተዋልኩ። አሁንም ድረስ አንዳንድ መጥፎ ባሕርያትን ለማስወገድ ጥረት እያደረግኩ ነው። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ችያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩ ከስድስት ወር በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ይህ የሆነው በ1997 ነበር።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ከተጠመቅኩ በኋላ ባርብራ ከተባለች አንዲት ወጣት ጋር ትዳር መሠረትኩ፤ እሷም የይሖዋ ምሥክር የሆነችው በቅርቡ ነበር። ከቀድሞ ጓደኞቼ አንዱ ምን ያህል እንደተለወጥኩ ሲያይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከጊዜ በኋላ እሱም ሆነ እህቱ የይሖዋ ምሥክር ሆኑ። ከዚያም ከ80 ዓመት በላይ የሆኑት የሴት አያቴ እህት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩ ሲሆን ከመሞታቸው በፊት ተጠምቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በአንድ ጉባኤ ውስጥ በሽማግሌነት እያገለገልኩ ሲሆን እኔም ሆንኩ ባለቤቴ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በመሆን ለንደን ውስጥ ለሚኖሩ ጣሊያንኛ ተናጋሪ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምራለን። አንዳንድ ጊዜ ቀድሞ ያሳለፍኩትን ሕይወት እያሰብኩ የምተክዝበት ወቅት አለ፤ ሆኖም ባርብራ ትልቅ የብርታት ምንጭ ሆናልኛለች። ሁልጊዜ እመኘው የነበረው ዓይነት የተረጋጋ የቤተሰብ ሕይወት አለኝ፤ እንዲሁም ምንጊዜም እፈልገው የነበረ ዓይነት አባት ማለትም የሚወደኝ አባት አግኝቼያለሁ። አምላክን የጠየቅኩት ቢያንስ ለአንድ ዓመት ሰላምና ደስታ እንዲሰጠኝ ነበር፤ እሱ ግን ከዚያ የበለጠ ነገር አድርጎልኛል!

ሁልጊዜ እመኘው የነበረው ዓይነት የተረጋጋ የቤተሰብ ሕይወት አለኝ፤ እንዲሁም ምንጊዜም እፈልገው የነበረ ዓይነት አባት ማለትም የሚወደኝ አባት አግኝቼያለሁ

^ አን.10 በሐምሌ 1, 2014 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-9 ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል—መሣሪያዬ ምንጊዜም ከእኔ አይለይም ነበር” በሚል ርዕስ የወጣውን የአኑንሲያቶ ሉጋራን የሕይወት ታሪክ አንብብ።