በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ምን ይላል?

ክፉ መላእክት አሉ?

ክፉ መላእክት አሉ?

አዎ፣ ክፉ መላእክት አሉ። የመጡት ከየት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት አምላክ ለመላእክት የመምረጥ ነፃነት እንደሰጣቸው ማስታወስ ያስፈልገናል። የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማለትም አዳምና ሔዋን ከተፈጠሩ ብዙም ሳይቆይ አንድ ፍጹም መንፈሳዊ ፍጡር የመምረጥ ነፃነቱን አላግባብ በመጠቀም በምድር ላይ ዓመፅ እንዲነሳ አደረገ። ይህ መልአክ አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ እንዲያምፁ አደረጋቸው። (ዘፍጥረት 3:1-7፤ ራእይ 12:9) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ከማመፁ በፊት ስለነበረው ስምም ሆነ ሥልጣን አይናገርም። ሆኖም ካመፀ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰይጣን እና ዲያብሎስ ተብሎ ተጠርቷል፤ ሰይጣን ማለት “ተቃዋሚ፣” ዲያብሎስ ማለት ደግሞ “ስም አጥፊ” በመሆኑ እንዲህ ያለ ስያሜ የተሰጠው መሆኑ ተገቢ ነው።—ማቴዎስ 4:8-11

የሚያሳዝነው ግን በአምላክ ላይ ዓመፅ የተነሳው በዚያ ጊዜ ብቻ አልነበረም። በኖኅ ዘመን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ መላእክት በአምላክ ሰማያዊ ቤተሰብ ውስጥ የነበራቸውን ‘የመኖሪያ ስፍራ ትተዋል።’ እነዚህ መላእክት ወደ ምድር መጥተው ሥጋዊ አካል በመልበስ በሥነ ምግባር ያዘቀጠ አኗኗር መከተል ጀመሩ፤ ይህ ደግሞ ከተፈጠሩበት ዓላማ ጋር ፈጽሞ የማይስማማ ነበር።—ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:1-4፤ 1 ጴጥሮስ 3:19, 20

ታዲያ እነዚህ ክፉ መላእክት ምን ደረሰባቸው? አምላክ ከምድር ላይ ክፋትን ለማስወገድ ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ሲያመጣ እነዚህ ክፉ መላእክት ሥጋዊ አካላቸውን ጥለው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመለሱ። ይሁን እንጂ አምላክ እነዚህ ዓመፀኛ መላእክት ‘መጀመሪያ ወደነበራቸው ቦታ’ እንዲመለሱ አልፈቀደላቸውም። ከዚህ ይልቅ ወደ እንጦሮጦስ ጥሏቸዋል፤ እንጦሮጦስ እነዚህ ክፉ መላእክት የደረሰባቸውን ከፍተኛ ውርደትና ያሉበትን “ድቅድቅ [መንፈሳዊ] ጨለማ” የሚያመለክት ቃል ነው። (ይሁዳ 6፤ 2 ጴጥሮስ 2:4) እነዚህ አጋንንት “የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን [የሚለዋውጠው]” እና ‘የአጋንንት አለቃ’ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ መሪያቸው እንዲሆን ፈቅደዋል።—ማቴዎስ 12:24፤ 2 ቆሮንቶስ 11:14

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት በ1914 በሰማይ ላይ እንደተቋቋመ ያስተምራል። * ከዚህ ወሳኝ ክንውን በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ የተባረሩ ሲሆን እንቅስቃሴያቸው በምድር አካባቢ ብቻ እንዲወሰን ተደርጓል። በዛሬው ጊዜ ክፋትና የሥነ ምግባር ውድቀት በምድር ላይ በጣም የተስፋፋ መሆኑ በቁጣ የተሞሉት እነዚህ ክፉ መላእክት ይህ ነው የማይባል ጎጂ ተጽዕኖ እያሳደሩ እንዳሉ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው።—ራእይ 12:9-12

ይሁን እንጂ የሥነ ምግባር ውድቀትና ዓመፅ እየተበራከተ መምጣቱ የሰይጣንና አጋንንቱ አስከፊ አገዛዝ ፍጻሜ መቅረቡንም ያረጋግጣል። በቅርቡ እነዚህ ጨካኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ይታገዳሉ። የአምላክ መንግሥት ገነት የሆነችውን ምድር ለ1,000 ዓመታት ከገዛ በኋላ እነዚህ ክፉ መናፍስት የሰው ልጆችን ለመፈተን አንድ አጭርና የመጨረሻ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ከዚያም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጠፋሉ።—ማቴዎስ 25:41፤ ራእይ 20:1-3, 7-10

^ አን.6 የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ተመልከት። መጽሐፉ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።