በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ምን ይላል?

መላእክትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

መላእክትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

መላእክት እነማን እንደሆኑና እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጡ፣ እንዲሁም ሥራቸው ምን እንደሆነ ትክክለኛውን ነገር ማወቅ ትፈልጋለህ? በአምላክ መንፈስ መሪነት ከተጻፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ ስለ መላእክት ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ሊሰጠን የሚችል የለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ምን ይላል?

  • አምላክ መንፈስ እንደሆነ ሁሉ መላእክትም “ሥጋና አጥንት” የሌላቸው በዓይን የማይታዩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው። ታማኝ መላእክት በሰማይ ላይ የሚኖሩ ሲሆን በአምላክ ፊት በቀጥታ የመቅረብ መብት አላቸው።—ሉቃስ 24:39፤ ማቴዎስ 18:10፤ ዮሐንስ 4:24

  • መላእክት፣ አምላክ በምድር ላይ እንዲያከናውኑ የሰጣቸውን ሥራ ለመሥራት ሲሉ ሰው መስለው የተገለጡባቸው ጊዜያት የነበሩ ሲሆን ተልእኳቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የለበሱትን ሥጋዊ አካል ጥለው ወደ ሰማይ ሄደዋል።—መሳፍንት 6:11-23፤ 13:15-20

  • መላእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትና ምንጊዜም ለሰዎች የታዩት በተባዕታይ ፆታ ቢሆንም እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ፆታ የላቸውም። በተጨማሪም አይጋቡም ወይም አይዋለዱም። እንዲሁም ሕፃናት፣ ልጆች ወይም ትላልቅ ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ ሄደው መላእክት አይሆኑም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ መላእክትን መጀመሪያውኑ የፈጠራቸው መልአክ አድርጎ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ “የእውነተኛው አምላክ ልጆች” በማለት የሚጠራቸው ለዚህ ነው።—ኢዮብ 1:6፤ መዝሙር 148:2, 5

  • መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስለ ሰዎችና ስለ መላእክት ልሳን’ የሚናገር መሆኑ፣ መንፈሳዊ አካላትም የሚግባቡበት ቋንቋ እንዳላቸው ያመለክታል። አምላክ ከሰዎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ በመላእክት የተጠቀመ ቢሆንም መላእክትን እንድናመልክ ወይም ወደ እነሱ እንድንጸልይ አይፈልግም።—1 ቆሮንቶስ 13:1፤ ራእይ 22:8, 9

  • መጽሐፍ ቅዱስ እልፍ አእላፋት መላእክት እንዳሉ የሚናገር በመሆኑ የመላእክት ቁጥር በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሊሆን ይችላል። *ዳንኤል 7:10፤ ራእይ 5:11

  • መላእክት ከሰዎች እጅግ የላቀ ኃይልና የማሰብ ችሎታ አላቸው። በተጨማሪም የሰው አእምሮ ሊገምተው በማይችል እጅግ ከፍተኛ ፍጥነት መጓዝ ይችላሉ።—መዝሙር 103:20፤ ዳንኤል 9:20-23

  • መላእክት ከፍተኛ የሆነ ኃይልና የማሰብ ችሎታ ቢኖራቸውም ማድረግ የማይችሏቸው ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ የማያውቋቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ።—ማቴዎስ 24:36፤ 1 ጴጥሮስ 1:12

  • ሁሉም መላእክት የራሳቸው ማንነት፣ መለኮታዊ ባሕርያትና የመምረጥ ነፃነት አላቸው። በመሆኑም እነሱም እንደ ሰዎች ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለማድረግ መምረጥ ይችላሉ። የሚያሳዝነው አንዳንድ መላእክት በአምላክ ላይ ለማመፅ መርጠዋል።—ይሁዳ 6

^ አን.8 አንድ እልፍ 10,000 ነው። አንድ እልፍ ጊዜ አንድ እልፍ ደግሞ 100 ሚሊዮን ነው። ሆኖም የራእይ መጽሐፍ “አእላፋት ጊዜ አእላፋት” (የ1954 ትርጉም) ስለሆኑ መላእክት ይናገራል። ይህም በመቶ ሚሊዮኖች፣ ምናልባትም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት እንዳሉ ይጠቁማል!