የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?
የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተጠብቆ ቆይቷል
ፈተናው፦ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የተደረጉት ጥረቶች ቢከሽፉም አንዳንድ ገልባጮችና ተርጓሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመቀየር ሙከራ አድርገው ነበር። እነዚህ ሰዎች የሚያምኑበትን ነገር በማስተካከል መሠረተ ትምህርታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከማስማማት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን መልእክት ለመቀየር ጥረት አድርገዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦
-
የአምልኮ ቦታዎች፦ በአራተኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መካከል የሳምራውያንን ፔንታቱክ a ያዘጋጁት ሰዎች ከዘፀአት 20:17 በኋላ “በገሪዛን ተራራ ላይ። በዚያም መሠዊያ ትሠራለህ” የሚለውን ሐሳብ ጨምረዋል። ሳምራውያን በዚህ ጥቅስ አማካኝነት “በገሪዛን ተራራ” ላይ ቤተ መቅደስ መሥራታቸው የቅዱሳን መጻሕፍት ድጋፍ ያለው እንዲመስል ለማድረግ ሞክረው ነበር።
-
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት፦ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ በኋላ 300 ዓመታት እንኳ ሳይሞላ፣ የሥላሴ አማኝ የሆነ አንድ ጸሐፊ በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ‘አብ፣ ቃልና መንፈስ ቅዱስ ሦስትም አንድም ናቸው’ የሚሉትን ቃላት ጨምሮ ነበር። ይህ ሐሳብ በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ አልነበረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ብሩስ ሜጽገር እንደገለጹት “ከስድስተኛው መቶ ዘመን ወዲህ ይህ ሐሳብ በጥንታዊው ላቲን እና [በላቲን] ቩልጌት በእጅ በተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ በተደጋጋሚ መገኘት ጀመረ።”
-
የአምላክ ስም፦ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአይሁዳውያንን አጉል እምነት መሠረት በማድረግ የአምላክን ስም ከቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለማውጣት ወሰኑ። በአምላክ ስም ምትክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈጣሪን ብቻ ሳይሆን ሰዎችን፣ ጣዖታትን፣ አልፎ ተርፎም ዲያብሎስን ለማመልከት የተሠራባቸውን እንደ “አምላክ” እና “ጌታ” ያሉትን የማዕረግ ስሞች ተጠቀሙ።—ዮሐንስ 10:34, 35፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4 b
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፈተና ያለፈው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች ግድየለሾች አልፎ ተርፎም አታላዮች ቢሆኑም እንኳ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውና
ጠንቃቃ የሆኑ በርካታ ገልባጮች ነበሩ። ከስድስተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ማሶሬቶች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥ የማሶሬቶች ጽሑፍ ተብለው የሚጠሩትን ቅጂዎች አዘጋጁ። ማሶሬቶች ምንም ዓይነት ስህተት ላለመሥራት ሲሉ ቃላትንና ፊደላትን ይቆጥሩ እንደነበር ይነገራል። ለመገልበጥ በሚጠቀሙበት ቅጂ ላይ ስህተት እንዳለ ከተሰማቸው ይህን በኅዳጉ ላይ ይገልጹ ነበር። ማሶሬቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚቀይር ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም። ፕሮፌሰር ሞሼ ጎሸን ጎትጺን “ማሶሬቶች ቅዱስ ጽሑፉን የሚቀይር ነገር ሆን ብሎ ማድረግን የሚመለከቱት እንደ ከባድ ወንጀል ነበር” በማለት ጽፈዋል።በሁለተኛ ደረጃ፣ በዛሬው ጊዜ ብዛት ያላቸው በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች መገኘታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ስህተት የሆኑ ሐሳቦችን ማስተያየት እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሚጠቀሙበት የላቲን ትርጉም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሆነ ለብዙ መቶ ዓመታት ሲያስተምሩ ኖረዋል። ሆኖም በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የተሳሳተ ሐሳብ አስገብተው ነበር። ይህ ስህተት ከፍተኛ ተቀባይነት ባለው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ውስጥም ጭምር ገብቷል! ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የተገኙት በእጅ የተገለበጡ ሌሎች ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ምን ነገር አሳይተዋል? ብሩስ ሜጽገር “[በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ] የገባው ሐሳብ ከላቲኑ በስተቀር በሁሉም ጥንታዊ ቅጂዎች (ሲሪያክ፣ ኮፕቲክ፣ አርመንኛ፣ ግዕዝ፣ አረብኛ፣ ስላቮኒክ) ውስጥ አይገኝም” በማለት ጽፈዋል። በዚህም የተነሳ ተሻሽለው የወጡ የኪንግ ጄምስ ቨርዥን እትሞችና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች ይህን የተሳሳተ ሐሳብ አውጥተውታል።
ቼስተር ቢቲ P46—በ200 ዓ.ም. ገደማ በፓፒረስ ላይ የተጻፈ አንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ
በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተጠብቆ እንደቆየ ያረጋግጣሉ? የሙት ባሕር ጥቅልሎች በ1947 በተገኙ ጊዜ ምሁራን የዕብራይስጡን የማሶሬቶች ጽሑፍ ከእነሱ አንድ ሺህ ዓመታት ቀደም ብለው ከተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎች ጋር ማስተያየት ቻሉ። ስለ ሙት ባሕር ጥቅልሎች የሚዘግበው ቡድን አባል የሆነ አንድ ሰው እንደገለጸው አንዱ ጥቅልል እንኳ “ቅዱስ ጽሑፉ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዓመታት በአይሁድ ገልባጮች አማካኝነት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሲገለበጥ መቆየቱን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።”
በደብሊን፣ አየርላንድ የሚገኘው የቼስተር ቢቲ ቤተ መጻሕፍት እያንዳንዱን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሚወክል የፓፒረስ ስብስብ አለው፤ ከዚህ ስብስብ መካከል በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀ ከ100 ዓመት በኋላ ብቻ በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ይገኙበታል። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንደገለጸው “ፓፒረሶቹ ከጽሑፎቹ ጋር በተያያዘ አዳዲስ ዝርዝር መረጃዎችን ይዘዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተገለበጠው ጽሑፍ በሚያስገርም ሁኔታ ከመጀመሪያው ጽሑፍ ጋር እንደሚመሳሰል አሳይተዋል።”
“የዚህን ያህል በትክክል የተላለፈ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም”
ውጤቱ፦ በእጅ የተገለበጡ በርካታ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች መገኘታቸው በጽሑፉ ጥራት ላይ ጥያቄ ከማስነሳት ይልቅ የጽሑፉን ጥራት አረጋግጠዋል። ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስመልክተው ሲጽፉ እንደገለጹት “ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተቀር ለመልእክቱ እንዲህ ያለ በርካታ ጥንታዊ ማስረጃ የተገኘለት ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ የለም፤ እንዲሁም ጽሑፉ ይዘቱ ሳይለወጥ ወደ እኛ እንደደረሰ ማንኛውም ከአድሎ ነፃ የሆነ ምሁር አይክድም።” ዊሊያም ሄንሪ ግሪን የተባሉ ምሁር ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በተመለከተ ሲናገሩ “የዚህን ያህል በትክክል የተላለፈ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ብለዋል።