ከዓመፅ የጸዳ ዓለም ይመጣል?
አንተ ወይም የቤተሰብህ አባል የዓመፅ ድርጊት ሰለባ ሆናችሁ ታውቃላችሁ? ወደፊትስ እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥመኝ ይችላል የሚል ስጋት አለህ? ዓመፅ “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣ የማኅበረሰብ ችግር” እንደሆነ ይነገራል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
በቤት ውስጥ የሚፈጸም በደልና ፆታዊ ጥቃት፦ “ከሦስት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ በወንድ ጓደኛዋ ወይም በትዳር አጋሯ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃት ይደርስባታል” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘግቧል። የሚያሳዝነው ነገር “በመላው ዓለም ከአምስት ሴቶች አንዷ ተገዳ እንደምትደፈር ወይም አስገድዶ የመድፈር ሙከራ እንደሚደረግባት ይገመታል።”
በጎዳና ላይ የሚፈጸም ወንጀል፦ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በዩናይትድ ስቴትስ ከ30,000 የሚበልጡ የወንጀለኛ ቡድኖች በወንጀል ሥራ ላይ ተሠማርተዋል። በላቲን አሜሪካ ውስጥ ከ3 ሰዎች 1ዱ የዓመፅ ድርጊት እንደተፈጸመበት ተናግሯል።
የነፍስ ግድያ፦ በ2012 ብቻ ግማሽ ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ተገድለዋል፤ ይህም በጦርነት ከሞቱት ሰዎች የበለጠ ነው። በደቡባዊ አፍሪካና በማዕከላዊ አሜሪካ በነፍስ ግድያ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች አማካይ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ይህ አኃዝ በመላው ዓለም ከተመዘገበው አማካይ ቁጥር ከአራት እጥፍ በላይ ነው። በላቲን አሜሪካ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ100,000 የሚበልጡ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከእነዚህ መካከል 50,000 የሚያህሉት ሰዎች የተገደሉት በብራዚል ነው። ይሁንና ለዓመፅ ዘላቂ መፍትሔ ይገኝ ይሆን?
ዓመፅን ማስቆም ይቻላል?
ዓመፅ ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው? ብዙ ምክንያቶች የሚቀርቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ልዩነት ምክንያት የሚመጣ ግጭት፣ ለሌሎች ሕይወት ግድየለሽ መሆን፣ አልኮልንና ዕፆችን አላግባብ መጠቀም፣ ልጆች ትላልቅ ሰዎች ለሚፈጽሙት የዓመፅ ድርጊት መጋለጣቸው እንዲሁም ከባድ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከቅጣት ማምለጣቸው።
በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ዓመፅን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ውጤት እንዳስገኘ አይካድም። ብራዚል ውስጥ በምትገኘውና በሕዝብ በተጨናነቀችው የሳኦ ፓውሎ ከተማ ውስጥ የሚፈጸመው የግድያ ወንጀል ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ 80 በመቶ እንደቀነሰ ሪፖርት ተደርጓል። ያም ቢሆን በዚህች ከተማ የተለያዩ ዓይነት የዓመፅ ወንጀሎች በስፋት ይፈጸማሉ፤ በተጨማሪም ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል 10 ገደማ የሚሆኑት የግድያ ሰለባ ይሆናሉ። ታዲያ ዓመፅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወገደው እንዴት ነው?
ለዓመፅ ዘላቂው መፍትሔ ከሰዎች አመለካከትና ከምግባራቸው ጋር የተያያዘ ነው። ዓመፀኛ ሰዎች ሊለወጡ የሚችሉት ኩራትን፣ ስግብግብነትንና ራስ ወዳድነትን አስወግደው ፍቅርን፣ አክብሮትንና አሳቢነትን ሲያዳብሩ ነው።
ታዲያ አንድ ሰው እንዲህ ያለ ትልቅ ለውጥ ለማድረግ የሚያነሳሳው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር እንመልከት፦
-
“አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው።”—1 ዮሐንስ 5:3
አንድ ዓመፀኛ የሆነ ሰውም እንኳ አምላክን የሚወድና እሱን እንዳያሳዝን የሚፈራ ከሆነ ይህ ሕይወቱን ለመቀየር የሚያስችል ኃይል ይሰጠዋል፤ እንዲህ ያለው ለውጥ መላ ስብዕናውን የሚቀይር እንጂ ላይ ላዩን ብቻ የሚታይ ለውጥ አይደለም። በእርግጥ ይህ ሊፈጸም የሚችል ነገር ነው?
በተደጋጋሚ ጊዜ በሰዎች ላይ ጥቃት በመፈጸሙ ምክንያት ያለፉትን 19 ዓመታት በብራዚል በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ያሳለፈውን አሌክስን * እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አሌክስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ በ2000 የይሖዋ ምሥክር ሆነ። የዓመፀኝነት ባሕርይውን በእርግጥ ለውጧል? አዎ፤ እንዲያውም በፈጸማቸው መጥፎ ድርጊቶች ክፉኛ ተጸጽቷል። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ከልብ ይቅር እንዳለኝ ይሰማኛል፤ ይህም እሱን እንድወደው አድርጎኛል። ለይሖዋ ያለኝ ፍቅርና እሱ ላደረገልኝ ነገር ያለኝ አመስጋኝነት አኗኗሬን እንድለውጥ ረድቶኛል።”
በብራዚል የሚኖር ሲዛር የሚባል ሌላ ሰውም በሌብነት ወንጀል ይካፈል የነበረ ከመሆኑም ሌላ በመሣሪያ አስፈራርቶ ዝርፊያ ይፈጽም ነበር። አሥራ አምስት ለሚያህሉ ዓመታት ይህን ሲያደርግ ቆይቷል። ታዲያ እንዲለወጥ የረዳው ምንድን ነው? እሥር ቤት ሳለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቶ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ሲዛር እንዲህ ይላል፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ የሕይወት ዓላማ ገባኝ። ለአምላክ ፍቅር ማዳበር ጀመርኩ። በተጨማሪም አምላካዊ ፍርሃት ይኸውም ወደ መጥፎ ሕይወቴ በመመለስ ይሖዋን እንዳላሳዝነው ጤናማ ፍርሃት አደረብኝ። አምላክ ላሳየኝ ደግነት ምስጋና ቢስ ሆኜ መገኘት አልፈለግኩም። ለውጥ እንዳደርግ የረዳኝ እንዲህ ያለው ፍቅርና ፍርሃት ነው።
እነዚህ ተሞክሮዎች ምን ያሳዩናል? መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን አስተሳሰብ በመቀየር በሕይወታቸው ላይ ሥር ነቀል ለውጥ የማምጣት ኃይል አለው። (ኤፌሶን 4:23) ቀደም ሲል የተጠቀሰው አሌክስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት ነገር እንደ ንጹሕ ውኃ ሆኖልኛል፤ ይህ ውኃ ውስጤ ገብቶ መጥፎ ሐሳቦችን በማጠብ እየነጻሁ እንድሄድ አድርጎኛል። ከእነዚህ መጥፎ ሐሳቦች እገላገላለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም።” አዎ፣ አእምሯችንን ንጹሕ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ስንሞላው ቃሉ በውስጣችን ያለውን ክፋት ሊያስወግድልን ይችላል። የአምላክ ቃል የማንጻት ኃይል አለው። (ኤፌሶን 5:26) በውጤቱም ጨካኝና ራስ ወዳድ የነበሩ ሰዎች አኗኗራቸውን ለውጠው ደግና ሰላማዊ ይሆናሉ። (ሮም 12:18) እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋላቸው ሰላም ያስገኝላቸዋል።—ኢሳይያስ 48:18
በ240 አገሮች የሚኖሩ ከስምንት ሚሊዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ዓመፅን ለማስወገድ ቁልፉ ምን እንደሆነ ተገንዝበዋል። የተለያየ ዘር፣ የኑሮ ደረጃና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች አምላክን መውደድና መፍራት እንዲሁም እርስ በርስ በመዋደድ እንደ አንድ ዓለም አቀፍ ቤተሰብ ሆነው በሰላም መኖር ችለዋል። (1 ጴጥሮስ 4:8) በእርግጥም ከዓመፅ የጸዳ ዓለም እንደሚመጣ ሕያው ማስረጃ ናቸው።
ከዓመፅ የጸዳ ዓለም በቅርቡ ይመጣል!
አምላክ በቅርቡ ምድራችንን ከዓመፅ እንደሚያጸዳት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በዛሬው ጊዜ ያለው በዓመፅ የተሞላ ዓለም ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቆ ይቆያል።’ (2 ጴጥሮስ 3:5-7) ከዚያ በኋላ ዓመፀኛ ሰዎች ሌሎችን አያሠቃዩም። ታዲያ አምላክ ዓመፅን ማጥፋት እንደሚፈልግ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ይሖዋ . . . ክፋትን የሚወዱ ሰዎችን ይጠላል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 11:5) ፈጣሪ ሰላምንና ፍትሕን ይወዳል። (መዝሙር 33:5፤ 37:28) በመሆኑም በዓመፀኛ ሰዎች ላይ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል።
አዎ፣ በቅርቡ ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ይመጣል። (መዝሙር 37:11፤ 72:14) ታዲያ ከዓመፅ በጸዳው ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልጉት ብቃቶች ምን እንደሆኑ ለመማር ለምን ጥረት አታደርግም?
^ አን.12 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።
^ አን.14 ስሞቹ ተቀይረዋል።