በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራ የአምላክ ቅጣት ነው?

መከራ የአምላክ ቅጣት ነው?

ሉዚያ ግራ እግሯ ላይ ባለባት ችግር ምክንያት ታነክሳለች። ገና በልጅነቷ፣ በቀላሉ በሚዛመተውና የሰውነትን የነርቭ ሥርዓት በሚያጠቃው የፖሊዮ በሽታ ተያዘች። የ16 ዓመት ወጣት ሳለች፣ አሠሪዋ የነበረች አንዲት ሴት “አምላክ ሽባ እንድትሆኚ በማድረግ የቀጣሽ እኮ እናትሽን የማትታዘዢ መጥፎ ልጅ ስለነበርሽ ነው” አለቻት። እንዲህ ካለቻት ዓመታት ቢያልፉም ሉዚያ በወቅቱ ምን ያህል ስሜቷ ተጎድቶ እንደነበር ታስታውሳለች።

ዳማሪስ የአንጎል ካንሰር እንዳለባት ሲነገራት አባቷ “ይህ የደረሰብሽ ምን አጥፍተሽ ነው? መቼም በጣም መጥፎ ነገር ሠርተሽ መሆን አለበት። አምላክ እየቀጣሽ ያለው ለዚህ ነው” አላት። ዳማሪስ አባቷ በተናገረው ነገር ስሜቷ ክፉኛ ተጎድቶ ነበር።

‘በሽታ የአምላክ ቅጣት ነው’ የሚለው አመለካከት ከብዙ ዘመናት በፊት ጀምሮ ሲታመንበት ኖሯል። ማነርስ ኤንድ ከስተምስ ኦቭ ባይብል ላንድስ የተሰኘው መጽሐፍ በክርስቶስ ዘመን የነበሩ በርካታ ሰዎች “በሽታ አንድም በራሱ በታመመው ሰው ኃጢአት አሊያም በዘመዶቹ ኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ቅጣት ነው” ብለው ያምኑ እንደነበር ይናገራል። ሜዲቫል ሜዲሲን ኤንድ ዘ ፕሌግስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ደግሞ በመካከለኛው ዘመን ይኖሩ የነበሩ “አንዳንድ ሰዎች አምላክ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት እነሱን ለመቅጣት ሲል ወረርሽኝ እንደሚያመጣባቸው ያምኑ ነበር።” ታዲያ በ14ኛው መቶ ዘመን፣ በመላው አውሮፓ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በወረርሽኝ ሕይወታቸውን ያጡት አምላክ በክፉ ሰዎች ላይ የቅጣት ፍርዱን እያስፈጸመ ስለነበር ነው? ወይስ የሕክምና ተመራማሪዎች ከጊዜ በኋላ በምርምር እንደደረሱበት ወረርሽኙ እንዲሁ በባክቴሪያ ምክንያት የመጣ በሽታ ነው? አንዳንድ ሰዎች ‘በእርግጥ አምላክ፣ ሰዎች ለሠሩት ኃጢአት ቅጣት እንዲቀበሉ ሲል በበሽታ እንዲሠቃዩ ያደርጋል?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስባቸዋል። *

እስቲ አስበው፦ በሽታና መከራ አምላክ ቅጣት የሚገባቸውን ሰዎች ለመቅጣት ሲል የሚያመጣቸው ነገሮች ከሆኑ ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን የፈወሰው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጉ ከአምላክ ፍትሕና ጽድቅ ጋር የሚቃረን ነገር ማድረግ አይሆንበትም? (ማቴዎስ 4:23, 24) ኢየሱስ፣ አምላክ የወሰደውን እርምጃ የሚቃወም ነገር ፈጽሞ አያደርግም። “ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]” እንዲሁም “አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 8:29፤ 14:31

መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ሐሳብ የማያሻማ ነው። ይሖዋ አምላክ “ፈጽሞ ፍትሕን [አያጓድልም]።” (ዘዳግም 32:4) ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በአውሮፕላን ላይ የተሳፈረን አንድ ሰው ለመቅጣት ሲል ብቻ አውሮፕላኑ እንዲከሰከስ በማድረግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ሰዎች እንዲሞቱ እንደማያደርግ ግልጽ ነው! የአምላክ ታማኝ አገልጋይ የነበረው አብርሃም፣ ‘ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብሮ ማጥፋት’ ከአምላክ ጽድቅ ጋር እንደማይስማማ ተናግሯል። አክሎም “ይህ በአንተ ዘንድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው” ብሏል። (ዘፍጥረት 18:23, 25) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ክፋት አይሠራም” እንዲሁም “ክፉ ነገር [አያደርግም]” በማለት ይናገራል።—ኢዮብ 34:10-12

መጽሐፍ ቅዱስ መከራ የአምላክ ቅጣት እንዳልሆነ የሚያሳይ ምን ማስረጃ ይዟል?

መከራ የሚደርስብን አምላክ ለሠራነው ኃጢአት እየቀጣን ስለሆነ አይደለም። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ፣ ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ ሰው ባገኙ ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ይህን ጉዳይ ግልጽ የሚያደርግ ሐሳብ ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱ “ረቢ፣ ይህ ሰው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ማን በሠራው ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም “እሱም ሆነ ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም” በማለት መልስ ሰጣቸው።—ዮሐንስ 9:1-3

በዚያ ዘመን በሰፊው ተቀባይነት አግኝቶ ከነበረው የተሳሳተ አመለካከት አንጻር ኢየሱስ ሰውየው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው በእሱም ሆነ በወላጆቹ ኃጢአት ምክንያት እንዳልሆነ ሲነግራቸው ደቀ መዛሙርቱ ተገርመው መሆን አለበት። ኢየሱስ የሰውየው ዓይን እንዲበራ ከማድረግ አልፎ ‘መከራ የአምላክ ቅጣት ነው’ የሚለው አመለካከት ስህተት እንደሆነ አጋልጧል። (ዮሐንስ 9:6, 7) በዛሬው ጊዜ ከከባድ ሕመም ጋር እየታገሉ ያሉ ሰዎች የሥቃያቸው መንስኤ አምላክ እንዳልሆነ ሲያውቁ ሊጽናኑ ይችላሉ።

አምላክ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችን እንዲታመሙ በማድረግ እየቀጣቸው ከነበረ ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች የፈወሳቸው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማረጋገጫ

  • “አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) እንዲያውም በሽታን፣ ሥቃይንና ሞትን ጨምሮ ለብዙ መቶ ዘመናት የሰውን ዘር ሲያስጨንቁ የኖሩትን ‘ክፉ ነገሮች’ በቅርቡ ያስወግዳል።

  • ኢየሱስ ክርስቶስ ‘እየተሠቃዩ የነበሩትን ሁሉ ፈውሷል።’ (ማቴዎስ 8:16) የአምላክ ልጅ ወደ እሱ የመጡትን ሁሉ በመፈወስ የአምላክ መንግሥት ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያከናውነውን ነገር በግልጽ አሳይቷል።

  • “እሱም [አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3-5

ለሚደርስብን መከራ ተጠያቂው ማን ነው?

ታዲያ የሰው ዘር ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ እየደረሰበት ያለው ለምንድን ነው? ሰዎች ለብዙ መቶ ዘመናት ይህን ጥያቄ ሲጠይቁ ኖረዋል። ለሚደርስብን መከራ ተጠያቂው አምላክ ካልሆነ ታዲያ ተጠያቂው ማን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ይዟል።

^ አን.4 ቀደም ባሉት ዘመናት አምላክ፣ ሰዎችን ለኃጢአት ድርጊታቸው የቀጣባቸው ጊዜያት እንደነበሩ አይካድም። ሆኖም ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን ለሠሩት ኃጢአት ለመቅጣት ሲል በበሽታ እንዲያዙ ወይም ሌሎች ችግሮች እንዲደርሱባቸው እንደሚያደርግ የሚጠቁም የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ የለም።