በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የዮሴፍ አባት ማን ነው?

ናዝሬት ውስጥ አናጺ የነበረው ዮሴፍ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ነው። ይሁንና የዮሴፍ አባት ማን ነው? በማቴዎስ ወንጌል ላይ ያለው የኢየሱስ የዘር ሐረግ ያዕቆብ ስለሚባል አንድ ሰው የሚናገር ሲሆን የሉቃስ ዘገባ ግን “ዮሴፍ የሄሊ ልጅ” መሆኑን ይናገራል። ይህ ልዩነት እንዴት ሊፈጠር ቻለ?—ሉቃስ 3:23፤ ማቴዎስ 1:16

የማቴዎስ ዘገባ “ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ” የሚል ሲሆን እዚህ ላይ የተሠራበት ግሪክኛ ቃል ያዕቆብ የዮሴፍ ወላጅ አባት መሆኑን በግልጽ ይጠቁማል። በመሆኑም ማቴዎስ የዮሴፍን የዘር ሐረግ የቆጠረው በንጉሣዊው የዳዊት መስመር በኩል ነው፤ ዮሴፍ ያሳደገው ልጅ ማለትም ኢየሱስ ዙፋኑን የመውረስ ሕጋዊ መብት የሚያገኘው በዚህ መሠረት ይሆናል።

በሌላ በኩል ግን የሉቃስ ዘገባ “ዮሴፍ የሄሊ ልጅ” ይላል። እዚህ ላይ የገባው “ልጅ” የሚለው ቃል “አማች” በሚል ሊወሰድም ይችላል። ሉቃስ 3:27 ላይ ተመሳሳይ ዘገባ የሚገኝ ሲሆን የሰላትያል ትክክለኛ አባት ኢኮንያን ሆኖ ሳለ ዝርዝሩ ላይ የሰፈረው ግን “የኔሪ ልጅ” ተብሎ ነው። (1 ዜና መዋዕል 3:17፤ ማቴዎስ 1:12) ሰላትያል በስም ያልተጠቀሰችን የኔሪን ሴት ልጅ በማግባቱ የኔሪ አማች ሳይሆን አይቀርም። ዮሴፍም የሄሊን ሴት ልጅ ይኸውም ማርያምን ስላገባ በተመሳሳይ ሁኔታ የሄሊ “ልጅ” ሊባል ይችላል። ስለዚህ ሉቃስ የኢየሱስን የዘር ሐረግ የቆጠረው ‘ከሥጋዊ ዘር’ አንጻር ማለትም በወላጅ እናቱ በማርያም በኩል ነው። (ሮም 1:3) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን የዘር ሐረግ ከሁለት የተለያዩ አቅጣጫዎች ያቀርብልናል፤ ሁለቱም ደግሞ ጠቃሚ መረጃ ይዘዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ምን ዓይነት ጨርቆችና ማቅለሚያዎች ይገኙ ነበር?

ከ135 ዓ.ም. በፊት የተዘጋጀ በሙት ባሕር አቅራቢያ ባለ ዋሻ ውስጥ የተገኘ ቀለም የተነከረ ሱፍ

ጥንት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ የበግ ሱፍ እንዲሁም የፍየልና የግመል ፀጉር ጨርቅ ለማምረት በሰፊው ይሠራባቸው ነበር። በጥንት ጊዜ አብዛኞቹ ጨርቆች ከሱፍ የተዘጋጁ ነበሩ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በጎች፣ በጎችን ስለ መሸለትና ከሱፍ ስለተሠራ ልብስ ብዙ ጊዜ ይናገራል። (1 ሳሙኤል 25:2፤ 2 ነገሥት 3:4፤ ኢዮብ 31:20) በፍታ ለማዘጋጀት የሚያገለግለው የተልባ እግር ተክል ግብፅና እስራኤል ውስጥ ይበቅል ነበር። (ዘፍጥረት 41:42፤ ኢያሱ 2:6) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ጥጥ ስለማምረታቸው የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ቅዱሳን መጻሕፍት ፋርስ ውስጥ የጥጥ ክር ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ይናገራሉ። (አስቴር 1:6) ሐር በጣም ውድ የሆነ የቅንጦት ጨርቅ ነበር፤ ከሩቅ ምሥራቅ የሚያመጡትም ተጓዥ ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ አይቀሩም።—ራእይ 18:11, 12

ጂሰስ ኤንድ ሂዝ ዎርልድ የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው “ሱፍ በተለያዩ ቀለማት ይዘጋጅ ነበር፤ ሙሉ በሙሉ ነጭ ከሆነ አንስቶ እስከ ደማቅ ቡኒ ድረስ የተለያየ ዓይነት ቀለማት ሊኖረው ይችላል።” ከዚህ በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ ሱፍ ቀለም ይነከራል። ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ሐምራዊ ቀለም ከአንዳንድ የዛጎል ዓይነቶች ይዘጋጅ ነበር፤ ልዩ ልዩ ተክሎች፣ ሥራ ሥሮች፣ ቅጠሎችና ነፍሳትም የተለያዩ ዓይነት ቀለሞችን ይኸውም ቀይ፣ ቢጫ፣ ሰማያዊና ጥቁር ቀለም ለማዘጋጀት ያገለግሉ ነበር።