በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ

የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም

የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም

ሐዘን የደረሰበትን ሰው ከማጽናናት ጋር በተያያዘ ምክር የማይሰጥ ሰው የለም ቢባል ይቀልላል። ይሁንና ሁሉም ምክር ጠቃሚ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች እንዳታለቅስ ወይም ስሜትህን ዋጥ አድርገህ እንድትይዝ ሊመክሩህ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ስሜትህን ሁሉ እንድታወጣ ይገፋፉህ ይሆናል። ከዚህ በተለየ መጽሐፍ ቅዱስ ሚዛናዊ የሆነ ሐሳብ ይዟል፤ በዘመናችን ያሉ ተመራማሪዎችም ይህን ሐሳብ ይጋራሉ።

በአንዳንድ ባሕሎች ወንድ ልጅ ማልቀስ እንደሌለበት ይነገራል። ይሁንና አንድ ሰው በሰው ፊት ማልቀስ አሳፋሪ ነገር እንደሆነ ሊሰማው ይገባል? የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ማልቀስ የተለመደ የሐዘን ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ። የደረሰብህ ጉዳት መራራ ቢሆንም ስሜትህን ማውጣትህ፣ ውሎ አድሮ ሁኔታውን ተቋቁመህ እንድትቀጥል ሊረዳህ ይችላል። ይሁን እንጂ ሐዘንን ማፈን ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ማልቀስ ተገቢ አይደለም የሚለውንም ሆነ ወንድ ልጅ ማልቀስ የለበትም የሚለውን አስተሳሰብ አይደግፍም። ኢየሱስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ ሙታንን የማስነሳት ኃይል ቢኖረውም እንኳ ወዳጁ አልዓዛር በሞተበት ወቅት በሰው ፊት አልቅሷል!—ዮሐንስ 11:33-35

በተለይ አንድን ሰው በሞት ያጣነው በድንገት ከሆነ አልፎ አልፎ የብስጭት ስሜት ሊያድርብን ይችላል። ሐዘን የደረሰበት ሰው እንዲበሳጭ የሚያደርገው ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ለምሳሌ በአክብሮት የምናየው ሰው ያልታሰበበትና አግባብ ያልሆነ ነገር ሲናገር እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊፈጠርብን ይችላል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ሲሞት ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ አንድ የአንግሊካን ሰባኪ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ አምላክ ጥሩ ሰዎች እንደሚያስፈልጉትና እነሱን በጊዜ እንደሚወስዳቸው ገለጸ። * አባታችን አብሮን መሆኑ በጣም ያስፈልገን ስለነበር ይህ አባባሉ አበሳጨኝ። ይህ ከሆነ 63 ዓመት ያለፈ ቢሆንም አባባሉ አሁንም ስሜቴ እንደጎዳው ነው።”

ስለ ጥፋተኝነት ስሜትስ ምን ማለት ይቻላል? በተለይ ግለሰቡ የሞተው በድንገት ከሆነ ሐዘንተኛው ‘እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ እኮ ባልሞተ ነበር’ በማለት ሊያውጠነጥን ይችላል። አሊያም ደግሞ ከሟቹ ጋር በተያያዘ ትዝ የሚልህ የመጨረሻው ነገር በመካከላችሁ የተፈጠረው ጭቅጭቅ ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜቱን ያባብስብህ ይሆናል።

በጥፋተኝነት ስሜት እና በብስጭት ከተዋጥክ እነዚህን ስሜቶች አፍነህ አለመያዝህ በጣም ይረዳሃል። ከዚህ ይልቅ ለሚያዳምጥህና ሐዘን ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች እንዲህ ያሉ ተገቢ ያልሆኑ ስሜቶች እንደሚታዩባቸው ሊነግርህ ለሚችል አንድ ወዳጅህ ስሜትህን አወያየው። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል።—ምሳሌ 17:17

ሐዘን የደረሰበት ሰው ከፈጣሪያችን፣ ከይሖዋ አምላክ የተሻለ ወዳጅ ሊያገኝ አይችልም። “እሱ ስለ [አንተ] ያስባል”፤ በመሆኑም የልብህን አፍስሰህ በጸሎት ንገረው። (1 ጴጥሮስ 5:7) በተጨማሪም ወደ እሱ ለሚጸልዩ ሁሉ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን የሚያረጋጋላቸው “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም” እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አምላክ፣ በሚያበረታታው ቃሉ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እንዲያጽናናህም ፍቀድለት። የሚያጽናኑ ጥቅሶችን በዝርዝር ጻፍ። ( ሣጥኑን ተመልከት።) እንዲያውም አንዳንዶቹን በቃልህ መያዝ ትፈልግ ይሆናል። በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰልህ  በተለይ ሌሊት ላይ ብቻህን ስትሆንና እንቅልፍ አልወስድ ሲልህ አበረታች ይሆንልሃል።—ኢሳይያስ 57:15

ጃክ * የተባለ የ40 ዓመት ሰው የሚወዳት ባለቤቱን በቅርቡ በካንሰር አጥቷል። ጃክ አንዳንድ ጊዜ የከፋ የብቸኝነት ስሜት እንደሚያድርበት ገልጿል። ሆኖም መጸለዩ ረድቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ይሖዋ ስጸልይ ፈጽሞ የብቸኝነት ስሜት አይሰማኝም። አብዛኛውን ጊዜ ሌሊት ላይ እነቃለሁ፤ ከዚያ በኋላ እንቅልፍ አይወስደኝም። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ የሚያጽናኑ ጥቅሶችን ሳነብ፣ ባነበብኩት ላይ ሳሰላስል ብሎም የልቤን ግልጥልጥ አድርጌ ስጸልይ ከፍተኛ የሆነ የመረጋጋትና የደህንነት ስሜት ይሰማኛል፤ እንዲህ ማድረጌ አእምሮዬንና ልቤን የሚያሳርፍልኝ ከመሆኑም ሌላ እንቅልፍ እንዲወስደኝ ይረዳኛል።”

ቨኒሳ የተባለች ወጣት እናቷን በበሽታ ምክንያት አጥታለች። እሷም ጸሎት ያለውን ኃይል በሕይወቷ ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ጭንቅ ሲለኝ የአምላክን ስም ጠርቼ ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ እጸልያለሁ። ይሖዋ ጸሎቴን ሰምቶ ሁልጊዜ የሚያስፈልገኝን ብርታት ይሰጠኛል።”

ለሐዘንተኞች ምክር የሚሰጡ አንዳንድ ባለሙያዎች ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ሌሎችን እንዲረዱ ወይም ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ነገር በማከናወን የተወሰነ ጊዜ እንዲያሳልፉ ይመክራሉ። እንዲህ ማድረግ ደስታ ሊያስገኝና ግለሰቡ ሐዘኑ እንዲቀለው ሊያደርግ ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ሐዘን የደረሰባቸው በርካታ ክርስቲያኖች ሌሎችን ለመርዳት አንዳንድ ነገሮችን ማከናወናቸው ከፍተኛ ማጽናኛ እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

^ አን.5 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። መጽሐፍ ቅዱስ ለሞት ምክንያት የሆኑ ሦስት ነገሮችን ይጠቅሳል።—መክብብ 9:11፤ ዮሐንስ 8:44፤ ሮም 5:12

^ አን.9 ስሙ ተቀይሯል።