በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ማን ነው?

የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ማን ነው?

አምላክ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች፣ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ የሚያስተዳድረውን ገዢ ለማወቅ የሚያስችሉ ምልክቶችን በዝርዝር እንዲጽፉ አድርጓል። ይህን ንጉሥ ለይተው ከሚያሳውቁ ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • በአምላክ የተመረጠ። “እኔ ራሴ . . . ንጉሤን ሾምኩ። . . . ብሔራትን ርስትህ፣ የምድርንም ዳርቻዎች ግዛትህ አድርጌ እሰጥሃለሁ።”—መዝሙር 2:6, 8

  • የንጉሥ ዳዊት ወራሽ። “ልጅ ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ . . . በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ ይቀመጣል፤ እየተጠናከረ የሚሄደው አገዛዙም ሆነ ሰላሙ ፍጻሜ አይኖረውም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም በማይናወጥ ሁኔታ ይመሠረታል።”—ኢሳይያስ 9:6, 7

  • በቤተልሔም ይወለዳል። “ቤተልሔም . . . ሆይ፣ . . . ገዢ የሚሆን ከአንቺ ይወጣልኛል። . . . ታላቅነቱ እስከ ምድር ዳርቻ ይደርሳል።”—ሚክያስ 5:2, 4

  • በሰዎች ይናቃል እንዲሁም ይገደላል። “ሰዎች ናቁት፤ እኛም ከቁብ አልቆጠርነውም። እሱ ግን ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችን ደቀቀ።”—ኢሳይያስ 53:3, 5

  • ከሞት ይነሳል እንዲሁም ክብር ይላበሳል። “መቃብር ውስጥ አትተወኝምና። ታማኝ አገልጋይህ ጉድጓድ እንዲያይ አትፈቅድም። . . . በቀኝህ ለዘላለም ደስታ አለ።”—መዝሙር 16:10, 11

ኢየሱስ ክርስቶስ ብቃቱን ያሟላል

በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ፣ ገዢ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ሁሉ አሟልቶ የተገኘው አንድ ሰው ብቻ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲያውም አንድ መልአክ ለኢየሱስ እናት ለማርያም “አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” ብሏት ነበር።—ሉቃስ 1:31-33

ኢየሱስ ምድር ላይ እያለ ንጉሥ አልነበረም። ወደፊት ግን የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን ከሰማይ ሆኖ የሰው ልጆችን ይገዛል። ኢየሱስ ከማንም የተሻለ ንጉሥ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ምን ዓይነት ሰው እንደነበር ለማስተዋል ሞክር።

  • ኢየሱስ ለሰዎች ያስብ ነበር። ኢየሱስ ሰዎችን በዕድሜ፣ በፆታ ወይም በኑሮ ደረጃ ሳይለይ ሁሉንም ይረዳ ነበር። (ማቴዎስ 9:36፤ ማርቆስ 10:16) በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ሲለምነው በጣም ስላዘነለት ፈውሶታል።—ማርቆስ 1:40-42

  • ኢየሱስ አምላክን ማስደሰት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አስተምሯል። “ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም” በማለት ተናግሯል። እንዲሁም ሌሎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር ሁሉ እኛም ልናደርግላቸው እንደሚገባ አስተምሯል፤ ይህ ምክር “ወርቃማው ሕግ” በመባል ይታወቃል። ከዚህም ሌላ፣ አምላክ ድርጊታችንን ብቻ ሳይሆን አስተሳሰባችንንና ስሜታችንንም ጭምር በትኩረት እንደሚመለከት ገልጿል። በመሆኑም አምላክን ማስደሰት ከፈለግን ውስጣዊ ስሜታችንን መቆጣጠር ይኖርብናል። (ማቴዎስ 5:28፤ 6:24፤ 7:12) ኢየሱስ እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግን አምላክ የሚጠብቅብንን ነገር ማወቅና ያወቅነውን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን አበክሮ ተናግሯል።—ሉቃስ 11:28

  • ኢየሱስ ሌሎችን መውደድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስተምሯል። ኢየሱስ የተናገራቸውም ሆነ ያደረጋቸው ነገሮች የአድማጮቹን ልብ በጥልቅ ነክተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤ የሚያስተምራቸው . . . እንደ ባለሥልጣን ነበርና” ይላል። (ማቴዎስ 7:28, 29) “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል። በእሱ ግድያ ለተካፈሉት አንዳንድ ሰዎች እንኳ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል።—ማቴዎስ 5:44፤ ሉቃስ 23:34

ኢየሱስ ደግና አሳቢ የዓለም ገዢ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ፍጹም በሆነ መልኩ ያሟላል። ሆኖም መግዛት የሚጀምረው መቼ ነው?