በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትክክል የተፈጸሙ ትንቢቶች

በትክክል የተፈጸሙ ትንቢቶች

የዴልፊው ጠንቋይ በሰጠው የተሳሳተ መረጃ ምክንያት በፋርስ ንጉሥ ድል ስለተመታው ስለ ክሪሰስ የሚናገረውን ታሪክ ቀደም ሲል ተመልክተን ነበር። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፋርስ ንጉሥ የተናገረው ትንቢት እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል።

ኢሳይያስ የተባለ አንድ ዕብራዊ ነቢይ አንድ ንጉሥ ኃያል የነበረችውን ባቢሎንን ድል የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ከ200 ዓመታት በፊት ተናግሮ ነበር፤ ኢሳይያስ ትንቢቱን የተናገረው ቂሮስ ከመወለዱ ከረጅም ዓመታት በፊት ቢሆንም የንጉሡ ስም ቂሮስ እንደሆነ ጭምር ተናግሯል።

ኢሳይያስ 44:24, 27, 28 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ . . . ‘ጥልቁን ውኃ “ደረቅ ሁን፤ ወንዞችህንም ሁሉ አደርቃለሁ” እላለሁ፤ ስለ ቂሮስ “እሱ እረኛዬ ነው፤ ፈቃዴንም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል” እላለሁ፤ ስለ ኢየሩሳሌም “ዳግም ትገነባለች”፤ ስለ ቤተ መቅደሱም “መሠረትህ ይጣላል” እላለሁ።’”

ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶቱስ የቂሮስ ሠራዊት የባቢሎንን ከተማ አቋርጦ ያልፍ የነበረውን የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ እንዳስቀየረ ጽፏል። ቂሮስ የተጠቀመበት የጦር ስልት ሠራዊቱ ወንዙን አቋርጦ ወደ ከተማዋ እንዲገባ አስችሏል። ቂሮስ ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ በምርኮ ወደ ባቢሎን የተወሰዱትን አይሁዳውያን ነፃ አውጥቷቸዋል፤ ከዚያም ወደ አገራቸው ተመልሰው ለ70 ዓመት ባድማ ሆና የቆየችውን ኢየሩሳሌምን መልሰው እንዲገነቡ ፈቀደላቸው።

ኢሳይያስ 45:1 “ይሖዋ . . . ብሔራትን በፊቱ ለማስገዛት፣ ነገሥታትን ትጥቅ ለማስፈታት እንዲሁም የከተማው በሮች እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ ለመክፈት [ሲል ቀኝ እጁን ለያዘው ለቂሮስ እንዲህ ይላል]።”

በባቢሎን ቅጥር ላይ ግዙፍ በሮች የነበሩ ሲሆን በዚያን ዕለት በግዴለሽነት ክፍት ተትተው ነበር፤ በመሆኑም ፋርሳውያን በእነዚህ በሮች በኩል ወደ ከተማዋ ገቡ። ባቢሎናውያን የቂሮስን ዕቅድ ቢያውቁ ኖሮ ወደ ወንዙ የሚወስዱትን በሮች በሙሉ ይዘጉ ነበር። ያም ሆነ ይህ የዚያን ዕለት የባቢሎን በሮች የከተማዋ መከላከያ መሆን አልቻሉም።

ይህ አስደናቂ ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በትክክል የተፈጸሙ በርካታ ትንቢቶች መካከል አንዱ ብቻ ነው። * ብዙውን ጊዜ ሰዎች ትንቢት ሲናገሩ ትንቢቶቹ የመጡት ከሚያመልኳቸው የሐሰት አማልክት እንደሆነ ይናገራሉ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች ምንጭ ግን “ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ገና ያልተከናወኑትንም ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሜ እናገራለሁ” በማለት የተናገረው አምላክ ነው።—ኢሳይያስ 46:10

እንዲህ ብሎ መናገር የሚችለው ስሙ ይሖዋ የሆነው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው። በርካታ ምሁራን ይሖዋ የሚለው ስም ትርጉም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል እንደሆነ ይስማማሉ። የዚህ ስም ትርጉም ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ እንዲሁም አንዳንድ ነገሮች ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲከናወኑ የማድረግ ችሎታ እንዳለው ያመለክታል። በተጨማሪም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በሙሉ እንደሚፈጽም ዋስትና ይሰጠናል።

በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉ ትንቢቶች

መጽሐፍ ቅዱስ የምንኖርበትን ዘመን አስመልክቶ ምን እንደሚል ማወቅ ትፈልጋለህ? የአምላክ ቃል ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ” ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይህ ወቅት የምን ነገር መጨረሻ ነው? የምድር ወይም የሰው ዘር መጨረሻ ሳይሆን የሰው ልጆችን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲያሠቃዩ የነበሩት ብጥብጥ፣ ጭቆናና መከራ ለዘለቄታው የሚጠፉበት ወቅት ነው። እስቲ ‘የመጨረሻዎቹን ቀናት’ ለይተው ከሚያሳውቁት ትንቢቶች ውስጥ የተወሰኑትን እንመልከት።

2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 “በመጨረሻዎቹ ቀናት . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፤ በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ።”

በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች እዚህ ላይ የተጠቀሱትን ባሕርያት እያንጸባረቁ ነው ቢባል አትስማማም? ብዙ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱና በኩራት የተወጠሩ አይደሉም? ከሌሎች ብዙ የሚጠብቁ ከመሆናቸውም ሌላ ለመስማማት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አላስተዋልክም? በተጨማሪም ልጆች ለወላጆች እንደማይታዘዙና በጥቅሉ ሲታይ ሰዎች ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን እንደሚወዱ ሳታስተውል አትቀርም። ደግሞም እነዚህ ነገሮች ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ ነው።

ማቴዎስ 24:6, 7 “ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። . . . ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል።”

ከ1914 ጀምሮ በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭቶች ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ100 ሚሊዮን እንደሚበልጥ ይገመታል፤ ይህ ቁጥር ብዙ አገሮች ካላቸው የሕዝብ ብዛት ይበልጣል። በዚህ ምክንያት የተከሰተው ሐዘን፣ ሰቆቃና መከራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ታዲያ መንግሥታት የደረሰውን እልቂት በማስተዋል ጦርነትን ለማቆም ይስማሙ ይሆን?

ማቴዎስ 24:7 “የምግብ እጥረት . . . ይከሰታል።”

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፦ “ዓለማችን ላይ ሁሉንም ሰው ለመመገብ የሚበቃ ምግብ ቢኖርም 815 ሚሊዮን ሰው ማለትም ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ ጦም አዳሪ ነው። ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያለው ሕዝብ ማለትም አንድ ሦስተኛው የዓለማችን ሕዝብ ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሠቃየ ነው።” በተጨማሪም በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን የሚያህሉ ሕፃናት በረሃብ ምክንያት እንደሚሞቱ ይገመታል።

ሉቃስ 21:11 “ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ።”

በየዓመቱ ሰዎች ሊያስተውሉት የሚችል ንዝረት ያላቸው 50,000 የሚያህሉ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ። ከእነዚህ መካከል 100 የሚያህሉት በሕንፃዎች ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን በየዓመቱ ቢያንስ አንድ ከፍተኛ የምድር ነውጥ ይከሰታል። አንድ ግምታዊ መረጃ እንደሚገልጸው ከሆነ ከ1975 እስከ 2000 ባሉት ዓመታት ውስጥ በመሬት ነውጥ ምክንያት 471,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ማቴዎስ 24:14 “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”

ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ምድር 240 በሚያህሉ አገሮች ውስጥ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሲሰብኩ ቆይተዋል። በትላልቅ ከተሞች፣ ርቀው በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች፣ በጫካዎች ውስጥ እንዲሁም በተራሮች ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን እያወጁ ነው። ይህ ሥራ አምላክ በቃ እስኪል ድረስ ከተካሄደ በኋላ “መጨረሻው ይመጣል” በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ይናገራል። ይህ ምን ማለት ይሆናል? ሰብዓዊ አገዛዝ ጠፍቶ የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ይሆናል። ታዲያ የአምላክ መንግሥት መግዛት ሲጀምር የትኞቹ ትንቢቶች ይፈጸማሉ? ይህ መጽሔት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

^ድምፅ አልባው ምሥክር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።