በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትችላለህ
ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! ፈጣሪያችን እዚሁ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ይህን አምኖ መቀበል ይከብዳቸዋል። ‘ሰው ሁሉ መሞቱ አይቀርም። ይህ ተፈጥሯዊ ዑደት ነው’ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ‘ለዘላለም መኖር ይቻላል፤ የምንኖረው ግን እዚህ ምድር ላይ አይደለም’ የሚል አመለካከት አላቸው። አንድ ሰው የዘላለም ሕይወት የሚያገኘው ከሞተ በኋላ ወደ ሰማይ ሲሄድ ነው ብለው ያምናሉ። አንተስ ምን ትላለህ?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠትህ በፊት ግን መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ መመርመርህ ጠቃሚ ነው፦ የሰው ልጅ አፈጣጠር በራሱ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ ተደርገው መፈጠራቸውን የሚያሳየው እንዴት ነው? አምላክ ለምድርና ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ምንድን ነው? ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?
የሰው ልጆች ልዩ አፈጣጠር
አምላክ በምድር ላይ እንዲኖሩ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ የሰው ልጆች በጣም የተለዩ ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች የተፈጠሩት በአምላክ “መልክ” እና “አምሳል” እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ይህ ምን ማለት ነው? የሰው ልጆች እንደ ፍቅርና ፍትሕ ያሉትን የአምላክ ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ ተሰጥቷቸዋል ማለት ነው።
በተጨማሪም ሰዎች የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ ተሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ከሥነ ምግባር አንጻር ጥሩና መጥፎ የሆነውን የመለየት ችሎታና ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና የመመሥረት ፍላጎት አላቸው። አጽናፈ ዓለምንና የፍጥረት ሥራዎችን ስንመለከት የምንደነቀው ወይም በሥነ ጥበብ፣ በሙዚቃና በሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የምንደመመው ለዚህ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሰው ልጅ ፈጣሪን የማምለክ ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለው። እነዚህ ነገሮች ሰዎችን በምድር ላይ ካሉ ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ እጅግ የተለዩ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።
ከዚህ አንጻር እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የሰው ልጆች የተፈጠሩት ለ70 ወይም ለ80 ዓመታት እንዲኖሩ ብቻ ቢሆን ኖሮ አምላክ እንዲህ ያሉ አስደናቂ ባሕርያትን የማንጸባረቅ ብሎም እነዚህን ባሕርያት ይበልጥ የማዳበር ችሎታ እንዲኖራቸው ያደርግ ነበር? በፍጹም! አምላክ እነዚህን ልዩ ባሕርያትና ችሎታዎች የሰጠን እዚሁ ምድር ላይ ለዘላለም በደስታ እንድንኖር አስቦ ነው።
የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ
ይሁንና አንዳንዶች አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ አይደለም ይላሉ። እነዚህ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ አምላክ ምድርን የፈጠራት ሰዎችን ለመፈተን የምታገለግል ጊዜያዊ መኖሪያ እንድትሆን አስቦ ነው፤ ሰዎች እዚህ ምድር ላይ ከተፈተኑ በኋላ ጥሩ ሆነው የተገኙት ሰዎች ወደ ሰማይ ሄደው ከአምላክ ጋር ለዘላለም ይኖራሉ ብለው ያምናሉ። ይህ ሐሳብ እውነት ከሆነ በምድር ላይ ለተስፋፋው ኃጢአትና ክፋት ዘዳግም 32:4
ተጠያቂው አምላክ ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከአምላክ ባሕርይ ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነገር ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ [ናቸው]። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው።”—መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ሲገልጽ “ሰማያት የይሖዋ ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል። (መዝሙር 115:16) አዎ፣ አምላክ ምድርን ውብ አድርጎ የፈጠራት የሰው ልጆች ለዘላለም እንዲኖሩባት ሲሆን አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት በሚያስችሉ ነገሮች እንድትሞላ አድርጓል።—ዘፍጥረት 2:8, 9
“ሰማያት የይሖዋ ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።”—መዝሙር 115:16
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች ምን ዓላማ እንዳለው በግልጽ ይናገራል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም። እንዲሁም . . . በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው” ብሏቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) አዳምና ሔዋን የሚኖሩባትን ገነት የመንከባከብና መላዋን ምድር ገነት የማድረግ ልዩ መብት አግኝተው ነበር። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አዳምና ሔዋን የተሰጣቸው ተስፋ ከልጆቻቸው ጋር በምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንጂ ወደ ሰማይ መሄድ አልነበረም።
የምንሞተው ለምንድን ነው?
ታዲያ የምንሞተው ለምንድን ነው? በአምላክ ላይ ያመፀ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስ አምላክ ለሰው ልጆች የነበረውን ዓላማ ለማጨናገፍ ጥረት አደረገ። ይህን ያደረገው እንዴት ነው?
ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ዓምፀው ከእሱ ጎን እንዲሰለፉ አደረገ። አምላክ ለእነሱ የሚጠቅማቸውን ነገር እንደከለከላቸው ይኸውም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለራሳቸው የመወሰን መብት እንደነፈጋቸው ሰይጣን ሲነግራቸው ከእሱ ጎን በመቆም ለአምላክ ጀርባቸውን ሰጡ። ውጤቱስ ምን ሆነ? አምላክ አስቀድሞ እንደተናገረው ከጊዜ በኋላ ሞቱ። ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጡ።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-6፤ 5:5
አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ማመፃቸው በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ችግር አስከትሏል። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ . . . ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) የምንሞተው ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአትንና ሞትን ስለወረስን እንጂ አምላክ አስቀድሞ የወሰነው ነገር ስለሆነ ወይም እኛ ያልተረዳነው የሆነ ‘ዕቅድ’ ስላለው አይደለም።
በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትችላለህ
በኤደን የተነሳው ዓመፅ አምላክ ለሰው ዘርና ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ እንዲከሽፍ አላደረገም። አምላክ አፍቃሪና ፍትሐዊ በመሆኑ ከአዳም ከወረስነው ኃጢአትና ሞት ነፃ የምንወጣበትን መንገድ አዘጋጅቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ብሏል። (ሮም 6:23) “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን [ኢየሱስ ክርስቶስን] ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ ራሱን በፈቃደኝነት ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ በአዳም ምክንያት ያጣነውን ነገር ሁሉ መልሰን ማግኘት የምንችልበትን መንገድ ከፍቷል። *
አምላክ ምድር ገነት እንደምትሆን የሰጠው ተስፋ በቅርቡ እውን ይሆናል። አንተም ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ካደረግክ ይህ አስደሳች ተስፋ ሲፈጸም ታያለህ፦ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) አዎ፣ ወደፊት የምታገኘው ነገር የተመካው አሁን በምታደርገው ምርጫ ላይ ነው። ታዲያ ምን ዓይነት ምርጫ ታደርግ ይሆን?
^ ቤዛው ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ የሚገልጽ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ከፈለግክ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 27 ተመልከት። መጽሐፉን ከwww.jw.org/am ላይ በነፃ ማውረድም ይቻላል።