በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያኖች በቅዱስ ስፍራዎች ማምለክ ይኖርባቸዋል?

ክርስቲያኖች በቅዱስ ስፍራዎች ማምለክ ይኖርባቸዋል?

በየዓመቱ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች፣ ጃፓን በሚገኘው በሺማ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ወዳለው የአርዘ ሊባኖስ ደን ይጓዛሉ። እነዚህ ሰዎች የሚሄዱት፣ አማቴራሱ ኦሚካሚ የምትባለው የሺንቶ የፀሐይ አምላክ፣ ሁለት ሺህ ለሚያህሉ ዓመታት ስትመለክ ወደኖረችበት ታላቁ የኢሴ ቅዱስ ስፍራ ነው። ለአምልኮ ወደዚያ የሚሄዱት ሰዎች በመጀመሪያ እጃቸውን በመታጠብና አፋቸውን በመጉመጥመጥ ራሳቸውን ያነፃሉ። ከዚያም በቅዱስ ስፍራው ሃኢደን (የማምለኪያ አዳራሽ) ፊት ለፊት ቆመው ለዚህች እንስት አምላክ መስገድን፣ ማጨብጨብንና መጸለይን ያካተተ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ይፈጽማሉ። * የሺንቶ ሃይማኖት አባላት፣ በሌሎች ሃይማኖቶች የአምልኮ ሥርዓት መካፈል ይፈቀድላቸዋል፤ አንዳንድ የቡድሂዝም እምነት ተከታዮች፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችና ሌሎችም በኢሴ ቅዱስ ስፍራ በሚካሄደው የሺንቶ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት መካፈላቸው ከራሳቸው ሃይማኖት ጋር እንደሚጋጭ አይሰማቸውም።

በርካታ የዓለም ዋና ዋና ሃይማኖቶች ቅዱስ ስፍራዎች * ያሏቸው ሲሆን በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ስፍራዎች ይጎበኟቸዋል። ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮችም ለኢየሱስ፣ ለማርያምና ለቅዱሳን የተሠሩ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ቅዱስ ስፍራዎች አሉ። ከእነዚህ ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች ቅዱስ ስፍራዎች የሚገኙት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ክስተቶች ወይም በቅርብ ዓመታት እንደተከናወኑ የሚነገሩ “ተአምራት” በተፈጸሙባቸው አሊያም ሃይማኖታዊ ቅርሶች በተቀመጡባቸው ቦታዎች ነው። ብዙ ሰዎች ወደነዚህ ቦታዎች የሚሄዱት፣ ጸሎታቸውን ቅዱስ በሆነ ስፍራ ቢያቀርቡ የበለጠ ተሰሚነት እንደሚኖራቸው ስለሚያምኑ ነው። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ለሃይማኖታቸው ማደራቸውን ለማሳየት ረጅም መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ ወደ ቅዱስ ስፍራዎች ይሄዳሉ።

ጃፓን የሚገኘውን ታላቁን የኢሴ ቅዱስ ስፍራ እንዲሁም በሉርድ፣ ፈረንሳይ ያለውን ግሮቶ ደ ማሳቤ ለማየት የሄዱ ጎብኚዎች

ይሁንና ሰዎች ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በቅዱስ ስፍራዎች ቢያቀርቡ ተሰሚነትና መልስ የማግኘት አጋጣሚያቸው ይጨምራል? አምላክ፣ ወደ ቅዱስ ስፍራዎች መንፈሳዊ ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች በሚያከናውኑት የአምልኮ ሥርዓት ይደሰት ይሆን? ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ጥያቄ ደግሞ፣ ክርስቲያኖች በቅዱስ ስፍራዎች ማምለክ ይኖርባቸዋል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ፣ በቅዱስ ስፍራዎች ለሚቀርብ አምልኮ ሊኖረን የሚገባውን አመለካከት የሚጠቁመን ከመሆኑም በላይ አምላክን የሚያስደስተው ምን ዓይነት አምልኮ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል።

“በመንፈስና በእውነት” ማምለክ

ኢየሱስ “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ እንዳለብን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር??

ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ጋር ያደረገው ውይይት፣ አምላክ በቅዱስ ስፍራዎች ስለሚቀርብ አምልኮ ያለውን አመለካከት ይጠቁመናል። ኢየሱስ ሰማርያን አቋርጦ እየተጓዘ ሳለ በሲካር ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ አለ። በዚያም ከጉድጓዱ ውኃ ልትቀዳ ከመጣች አንዲት ሴት ጋር ውይይት ጀመረ። በሚነጋገሩበት ጊዜ፣ ሴትየዋ በአይሁዳውያንና በሳምራውያን ሃይማኖት መካከል ስላለው ዋነኛ ልዩነት አነሳች። “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ አምልኳቸውን ያካሂዱ ነበር፤ እናንተ አይሁዳውያን ግን ሰዎች ማምለክ ያለባቸው በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” አለችው።—ዮሐንስ 4:5-9, 20

ሴትየዋ የጠቀሰችው ተራራ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የገሪዛን ተራራ ነው። በዚያ ተራራ ላይ ሳምራውያን እንደ ፋሲካ ያሉ በዓላትን የሚያከብሩበት ቤተ መቅደስ ነበራቸው። ኢየሱስ ግን በአይሁዳውያንና በሳምራውያን መካከል ባለው አወዛጋቢ ልዩነት ላይ ከማተኮር ይልቅ ለሴትየዋ “አንቺ ሴት፣ እመኚኝ፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም አብን የማታመልኩበት ሰዓት ይመጣል” አላት። (ዮሐንስ 4:21) እንዴት የሚያስገርም ሐሳብ ነው! በተለይ ደግሞ ተናጋሪው አይሁዳዊ መሆኑ ትኩረት ይስባል። ታዲያ ኢየሱስ፣ በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስ አምላክ የማይመለክበት ጊዜ እንደሚመጣ የተናገረው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ በመቀጠል “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ ምክንያቱም አብ እንዲያመልኩት የሚፈልገው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:23) አይሁዳውያን፣ በኢየሩሳሌም የነበረውን ዕፁብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ለብዙ መቶ ዓመታት የአምልኳቸው ማዕከል አድርገው ይመለከቱት ነበር። ለአምላካቸው ለይሖዋ መሥዋዕቶች ለማቅረብ በዓመት ሦስት ጊዜ ወደዚያ ይጓዙ ነበር። (ዘፀአት 23:14-17) ኢየሱስ ግን ይህ ሁሉ እንደሚቀርና “እውነተኛ አምላኪዎች . . . በመንፈስና በእውነት” እንደሚያመልኩ ተናገረ።

የአይሁዳውያን ቤተ መቅደስ፣ በአንድ ቦታ ላይ የተሠራ የሚታይ ሕንፃ ነበር። መንፈስና እውነት ግን እንደ ቤተ መቅደስ ግዑዝ ነገሮች ስላልሆኑ በአንድ የተወሰነ ስፍራ ሊቀመጡ አይችሉም። ስለዚህ ኢየሱስ፣ ክርስቲያኖች የሚያቀርቡት እውነተኛ አምልኮ ማንኛውንም ሕንፃ ወይም ቦታ ማዕከል ያደረገ እንዳልሆነና መከናወን ያለበት በአንድ ቦታ ብቻ አለመሆኑን እየገለጸ ነበር፤ እንዲህ ያለውን አምልኮ ለማቅረብ ወደ ገሪዛን ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ወደነበረው ቤተ መቅደስ ወይም ወደ የትኛውም ቅዱስ ቦታ መሄድ አያስፈልግም።

ኢየሱስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ለአምላክ ከሚቀርበው አምልኮ ጋር በተያያዘ ለውጥ የሚደረግበት ‘ሰዓት እንደሚመጣ’ ጠቅሶ ነበር። ለውጡ የተደረገው መቼ ነው? ይህ የሆነው ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ በመሞት፣ በሙሴ ሕግ ላይ የተመሠረተውን የአይሁዳውያንን የአምልኮ ሥርዓት ወደ ፍጻሜ ባመጣው ጊዜ ነበር። (ሮም 10:4) ሆኖም ኢየሱስ “ያም ሰዓት አሁን ነው” በማለትም ተናግሯል። እንዲህ ያለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ መሲሕ እንደመሆኑ መጠን ደቀ መዛሙርት መሰብሰብ ጀምሮ ነበር፤ ለእነዚህ ደቀ መዛሙርቱ “አምላክ መንፈስ ነው፤ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል” የሚለውን መመሪያ የሰጣቸው ሲሆን እነሱም ይህን መመሪያ ታዘዋል። (ዮሐንስ 4:24) ታዲያ በመንፈስና በእውነት ማምለክ ሲባል ምን ማለት ነው?

ኢየሱስ በመንፈስ ማምለክ ሲል፣ ሞቅ ባለ መንፈስና ግለት በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለሚቀርብ አምልኮ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ስለመመራት መናገሩ ነበር፤ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንድንረዳ ከሚያግዙን ነገሮች አንዱ ይህ መንፈስ ነው። (1 ቆሮንቶስ 2:9-12) ኢየሱስ የጠቀሰው እውነት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላሉት ትምህርቶች ትክክለኛ እውቀት ማግኘትን ያመለክታል። እንግዲያው አምልኳችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው ልዩ በሆነ ቦታ በመቅረቡ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ጋር የሚስማማና በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ በመሆኑ ነው።

ክርስቲያኖች ለቅዱስ ስፍራዎች ያላቸው አመለካከት

ክርስቲያኖች ወደ ቅዱስ ስፍራዎች ስለሚደረጉ መንፈሳዊ ጉዞዎችና በዚያ ስለሚከናወነው አምልኮ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ኢየሱስ እውነተኛ አምላኪዎች፣ አምላክን በመንፈስና በእውነት እንዲያመልኩት ያዘዘ ከመሆኑ አንጻር፣ ቅዱስ ተደርጎ በሚታይ በማንኛውም ስፍራ የሚቀርብ አምልኮ በሰማይ ባለው አባታችን ዘንድ የተለየ ቦታ እንደማይሰጠው ግልጽ ነው። በተጨማሪም አምላክ፣ ለጣዖቶች አምልኮ አከል ክብር ስለመስጠት ምን እንደሚሰማው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የአምላክ ቃል “ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” እንዲሁም “ከጣዖቶች ራቁ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 10:14፤ 1 ዮሐንስ 5:21) ስለሆነም አንድ እውነተኛ ክርስቲያን፣ ቅዱስ እንደሆነ ተደርጎ በሚታይ ወይም ጣዖት አምልኮን በሚያበረታታ ማንኛውም ስፍራ አምልኮ አያቀርብም። ቅዱስ ስለሚባሉ ስፍራዎች ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደዚህ ወዳሉ ስፍራዎች ለአምልኮ አይሄዱም።

ይህ ሲባል ግን የአምላክ ቃል ለጸሎት፣ ለጥናት ወይም ለማሰላሰል የሚያመቸንን ቦታ መምረጥን ያወግዛል ማለት አይደለም። ሥርዓታማ የሆነና ክብር ያለው የመሰብሰቢያ ቦታ መንፈሳዊ ነገሮችን ለመማርና ለመወያየት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ለሞተ ሰው መታሰቢያ እንዲሆን ሐውልት ማቆምም ቢሆን ስህተት አይደለም። ሰዎች ይህ የሚያደርጉት የሞተውን ሰው እንደሚያስታውሱት ወይም እንደሚወዱት ለመግለጽ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለውን ስፍራ እንደ ቅዱስ መቁጠር ወይም በዚያ ቦታ ምስሎች ወይም ቅርሶች አስቀምጦ ክብር መስጠት ኢየሱስ ከተናገረው ነገር ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው።

ስለዚህ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ብትጸልይ በአምላክ ዘንድ ይበልጥ ተሰሚነት እንደምታገኝ በማሰብ እንደነዚህ ወዳሉ ስፍራዎች መሄድ አያስፈልግህም። እንዲሁም ቅዱስ ወደሚባል ስፍራ መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግህ አምላክ እንደሚደሰትብህ ወይም ልዩ በረከት እንደሚሰጥህ መጠበቅ የለብህም። ይሖዋ አምላክ “የሰማይና የምድር ጌታ ስለሆነ በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ አይኖርም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እንዲህ ሲባል ግን ወደ አምላክ መቅረብ አንችልም ማለት አይደለም። “እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ” ስላልሆነ የትም ቦታ ሆነን ብንጸልይ ይሰማናል።—የሐዋርያት ሥራ 17:24-27.

^ አን.2 በሺንቶ ቅዱስ ስፍራዎች የሚፈጸሙት ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ሊለያዩ ይችላሉ።

^ አን.3 ቅዱስ ስፍራ የሚባለው ምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።