በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ቀውስ

ዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ቀውስ

“በአንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን ተቀምጬም እንኳ ያለምንም ምክንያት ሁልጊዜ ጭንቀት ይሰማኛል።”

“በጣም ስደሰት ስጋት ያድርብኛል። ምክንያቱም ስሜቴ በደስታ ወደ ላይ ከወጣ ወደ ታች ማሽቆልቆሉ እንደማይቀር አውቃለሁ።”

“ስለ ዛሬ ብቻ ለማሰብ ጥረት አደርጋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ግን የብዙ ቀን ጭንቀት ተደራርቦ ይመጣብኛል።”

እነዚህን ሐሳቦች የተናገሩት የአእምሮ ጤንነት እክል ያለባቸው ሰዎች ናቸው። አንተስ እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል? ወይም እንደዚህ የሚሰማው ሰው ታውቃለህ?

አይዞህ፣ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ከአእምሮ ጤና ችግር ጋር የሚታገሉ ወይም እንዲህ ያለ ችግር ያለበት የቤተሰብ አባል ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ።

የምንኖረው “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ስለሆነ ጭንቀት የሚፈጥሩ ብዙ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አንድ ጥናት እንደገለጸው በዓለም ዙሪያ ከስምንት ሰዎች አንዱ የአእምሮ ጤና መቃወስ ያጋጥመዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ በ2020 በጭንቀት የሚዋጡ ሰዎች ቁጥር በ26 በመቶ፣ በከባድ ድባቴ የሚሠቃዩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በ28 በመቶ ጨምሯል።

ይሁንና በዋነኝነት የሚያሳስበን ከአእምሮ ጤንነት ጋር በተያያዘ የሚጠቀሰው አኃዝ አይደለም። ዋናው ነገር፣ እኛም ሆንን ወዳጅ ዘመዶቻችን ይህን ችግር ማሸነፍ የምንችልበትን መንገድ ማወቃችን ነው።

የአእምሮ ጤንነት ምንድን ነው?

የአእምሮ ጤንነቱ የተጠበቀ ሰው በአብዛኛው ጥሩ ስሜት ይሰማዋል፤ እንዲሁም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በአግባቡ ማከናወን ይችላል። ውጥረት የሚፈጥሩ ነገሮችን መቋቋም፣ ፍሬያማ ሥራ መሥራት እንዲሁም በሕይወቱ እርካታ ማግኘት ይችላል።

የአእምሮ ጤንነት መቃወስ . . .

  • የድክመት ምልክት አይደለም።

  • ከፍተኛ ጭንቀት የሚፈጥር እንዲሁም የግለሰቡን አስተሳሰብ፣ ስሜትን የመቆጣጠር ችሎታና ባሕርይ የሚነካ የጤና እክል ነው።

  • ግለሰቡ ከሌሎች ጋር ያለውን ዝምድና ሊያበላሽበትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቹን ማከናወን እንዲከብደው ሊያደርግ ይችላል።

  • የትኛውም ባሕል፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ የትምህርት ደረጃ ወይም የኑሮ ደረጃ ያላቸውን በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች ሊነካ ይችላል።

ለአእምሮ ጤንነት ቀውስ እርዳታ ማግኘት

አንተም ሆንክ ጓደኛህ ወይም የቤተሰብህ አባል ጉልህ የባሕርይ ለውጥ፣ የእንቅልፍ ችግር ወይም የአመጋገብ ልማድ ለውጥ አሊያም ደግሞ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጭንቀት፣ ውጥረት ወይም ሐዘን ካጋጠማችሁ የችግሩን መንስኤ ለማወቅና ሕክምና ለማግኘት የባለሙያ እርዳታ መጠየቅ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። ይሁንና እርዳታ ማግኘት የምትችሉት ከየት ነው?

በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ ጥበበኛ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ብሏል። (ማቴዎስ 9:12) አስፈላጊውን ሕክምና እና መድኃኒት የሚወስዱ ታማሚዎች ከሚያታግላቸው የስሜት ቀውስ እፎይታ ማግኘትና ፍሬያማ የሆነ ሕይወት መምራት ይችላሉ። እንዲህ ያሉት ሰዎች ያደረባቸው የስሜት ቀውስ ከባድ ከሆነ ወይም ለረጅም ጊዜ ከዘለቀ ዛሬ ነገ ሳይሉ የሕክምና እርዳታ ማግኘታቸው ጥበብ ይሆናል። a

መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም በውስጡ ያለው ሐሳብ ለአእምሮ ጤንነታችን ሊጠቅመን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከአእምሮ ጤንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ እንመለከታለን። እነዚህን ምክሮች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

a መጠበቂያ ግንብ አንድን የሕክምና ዓይነት ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል።