መጸለይህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
ከባድ የጤና ችግር ያጋጠማት ፓሜላ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት ታደርግ ነበር። በተጨማሪም አምላክ ያለችበትን ከባድ ሁኔታ ለመወጣት ጥንካሬ እንዲሰጣት ትጸልይ ነበር። ታዲያ መጸለይዋ የረዳት እንዴት ነው?
ፓሜላ እንዲህ ብላለች፦ “የካንሰር ሕክምና በሚደረግልኝ ወቅት ብዙ ጊዜ ውስጤ በፍርሃት ይርድ ነበር። ወደ ይሖዋ ስጸልይ ግን የመረጋጋት ስሜት ስለሚሰማኝ አጥርቼ ማሰብ እችላለሁ። አሁንም ቢሆን ነጋ ጠባ ከሚያሠቃየኝ ሕመም ጋር እየታገልኩ ቢሆንም ጸሎት አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ይረዳኛል። ሰዎች ስለ ደህንነቴ ሲጠይቁኝ ‘ሕመሙ እንዳለ ቢሆንም ደስተኛ ነኝ!’ እላቸዋለሁ።”
እርግጥ ወደ አምላክ ለመጸለይ ከባድ ሕመም እስኪይዘን መጠበቅ አያስፈልገንም። ይነስም ይብዛ ሁላችንም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙን እነዚህን ሁኔታዎች ለመወጣት እርዳታ ያስፈልገናል። ታዲያ ጸሎት በዚህ ረገድ ሊረዳን ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም” ይላል። (መዝሙር 55:22) ይህ ሐሳብ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ለመሆኑ ጸሎት የሚጠቅምህ እንዴት ነው? በተገቢው መንገድ ወደ አምላክ ከጸለይክ ያጋጠመህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስፈልግህን ነገር ይሰጥሃል።—“ ጸሎት ምን ለማግኘት ያስችልሃል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።