በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ሕይወት የመረረውና ዓመፀኛ ሰው ነበርኩ

ሕይወት የመረረውና ዓመፀኛ ሰው ነበርኩ
  • የትውልድ ዘመን፦ 1974

  • የትውልድ አገር፦ ሜክሲኮ

  • የኋላ ታሪክ፦ በጉርምስና ዕድሜው ዓመፀኛና ተደባዳቢ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት ሜክሲኮ ውስጥ በታማውሊፓስ ግዛት በምትገኘው ስዩታት ማንቴ በተባለች ውብ ከተማ ነው። በጥቅሉ ሲታይ የከተማዋ ነዋሪዎች ለጋስና ደጎች ናቸው። የሚያሳዝነው ግን በከተማዋ ውስጥ የተደራጁ ወንጀለኞች ስለነበሩ አካባቢው በጣም አደገኛ ነበር።

በቤተሰባችን ውስጥ ያለነው አራት ወንዶች ልጆች ስንሆን እኔ ሁለተኛ ልጅ ነኝ። ወላጆቼ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስጠምቀውኛል፣ እንዲሁም ከጊዜ በኋላ የደብሩ መዘምራን አባል ሆኜ ነበር። አምላክን ማስደሰት እፈልግ ነበር፤ ምክንያቱም ለዘላለም በገሃነመ እሳት መቃጠል የሚለው ሐሳብ ያስፈራኝ ነበር።

አምስት ዓመት ሲሞላኝ አባታችን ጥሎን ሄደ። ይህም ክፉኛ አሳዘነኝ እንዲሁም የባዶነት ስሜት እንዲያድርብኝ አደረገ። አባቴ፣ እኛ በጣም እየወደድነው ለምን ጥሎን እንደሄደ ሊገባኝ አልቻለም። እናቴ አራታችንንም ለማሳደግ ከቤት ውጪ ረጅም ሰዓት መሥራት ግድ ሆኖባት ነበር።

ይህም ከትምህርት ቤት ቀርቼ በዕድሜ ከሚበልጡኝ ልጆች ጋር ለመዋል አጋጣሚ ከፈተልኝ። እነሱም መሳደብ፣ ማጨስ፣ መስረቅና መደባደብ አስተማሩኝ። በሌሎች ላይ የበላይ መሆን እወድ ስለነበረ ቡጢ፣ ትግል እና ማርሻል አርት እንዲሁም የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ተማርኩኝ። ዓመፀኛ ወጣት ሆንኩ። አብዛኛውን ጊዜ እንታኮስ የነበረ ሲሆን ደም በደም ሆኜ መንገድ ላይ ወድቄ ሲያዩኝ የሞትኩ መስሏቸው ትተውኝ የሄዱበት ጊዜ ነበር። እናቴ እንዲህ ሆኜ ስታየኝና በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ስትወስደኝ ልቧ ምን ያህል በሐዘን ሊሰበር እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

አሥራ ስድስት ዓመት ሲሞላኝ ጆርጅ የሚባል አንድ የልጅነት ጓደኛዬ ቤታችን መጣ። የይሖዋ ምሥክር እንደሆነና ጠቃሚ መልእክት ሊያካፍለን እንደሚፈልግ ነገረን። ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ የሚያምንበትን ነገር ማስረዳት ጀመረ። ከዚያ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ አንብቤ አላውቅም፤ ሆኖም ስለ አምላክ ስምና ስለ ዓላማው ስሰማ በጣም ተደሰትኩ። ጆርጅ መጽሐፍ ቅዱስ እንድናጠና ግብዣ አቀረበልን። እኛም ግብዣውን ተቀበልን።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በገሃነመ እሳት መቃጠል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዳልሆነ ሳውቅ ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5) ይህን ካወቅሁ በኋላ አምላክ ያቃጥለኛል ብዬ መፍራት አቆምኩ። ከዚህ ይልቅ ለልጆቹ ከሁሉ የተሻለውን እንደሚመኝ አፍቃሪ አባት አድርጌ እመለከተው ጀመር።

 በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ እየገፋሁ ስሄድ የባሕርይ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። ትሕትናን ማዳበርና ዓመፅን እንደ መፍትሔ አድርጌ ማየትን ማቆም ነበረብኝ። በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ የሚገኘው ምክር በጣም ጠቅሞኛል። ጥቅሱ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ይላል፤ የግርጌ ማስታወሻው ደግሞ “ጥሩውን ሥነ ምግባር” እንደሚያበላሽ ይናገራል። ስለዚህ ባሕርዬን ለመለወጥ መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብኝ ሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቋረጥ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። በመሆኑም የቀድሞ ጓደኞቼን ትቼ በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ወዳጆችን አፈራሁ፤ እነዚህ ሰዎች ልዩነቶቻቸውን የሚፈቱት በኃይል ወይም በዓመፅ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ በማዋል ነው።

ባሕርዬን እንድለውጥ የረዳኝ ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ደግሞ ሮም 12:17-19 ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ይሖዋ።” ይሖዋ እሱ ራሱ በፈለገው መንገድና በወሰነው ጊዜ የፍትሕ መዛባትን እንደሚያስወግድ አምኜ ተቀበልኩ። ቀስ በቀስ የዓመፀኝነት ባሕርዬን አሸነፍኩ።

አንድ ቀን አመሻሹ ላይ ወደ ቤት ስመለስ ያጋጠመኝን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም። ዓመፀኛ በነበርኩበት ወቅት ተቀናቃኛችን የነበረ ቡድን አባላት ጥቃት አደረሱብኝ፤ የቡድኑ መሪ “ራስህን ተከላከል!” እያለ ጀርባዬን ይደበድበኝ ነበር። በዚያው ቅጽበት ወደ ይሖዋ አጭር ጸሎት በማቅረብ ሁኔታውን ለመቋቋም እንዲረዳኝ ለመንኩት። ሲመቱኝ መልሼ ለመማታት በጣም የተፈተንኩ ቢሆንም እንደምንም ብዬ ትቻቸው ሄድኩኝ። በማግስቱ የቡድኑን መሪ ብቻውን አገኘሁት። ሳየው ብድሬን ለመመለስ ብገፋፋም ራሴን ለመቆጣጠር እንዲረዳኝ በድጋሚ ይሖዋን ለመንኩት። የሚገርመው ወጣቱ ቀጥ ብሎ ወደ እኔ መጣና “ትናንትና ማታ ለተፈጸመው ነገር ይቅርታ አድርግልኝ። እውነቱን ልንገርህ፣ እኔም እንዳንተ መሆን ብችል ደስ ይለኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እፈልጋለሁ” አለኝ። ቁጣዬን መቆጣጠር በመቻሌ በጣም ተደሰትኩ! በመሆኑም ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን።

የሚያሳዝነው ግን የቤተሰቤ አባላት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውን አቆሙ። እኔ ግን ጥናቴን ለመቀጠልና ምንም ነገር ቢያጋጥመኝ ወደኋላ ላለማለት ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር። አዘውትሬ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በመሆን ስሜታዊ ቁስሌ እንደሚፈወስና የሚያስፈልገኝን የቤተሰብ ፍቅር እንደማገኝ አውቄ ነበር። እድገት ማድረጌን በመቀጠል በ1991 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦

ሕይወት የመረረኝ፣ አምባገነንና ዓመፀኛ ነበርኩ። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለወጠው። አሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሰላም መልእክት መስማት ለሚፈልግ ሰው ሁሉ እናገራለሁ። ላለፉት 23 ዓመታት በሙሉ ጊዜዬ አምላክን የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

በሜክሲኮ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኜ ለተወሰነ ጊዜ ሠርቼ ነበር። እዚያ እያለሁ ክላውዲያ ከምትባል አንዲት ጎበዝ ወጣት ጋር ተዋወቅሁ፤ ከዚያም በ1999 ተጋባን። ይሖዋ ይህቺን ታማኝ የትዳር ጓደኛ በመስጠት ስለባረከኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ!

ከክላውዲያ ጋር በሜክሲኮ በሚገኝ አንድ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ ሆነን መስማት የተሳናቸው ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ስንረዳ ነበር። ከጊዜ በኋላ ወደ ቤሊዝ ተዛውረን በዚያ ያሉ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እንድናስተምር ተጋበዝን። አሁን የምንመራው ሕይወት ቀላል ቢሆንም ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ አሉን። ይህንን በምንም ነገር መለወጥ አንፈልግም።

ከጊዜ በኋላ እናቴ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን ቀጥላ ተጠመቀች። እንዲሁም ታላቅ ወንድሜ፣ ሚስቱና ልጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። በተጨማሪም የመንግሥቱን ምሥራች ከነገርኳቸው የቀድሞ ጓደኞቼ መካከል አንዳንዶቹ ይሖዋን እያገለገሉ ነው።

የሚያሳዝነው አንዳንድ የቤተሰቤ አባላት የዓመፀኝነት ባሕርያቸውን ለመተው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል። እኔም በዚያው ጎዳና ቀጥዬ ቢሆን ኖሮ መጨረሻዬ ከዚህ የተለየ አይሆንም ነበር። ይሖዋ ወደ ራሱ ስለሳበኝ እንዲሁም አገልጋዮቹ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ሥራ ላይ እንዳውል በትዕግሥትና በደግነት ስለረዱኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።