በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትንና ሞትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወትና ስለ ሞት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወትና ስለ ሞት ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን እንዲህ ሲል እንዳዘዘው ይናገራል፦ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ። ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ግን አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይህ ጥቅስ በግልጽ እንደሚያሳየው አዳም የአምላክን ትእዛዝ ቢያከብር ኖሮ አይሞትም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ በኤደን ገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ይችል ነበር።

የሚያሳዝነው ግን አዳም የአምላክን ትእዛዝ ችላ በማለት ሚስቱ ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ እንዲበላ ያቀረበችለትን ግብዣ ተቀበለ። (ዘፍጥረት 3:1-6) አዳም አለመታዘዙ ያስከተለው መዘዝ ለእኛም ተርፏል። ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) እዚህ ጥቅስ ላይ “አንድ ሰው” የተባለው አዳም ነው። ለመሆኑ አዳም የሠራው ኃጢአት ምን ነበር? ሞት ያስከተለበትስ ለምንድን ነው?

አዳም ያደረገው ነገር ማለትም የአምላክን ሕግ ሆን ብሎ መጣሱ ወይም አለመታዘዙ ኃጢአት ነው። (1 ዮሐንስ 3:4) አምላክ ለአዳም እንደገለጸለት ኃጢአት የሞት ቅጣት ያስከትላል። አዳምም ሆነ ዘሮቹ አምላክን እስከታዘዙ ድረስ ለኃጢአትና ለሞት አይዳረጉም ነበር። አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው እንዲሞቱ ሳይሆን ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘ሞት ለሰው ሁሉ እንደተዳረሰ’ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከሞትን በኋላ ከእኛ ተለይታ በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ነገር አለች? ብዙዎች ለዚህ ጥያቄ አዎ የሚል መልስ ይሰጣሉ፤ የማትሞት ነፍስ በውስጣችን አለች ብለው ያምናሉ። ይህ ግን አምላክ አዳምን ዋሽቶታል ብሎ እንደመናገር የሚቆጠር ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በውስጡ ያለች አንዲት ረቂቅ ነገር በሌላ ዓለም በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ከሆነ አምላክ እንደተናገረው ሞት ለኃጢአት ቅጣት አይሆንም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ሊዋሽ [አይችልም]” ይላል። (ዕብራውያን 6:18) እንዲያውም ሔዋንን “አትሞቱም” በማለት የዋሸው ሰይጣን ነበር።—ዘፍጥረት 3:4

ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በውሸት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ሠራው፤ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውየውም ሕያው ሰው ሆነ።” “ሕያው ሰው” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ነፈሽ * የሚል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “የሚተነፍስ ፍጥረት” ማለት ነው።—ዘፍጥረት 2:7 የግርጌ ማስታወሻ

ከዚህ መመልከት እንደምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ ሰው የማትሞት ነፍስ እንዳለችው አይናገርም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ግለሰብ “ሕያው ሰው” ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስናገላብጥ ብንውል “የማትሞት ነፍስ” የሚል አገላለጽ አናገኝም።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው የማትሞት ነፍስ እንዳለችው የማይናገር ከሆነ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ነፍስ አትሞትም ብለው የሚያስተምሩት ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የጥንቶቹ ግብፃውያን የነበራቸውን እምነት እንመርምር።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት ተስፋፋ

በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ሄሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ “ነፍስ አትሞትም ብለው ማስተማር የጀመሩት” ግብፃውያን እንደነበሩ ተናግሯል። የጥንቶቹ ባቢሎናውያንም ነፍስ አትሞትም ብለው ያምኑ ነበር። ታላቁ እስክንድር በ332 ዓ.ዓ. መካከለኛውን ምሥራቅ በተቆጣጠረበት ወቅት ግሪካውያን ፈላስፎች ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርገው ነበር፤ በመሆኑም ይህ ትምህርት በመላው የግሪክ ግዛት በፍጥነት ተስፋፋ።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የማትሞት ነፍስ” የሚል አገላለጽ አይገኝም

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ኤሴናውያን እና ፈሪሳውያን የሚባሉ ሁለት የአይሁድ እምነት ኑፋቄዎች ‘ሰው ሲሞት ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች’ ብለው ያስተምሩ ነበር። ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “አይሁዳውያን ነፍስ አትሞትም ብለው ማመን የጀመሩት የግሪካውያን አስተሳሰብ በተለይ ደግሞ የፕላቶ ፍልስፍና ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ነው።” በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስም ይህ ትምህርት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሳይሆን ‘የአፈ ታሪክና የተረቶች ስብስብ’ ብሎ በጠራው “የግሪክ ልጆች እምነት” ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጿል።

የግሪካውያን አስተሳሰብ እየተስፋፋ ሲሄድ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችም ይህን የአረማውያን ትምህርት ተቀበሉ። ታሪክ ጸሐፊው ዮና ሌንደሪንግ እንደገለጹት ከሆነ “ነፍሳችን በአንድ ወቅት በተሻለ ቦታ ትኖር እንደነበረ፣ አሁን ግን ኃጢአተኛ በሆነ ዓለም ውስጥ እንደምትኖር የሚገልጸው የፕላቶ ግምታዊ ሐሳብ ክርስቲያኖች የእሱን ፍልስፍና በቀላሉ እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል።” በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያን ነፍስ አትሞትም የሚለውን የአረማውያን ትምህርት የተቀበለች ሲሆን ውሎ አድሮ ይህ እምነት ከዋነኞቹ የክርስትና ትምህርቶች አንዱ ሆነ።

‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፦ “በመንፈስ መሪነት የተነገረው ቃል በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች ከመናፍስት ለሚመነጩ አሳሳች ቃሎችና ለአጋንንት ትምህርቶች ጆሯቸውን በመስጠት ከእምነት መውጣታቸው እንደማይቀር በግልጽ ይናገራል።” (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑ በግልጽ ታይቷል። ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ‘ከአጋንንት ትምህርቶች’ አንዱ ነው። ይህ ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሌለው ሲሆን ከጥንቶቹ አረማዊ ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች የመነጨ ነው።

ደስ የሚለው ነገር ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:32) የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን አብዛኞቹ የዓለም ሃይማኖቶች ከሚያስፋፏቸው አምላክን የሚያዋርዱ ትምህርቶችና ልማዶች ነፃ እንድንወጣ አስችሎናል። ከዚህም በላይ በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው እውነት ከሞት ጋር በተያያዘ ሰዎች ከሚከተሏቸው ልማዶችና አጉል እምነቶች ነፃ ያወጣናል።—“ ሙታን የት ናቸው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በምድር ላይ 70 ወይም 80 ዓመት ብቻ ከኖሩ በኋላ ወደ ሌላ ዓለም ተሸጋግረው ለዘላለም እንዲኖሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የእሱ ታዛዥ ልጆች ሆነው እዚሁ ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ በማሰብ ነው። ይህ ታላቅ ዓላማ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር መግለጫ ሲሆን ዓላማው መፈጸሙ አይቀርም። (ሚልክያስ 3:6) መዝሙራዊው “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት በመንፈስ መሪነት የተናገረው ሐሳብ የሚያጽናና ነው።—መዝሙር 37:29

 

^ አን.9 ነፈሽ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል የ1954 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እና አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ሕያው ነፍስ” በማለት የተረጎሙት ሲሆን የ1980 ትርጉም ደግሞ “ሕይወት ያለው ፍጡር” ብሎ ተርጉሞታል።