ሁለተኛ ዜና መዋዕል 6:1-42
6 በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል።+
2 አሁን እኔ እጅግ ከፍ ያለ ቤት፣ ለዘላለም የምትኖርበት ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ ገንብቼልሃለሁ።”+
3 ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ቆሞ ሳለ ንጉሡ ዞሮ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መባረክ ጀመረ።+
4 እንዲህም አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ እንዲህ ብሎ ቃል የገባውና ይህን በራሱ እጆች የፈጸመው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ፦
5 ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንስቶ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስሜ የሚጠራበት ቤት እንዲሠራበት አንድም ከተማ አልመረጥኩም፤+ ደግሞም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ እንዲሆን ማንንም አልመረጥኩም።
6 ሆኖም ስሜ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን፣+ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ገዢ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ።’+
7 አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት ከልቡ ተመኝቶ ነበር።+
8 ሆኖም ይሖዋ አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት ከልብህ ተመኝተህ ነበር፤ ይህን በልብህ መመኘትህም መልካም ነው።
9 ይሁንና ቤቱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ሆኖም ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ የሚወለድልህ የገዛ ልጅህ* ይሆናል።’+
10 ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል፤ ልክ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት+ አባቴን ዳዊትን ተክቼ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁና።+ በተጨማሪም ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ሠርቻለሁ፤
11 በዚያም ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት+ አስቀምጫለሁ።”
12 ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ መሠዊያ ፊት፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ዘረጋ።+
13 (ሰለሞን የመዳብ መድረክ ሠርቶ በግቢው መካከል አስቀምጦ ነበር።+ የመድረኩ ርዝመት አምስት ክንድ፣* ወርዱ አምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበር፤ እሱም በመድረኩ ላይ ቆሞ ነበር።) በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮም እጆቹን ወደ ሰማያት ዘረጋ፤+
14 እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በፊቱ በሙሉ ልባቸው ለሚመላለሱ አገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ አምላክ በሰማያትም ሆነ በምድር የለም።+
15 ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቀሃል።+ በገዛ አፍህ ቃል ገባህ፤ ዛሬ ደግሞ በራስህ እጅ ፈጸምከው።+
16 አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ ‘አንተ በፊቴ እንደተመላለስከው ሁሉ+ ልጆችህም በጥንቃቄ ሕጌን ጠብቀው ከተመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከፊቴ አይታጣም’+ በማለት ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቅ።
17 አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ለአገልጋይህ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም።
18 “በእርግጥ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በምድር ላይ ይኖራል?+ እነሆ ሰማያት፣ አዎ ሰማየ ሰማያት እንኳ ሊይዙህ አይችሉም፤+ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤትማ ምንኛ ያንስ!+
19 እንግዲህ አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመና በትኩረት ስማ፤ አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰማውን ጩኸትና በፊትህ የሚያቀርበውን ጸሎት አዳምጥ።
20 አገልጋይህ ወደዚህ ስፍራ የሚያቀርበውን ጸሎት ለመስማት ስምህ እንደሚጠራበት+ ወደተናገርከው ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ሌሊትና ቀን ይመልከቱ።
21 አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመናና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸልይበት ጊዜ+ የሚያቀርበውን ልመና አዳምጥ፤ በማደሪያህም በሰማያት ሆነህ ስማ፤+ ሰምተህም ይቅር በል።+
22 “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ እንዲምል ቢደረግ፣* በመሐላውም* ተጠያቂ ቢሆን፣ በዳዩም በዚህ መሐላ* ሥር ሆኖ እዚህ ቤት ውስጥ ባለው መሠዊያህ ፊት ቢቀርብ፣+
23 አንተ በሰማያት ሆነህ ስማ፤ ለክፉው እንደ ሥራው በመመለስና+ የእጁን እንዲያገኝ በማድረግ፣ ጻድቁንም ንጹሕ* መሆኑን በማሳወቅና እንደ ጽድቁ ወሮታውን በመክፈል+ እርምጃ ውሰድ፤ አገልጋዮችህንም ዳኝ።
24 “ሕዝብህ እስራኤላውያን አንተን ከመበደላቸው የተነሳ በጠላት ድል ቢነሱና+ ተመልሰው ስምህን ቢያወድሱ+ እንዲሁም በዚህ ቤት በፊትህ ቢጸልዩና+ ሞገስ ለማግኘት ልመና ቢያቀርቡ+
25 ከሰማያት ሆነህ ስማ፤+ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነሱና ለአባቶቻቸው ወደሰጠኸው ምድርም መልሳቸው።+
26 “ሕዝቡ አንተን በመበደሉ የተነሳ+ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ቢጠፋ፣+ እነሱም አንተ ስላዋረድካቸው* ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢያወድሱ እንዲሁም ከኃጢአታቸው ቢመለሱ+
27 ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የአገልጋዮችህን፣ የሕዝብህን የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር በል፤ ስለሚሄዱበት ቀና መንገድ ታስተምራቸዋለህና፤+ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ ባወረስከው ምድርህም ላይ ዝናብ አዝንብ።+
28 “በምድሪቱ ላይ ረሃብ+ ወይም ቸነፈር፣+ የሚለበልብና የሚያደርቅ ነፋስ ወይም ዋግ+ ቢከሰት፣ የአንበጣ መንጋ ወይም የማይጠግብ አንበጣ*+ ቢመጣ አሊያም ጠላቶቻቸው በምድሪቱ ላይ ባለ በየትኛውም ከተማ* ውስጥ ሳሉ ቢከቧቸው+ ወይም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት አሊያም ማንኛውም ዓይነት በሽታ ቢከሰትና+
29 ማንኛውም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል በሙሉ (እያንዳንዱ የገዛ ጭንቀቱንና ሥቃዩን ያውቃልና)+ ወደ አንተ ለመጸለይ+ ወይም ሞገስ እንድታሳየው ልመና ለማቅረብ+ እጁን ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ+
30 አንተ ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤+ ደግሞም ይቅር በል፤+ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ብድራቱን ክፈለው፤ ምክንያቱም አንተ ልቡን ታውቃለህ (የሰውን ልብ በሚገባ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ)፤+
31 ይህም ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ በመንገዶችህ በመመላለስ አንተን እንዲፈሩ ነው።
32 “በተጨማሪም ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ የባዕድ አገር ሰው ከታላቁ ስምህ፣* ከኃያሉ እጅህና ከተዘረጋው ክንድህ የተነሳ ከሩቅ አገር ቢመጣ፣+ ወደዚህም ቤት መጥቶ ቢጸልይ፣+
33 ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ስምህን እንዲያውቁና+ እንዲፈሩህ እንዲሁም ስምህ እኔ በሠራሁት በዚህ ቤት እንደሚጠራ እንዲያውቁ ያ የባዕድ አገር ሰው የጠየቀህን ሁሉ ፈጽምለት።
34 “ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ለጦርነት ቢወጡና+ አንተ ወደመረጥከው ወደዚህ ከተማ እንዲሁም ለስምህ ወደሠራሁት ቤት አቅጣጫ+ ቢጸልዩ+
35 ከሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና ስማ፤ ፍረድላቸውም።+
36 “በአንተ ላይ ኃጢአት ቢሠሩ (መቼም ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለም)፣+ አንተም በእነሱ እጅግ ተቆጥተህ ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ ጠላቶቻቸውም ራቅ ወዳለ ወይም ቅርብ ወደሆነ ምድር ምርኮኛ አድርገው ቢወስዷቸው፣+
37 እነሱም በምርኮ በተወሰዱበት ምድር ወደ ልቦናቸው ቢመለሱና ወደ አንተ ዞር በማለት ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ አጥፍተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ በማለት በተማረኩበት ምድር ሆነው ሞገስ ለማግኘት ወደ አንተ ልመና ቢያቀርቡ፣+
38 ደግሞም ተማርከው በተወሰዱበት፣ ምርኮኛ ሆነው በሚኖሩበት ምድር፣+ በሙሉ ልባቸውና+ በሙሉ ነፍሳቸው* ወደ አንተ ቢመለሱ እንዲሁም ለአባቶቻቸው በሰጠሃቸው ምድር፣ አንተ በመረጥካት ከተማና ለስምህ በሠራሁት ቤት አቅጣጫ ቢጸልዩ፣+
39 ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት ያቀረቡትን ልመና ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ ፍረድላቸውም፤+ በአንተ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሕዝብህን ይቅር በል።
40 “አሁንም አምላኬ ሆይ፣ እባክህ በዚህ ቦታ* ወደቀረበው ጸሎት ዓይኖችህ ይመልከቱ፤ ጆሮዎችህም በትኩረት ያዳምጡ።+
41 አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ከብርታትህ ታቦት ጋር ወደ ማረፊያ ቦታህ+ ውጣ። ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ካህናትህ መዳንን ይልበሱ፤ ታማኞችህም በጥሩነትህ ሐሴት ያድርጉ።+
42 ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ የቀባኸውን ሰው ገሸሽ አታድርግ።*+ ለአገልጋይህ ለዳዊት ያሳየኸውን ታማኝ ፍቅር አስብ።”+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “ከወገብህ የሚወጣው ወንድ ልጅህ።”
^ ወይም “ባልንጀራው በእርግማን ሥር ቢያደርገው።” ግለሰቡ የማለው በውሸት ከሆነ ወይም መሐላውን ከጣሰ እርግማኑ እንደ ቅጣት እንደሚደርስበት ያመለክታል።
^ ቃል በቃል “በእርግማኑም።”
^ ቃል በቃል “እርግማን።”
^ ቃል በቃል “ጻድቅ።”
^ ወይም “ስላጎሳቆልካቸው።”
^ ቃል በቃል “በበሮቹ ምድር።”
^ ወይም “ፌንጣ።”
^ ወይም “ዝናህ።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ከዚህ ቦታ ጋር በተያያዘ።”
^ ቃል በቃል “ፊት አትመልስ።”