ሁለተኛ ዜና መዋዕል 1:1-17
1 የዳዊት ልጅ ሰለሞን ንግሥናውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ ሄደ፤ አምላኩ ይሖዋም ከእሱ ጋር ስለነበር እጅግ ገናና አደረገው።+
2 ሰለሞን ለእስራኤል ሁሉ፣ ለሺህ አለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለፈራጆችና የአባቶች ቤቶች መሪዎች ለሆኑት በመላው እስራኤል ለሚገኙት አለቆች ሁሉ መልእክት ላከ።
3 ከዚያም ሰለሞንና መላው ጉባኤ በገባኦን+ ወደሚገኘው ኮረብታ ሄዱ፤ ምክንያቱም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእውነተኛው አምላክ የመገናኛ ድንኳን የሚገኘው በዚያ ነበር።
4 ይሁን እንጂ ዳዊት የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከቂርያትየአሪም+ እሱ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ድንኳን ተክሎለት ነበር።+
5 የሁር ልጅ የዖሪ ልጅ ባስልኤል+ የሠራው የመዳብ መሠዊያ+ በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊት ይገኝ ነበር፤ ሰለሞንና ጉባኤውም በመሠዊያው ፊት ይጸልዩ ነበር።*
6 ሰለሞንም በዚያ በይሖዋ ፊት መባ አቀረበ፤ በመገናኛው ድንኳን በሚገኘው የመዳብ መሠዊያ ላይ 1,000 የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረበ።+
7 በዚያ ሌሊት አምላክ ለሰለሞን ተገልጦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው።+
8 በዚህ ጊዜ ሰለሞን አምላክን እንዲህ አለው፦ “ለአባቴ ለዳዊት ጥልቅ የሆነ ታማኝ ፍቅር አሳይተኸዋል፤+ በእሱም ምትክ አንግሠኸኛል።+
9 አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም፤+ እንደ ምድር አፈር እጅግ ብዙ በሆነ ሕዝብ+ ላይ አንግሠኸኛልና።
10 ይህን ሕዝብ መምራት* እንድችል ጥበብና እውቀት ስጠኝ፤+ አለዚያማ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊዳኝ ይችላል?”+
11 ከዚያም አምላክ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “የልብህ መሻት ይህ ስለሆነ ደግሞም ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር ወይም የሚጠሉህን ሰዎች ሞት* አሊያም ረጅም ዕድሜ* ስላልተመኘህ፣ ይልቁንም አንተን ንጉሥ አድርጌ የሾምኩበትን ሕዝቤን ማስተዳደር እንድትችል ጥበብና እውቀት ስለጠየቅክ፣+
12 ጥበብና እውቀት ይሰጥሃል፤ ከዚህም ሌላ ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተም በኋላ የሚነሳ የትኛውም ንጉሥ የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።”+
13 ሰለሞንም በገባኦን+ ኮረብታ ከሚገኘው ከመገናኛው ድንኳን ፊት ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።
14 ሰለሞን ሠረገሎችንና ፈረሶችን* መሰብሰቡን ቀጠለ፤ እሱም 1,400 ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች* ነበሩት፤+ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና+ በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።+
15 ንጉሡ ብርና ወርቅ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ እስኪሆን ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲበዛ አደረገ፤+ አርዘ ሊባኖሱንም ከብዛቱ የተነሳ በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።+
16 የሰለሞን ፈረሶች ከግብፅ ያስመጣቸው ነበሩ፤+ የንጉሡ ነጋዴዎችም የፈረሶቹን መንጋ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዙ ነበር።*+
17 ከግብፅ የሚመጣው እያንዳንዱ ሠረገላ 600 የብር ሰቅል ያወጣ ነበር፤ አንድ ፈረስ ደግሞ 150 ሰቅል ያወጣል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለሂታውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይሸጡ ነበር።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “በዚያ አምላክን ይጠይቁ ነበር።”
^ ቃል በቃል “በዚህ ሕዝብ ፊት መውጣትና መግባት።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ቃል በቃል “ብዙ ቀናት።”
^ ወይም “ፈረሰኞችን።”
^ ወይም “ፈረሰኞች።”
^ “ከግብፅና ከቀዌ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎች ከቀዌ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዟቸው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቀዌ ኪልቅያን ልታመለክት ትችላለች።