ሁለተኛ ነገሥት 14:1-29

  • አሜስያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-6)

  • ከኤዶምና ከእስራኤል ጋር የተደረገ ውጊያ (7-14)

  • የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ሞተ (15, 16)

  • አሜስያስ ሞተ (17-22)

  • ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል ላይ ነገሠ (23-29)

14  የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ+ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ።  አሜስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ የሆዓዲን የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች።+  እሱም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ባይሆንም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ፈጸመ።+ ሁሉንም ነገር አባቱ ኢዮዓስ እንዳደረገው አደረገ።+  ሆኖም ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤+ ሕዝቡ አሁንም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ ይሠዋ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።+  እሱም መንግሥቱ በእጁ እንደጸናለት፣ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን አገልጋዮቹን+ ገደላቸው።  ይሁንና “አባቶች በልጆቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ልጆችም በአባቶቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ይልቁንም እያንዳንዱ ሰው በገዛ ኃጢአቱ ይገደል”+ በሚለው በሙሴ የሕግ መጽሐፍ ላይ በተጻፈው የይሖዋ ትእዛዝ መሠረት የገዳዮቹን ልጆች አልገደላቸውም።  እሱም 10,000 ኤዶማውያንን+ በጨው ሸለቆ+ መታ፤ ተዋግቶም ሴላን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ፤+ እሷም እስከ ዛሬ ድረስ ዮቅተኤል ተብላ ትጠራለች።  ከዚያም አሜስያስ የእስራኤል ንጉሥ ወደሆነው ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮዓካዝ ልጅ ወደ ኢዮዓስ “ና፤ ውጊያ እንግጠም”* በማለት መልእክተኞች ላከ።+  የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ደግሞ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ይህን መልእክት ላከ፦ “በሊባኖስ የሚገኘው ኩርንችት በሊባኖስ ወደሚገኘው አርዘ ሊባኖስ ‘ሴት ልጅህን ለወንድ ልጄ ዳርለት’ የሚል መልእክት ላከ። ይሁን እንጂ በሊባኖስ የነበረ አንድ የዱር አውሬ በዚያ ሲያልፍ ያን ኩርንችት ረገጠው። 10  እርግጥ ኤዶምን መተሃል፤+ በመሆኑም ልብህ ታብዮአል። ክብርህን ጠብቀህ አርፈህ ቤትህ* ተቀመጥ። በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ትጋብዛለህ? ደግሞስ ራስህንም ሆነ ይሁዳን ለምን ለውድቀት ትዳርጋለህ?” 11  አሜስያስ ግን አልሰማም።+ በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ወጣ፤ እሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ በምትገኘው በቤትሼሜሽ+ ተጋጠሙ።+ 12  ይሁዳ በእስራኤል ድል ተመታ፤ እያንዳንዳቸውም ወደየቤታቸው* ሸሹ። 13  የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ የአካዝያስ ልጅ፣ የኢዮዓስ ልጅ የሆነውን የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሼሜሽ ላይ ያዘው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ እሱም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ከኤፍሬም በር+ አንስቶ እስከ ማዕዘን በር+ ድረስ አፈረሰ፤ ርዝመቱም 400 ክንድ* ያህል ነበር። 14  በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች የተገኘውን ወርቅ፣ ብርና ዕቃ ሁሉ እንዲሁም የታገቱትን ሰዎች ወሰደ። ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 15  የቀረው የኢዮዓስ ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮችና ኃያልነቱ እንዲሁም ከይሁዳ ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንዴት እንደተዋጋ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 16  በመጨረሻም ኢዮዓስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ጋር በሰማርያ ተቀበረ፤+ ልጁም ኢዮርብዓም*+ በእሱ ምትክ ነገሠ። 17  የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ+ ከሞተ በኋላ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ+ 15 ዓመት ኖረ።+ 18  የቀረው የአሜስያስ ታሪክ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኝ የለም? 19  ከጊዜ በኋላ ኢየሩሳሌም ውስጥ በእሱ ላይ ሴራ ተጠነሰሰ፤+ እሱም ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ እነሱ ግን ተከታትለው እንዲይዙት ሰዎችን ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 20  ከዚያም በፈረሶች ላይ ጭነው አመጡት፤ እሱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም ተቀበረ።+ 21  ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ በወቅቱ የ16 ዓመት+ ልጅ የነበረውን አዛርያስን*+ ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ምትክ አነገሡት።+ 22  እሱም፣ ንጉሡ* ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን+ መልሶ በመገንባት ወደ ይሁዳ መለሳት።+ 23  የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ በነገሠ በ15ኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ ኢዮርብዓም+ በሰማርያ ነገሠ፤ እሱም 41 ዓመት ገዛ። 24  በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ካደረጋቸው ኃጢአት ሁሉ ዞር አላለም።+ 25  የእስራኤል አምላክ ይሖዋ የጋትሔፌር+ ነቢይ በሆነው በአሚታይ ልጅ፣ በአገልጋዩ በዮናስ+ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ከሌቦሃማት*+ አንስቶ እስከ አረባ ባሕር*+ ድረስ ያለውን የእስራኤልን ወሰን አስመለሰ። 26  ይሖዋ በእስራኤል ላይ እየደረሰ ያለውን ከባድ ሥቃይ ተመልክቶ ነበርና።+ በዚያም እስራኤልን ሌላው ቀርቶ ምስኪኑንና ደካማውን የሚረዳ አልነበረም። 27  ሆኖም ይሖዋ የእስራኤልን ስም ከሰማይ በታች ጠራርጎ እንደማያጠፋ ቃል ገብቶ ነበር።+ በመሆኑም በኢዮዓስ ልጅ በኢዮርብዓም አማካኝነት አዳናቸው።+ 28  የቀረው የኢዮርብዓም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉና ኃያልነቱ እንዲሁም እንዴት እንደተዋጋ ብሎም ደማስቆንና ሃማትን+ ለይሁዳና ለእስራኤል እንዴት እንዳስመለሰ+ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 29  በመጨረሻም ኢዮርብዓም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያስ+ በእሱ ምትክ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ፊት ለፊት እንገናኝ።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ቃል በቃል “ወደየድንኳናቸው።”
ወደ 178 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ዳግማዊ ኢዮርብዓምን የሚያመለክት ነው።
“ይሖዋ ረዳ” የሚል ትርጉም አለው። በ2ነገ 15:13፣ 2ዜና 26:1-23፣ ኢሳ 6:1 እና ዘካ 14:5 ላይ ዖዝያ ተብሎም ተጠርቷል።
አባቱን አሜስያስን ያመለክታል።
ወይም “ከሃማት መግቢያ።”
ጨው ባሕርን ወይም ሙት ባሕርን ያመለክታል።