ሁለተኛ ሳሙኤል 9:1-13

  • ዳዊት ለሜፊቦስቴ ታማኝ ፍቅር አሳየው (1-13)

9  ከዚያም ዳዊት “ለመሆኑ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለ።+  በዚህ ጊዜ የሳኦል ቤት አገልጋይ የሆነ ሲባ+ የሚባል ሰው ነበር። እሱንም ወደ ዳዊት እንዲመጣ ጠሩት፤ ንጉሡም “ሲባ የምትባለው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም “አዎ፣ እኔ አገልጋይህ ሲባ ነኝ” በማለት መለሰ።  ከዚያም ንጉሡ “እንደው የአምላክን ታማኝ ፍቅር ላሳየው የምችል ከሳኦል ቤት የቀረ ሰው ይኖራል?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሁለቱም እግሮቹ ሽባ+ የሆኑ አንድ የዮናታን ልጅ አለ” አለው።  ንጉሡም “ለመሆኑ የት ነው ያለው?” አለው። ሲባም ንጉሡን “ሎደባር ባለው በአሚዔል ልጅ በማኪር+ ቤት ይገኛል” አለው።  ንጉሥ ዳዊትም ወዲያውኑ መልእክተኞችን ልኮ ሎደባር ከሚገኘው ከአሚዔል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው።  የሳኦል ልጅ፣ የዮናታን ልጅ ሜፊቦስቴ ወደ ዳዊት ሲገባ ወዲያውኑ በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ። ከዚያም ዳዊት “ሜፊቦስቴ!” ብሎ ጠራው፤ እሱም “አቤት ጌታዬ” አለ።  ዳዊትም “ለአባትህ ለዮናታን ስል ታማኝ ፍቅር ስለማሳይህ አትፍራ፤+ የአያትህን የሳኦልንም መሬት በሙሉ እመልስልሃለሁ፤ አንተም ዘወትር ከማዕዴ ትበላለህ”+ አለው።  እሱም ከሰገደ በኋላ “እንደ እኔ ላለ የሞተ ውሻ+ ሞገስ ታሳይ ዘንድ ለመሆኑ እኔ አገልጋይህ ማን ነኝ?” አለው።  ከዚያም ንጉሡ ለሳኦል አገልጋይ ለሲባ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ “የሳኦልና የቤተሰቡ የሆነውን ነገር ሁሉ ለጌታህ የልጅ ልጅ ሰጥቼዋለሁ።+ 10  አንተ፣ ልጆችህና አገልጋዮችህ መሬቱን ታርሱለታላችሁ፤ ምርቱንም ታስገቡለታላችሁ፤ ይህም ለጌታህ የልጅ ልጅ ቤተሰቦች መብል ይሆናል። የጌታህ የልጅ ልጅ ሜፊቦስቴ ግን ዘወትር ከማዕዴ ይመገባል።”+ ሲባ 15 ልጆችና 20 አገልጋዮች ነበሩት።+ 11  ከዚያም ሲባ ንጉሡን “እኔ አገልጋይህ፣ ጌታዬ ንጉሡ ያዘዘኝን ሁሉ እፈጽማለሁ” አለው። ስለዚህ ሜፊቦስቴ ከንጉሡ ልጆች እንደ አንዱ ከዳዊት* ማዕድ በላ። 12  ሜፊቦስቴም ሚካ+ የሚባል ትንሽ ልጅ ነበረው፤ በሲባ ቤት የሚኖሩም ሁሉ የሜፊቦስቴ አገልጋዮች ሆኑ። 13  ሜፊቦስቴም ዘወትር ከንጉሡ ማዕድ ይበላ+ ስለነበር የሚኖረው በኢየሩሳሌም ነበር፤ ሁለቱም እግሮቹ ሽባ ነበሩ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ከእኔ” ማለትም ሊሆን ይችላል።