ሁለተኛ ሳሙኤል 4:1-12

  • ኢያቡስቴ ተገደለ (1-8)

  • ዳዊት የኢያቡስቴን ገዳዮች አስገደላቸው (9-12)

4  የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ፣*+ አበኔር በኬብሮን መሞቱን+ ሲሰማ ወኔ ከዳው፤* እስራኤላውያንም በሙሉ ተረበሹ። 2  የሳኦል ልጅ የሚመራቸው ወራሪ ቡድኖች አለቃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ የአንደኛው ስም ባአናህ ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሬካብ ነበር። እነሱም ከቢንያም ነገድ የሆነው የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ነበሩ። (ምክንያቱም በኤሮት+ ከቢንያም ወገን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። 3  በኤሮታውያን ወደ ጊታይም+ ሸሹ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ የባዕድ አገር ሰው ሆነው ይኖራሉ።) 4  የሳኦል ልጅ ዮናታን+ እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው።+ እሱም ስለ ሳኦልና ስለ ዮናታን የሚገልጸው ወሬ ከኢይዝራኤል+ በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበር፤ ሞግዚቱም አንስታው መሸሽ ጀመረች፤ ሆኖም በድንጋጤ ሸሽታ ስትሮጥ ከእጇ ላይ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜፊቦስቴ+ ነበር። 5  የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ሬካብ እና ባአናህ ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ወደ ኢያቡስቴ ቤት ሄዱ፤ እሱም ቀትር ላይ አረፍ ብሎ ነበር። 6  እነሱም ስንዴ የሚወስዱ ሰዎች መስለው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቀው ገቡ፤ ኢያቡስቴንም ሆዱ ላይ ወጉት፤ ከዚያም ሬካብ እና ወንድሙ ባአናህ+ ሸሽተው አመለጡ። 7  ወደ ቤት ሲገቡ ኢያቡስቴ መኝታ ቤቱ ውስጥ አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ነበር፤ እነሱም መትተው ገደሉት፤ ከዚያም ራሱን ቆርጠው በመውሰድ ወደ አረባ በሚወስደው መንገድ ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ አደሩ። 8  የኢያቡስቴንም+ ራስ በኬብሮን ወዳለው ወደ ዳዊት አምጥተው ንጉሡን “ሕይወትህን* ሲፈልጋት+ የነበረው የጠላትህ+ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ። ይሖዋ በዛሬው ዕለት ሳኦልንና ዘሮቹን ለጌታዬ ለንጉሡ ተበቀለለት” አሉት። 9  ሆኖም ዳዊት ለበኤሮታዊው ለሪሞን ልጆች ለሬካብ እና ለወንድሙ ለባአናህ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሕይወቴን ከመከራ ሁሉ በታደገልኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ 10  አንድ ሰው ምሥራች ያበሰረኝ መስሎት ‘ሳኦል እኮ ሞተ’+ ብሎ በነገረኝ ጊዜ ጺቅላግ ላይ ገደልኩት።+ መልእክተኛው ከእኔ ያገኘው ሽልማት ይህ ነበር! 11  ታዲያ በገዛ ቤቱ አልጋው ላይ ተኝቶ የነበረውን ጻድቅ ሰው የገደሉ ክፉ ሰዎችማ እንዴት ከዚህ የባሰ ነገር አይጠብቃቸው! እና አሁን ደሙን ከእጃችሁ መጠየቅም+ ሆነ እናንተን ከምድር ገጽ ማጥፋት አይገባኝም?” 12  ከዚያም ዳዊት እንዲገድሏቸው ለወጣቶቹ ትእዛዝ ሰጠ።+ እነሱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ቆርጠው በኬብሮን በሚገኘው ኩሬ አጠገብ ሰቀሏቸው።+ የኢያቡስቴን ራስ ግን ወስደው በኬብሮን ባለው በአበኔር የመቃብር ቦታ ቀበሩት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የሳኦል ወንድ ልጅ።”
ቃል በቃል “እጆቹ ዛሉ።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ በተቤዠልኝ።”