ሁለተኛ ሳሙኤል 20:1-26

  • ሳባ ዓመፀ፤ ኢዮዓብ አሜሳይን ገደለው (1-13)

  • ሳባን አሳደው ደረሱበት፤ እንዲሁም ተገደለ (14-22)

  • የዳዊት አስተዳደር (23-26)

20  በዚህ ጊዜ የቢንያማዊው የቢክሪ ልጅ የሆነ ሳባ+ የሚባል አንድ አስቸጋሪ ሰው ነበር። እሱም ቀንደ መለከት በመንፋት+ “እኛ ከዳዊት ጋር ምንም ድርሻ የለንም፤ ከእሴይም ልጅ ጋር ምንም ውርሻ የለንም።+ እስራኤል ሆይ፣ እያንዳንድህ ወደ አማልክትህ* ተመለስ!” አለ።+  ስለዚህ የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ዳዊትን መከተል ትተው የቢክሪን ልጅ ሳባን መከተል ጀመሩ፤+ የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ አንስቶ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ከንጉሣቸው አልተለዩም።+  ዳዊት በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤቱ*+ ሲመጣ ንጉሡ ቤቱን እንዲጠብቁ ትቷቸው ሄዶ የነበሩትን አሥሩን ቁባቶቹን+ ወስዶ በዘብ በሚጠበቅ አንድ ቤት ውስጥ አስገባቸው። በየጊዜው ቀለብ ይሰጣቸው የነበረ ቢሆንም ከእነሱ ጋር ምንም ግንኙነት አልፈጸመም።+ እነሱም ባላቸው በሕይወት ያለ ቢሆንም እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ እንደ መበለት ሆነው ኖሩ።  ንጉሡም አሜሳይን+ “የይሁዳን ሰዎች በሦስት ቀን ውስጥ ጠርተህ ወደ እኔ ሰብስብልኝ፤ አንተም እዚህ መገኘት ይኖርብሃል” አለው።  ስለዚህ አሜሳይ የይሁዳን ሕዝብ ለመሰብሰብ ሄደ፤ ሆኖም ንጉሡ ከቀጠረለት ጊዜ ዘገየ።  ከዚያም ዳዊት አቢሳን+ “ከአቢሴሎም ይልቅ የቢክሪ ልጅ ሳባ+ የከፋ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል።+ ስለሆነም የተመሸጉ ከተሞች አግኝቶ እንዳያመልጠን የጌታህን አገልጋዮች ይዘህ አሳደው” አለው።  በመሆኑም የኢዮዓብ+ ሰዎች፣ ከሪታውያን፣ ጴሌታውያን+ እና ኃያላን የሆኑት ሰዎች በሙሉ ተከትለውት ሄዱ፤ የቢክሪን ልጅ ሳባን ለማሳደድም ከኢየሩሳሌም ወጡ።  እነሱም በገባኦን+ በሚገኘው ትልቅ ድንጋይ አጠገብ ሲደርሱ አሜሳይ+ ሊገናኛቸው መጣ። ኢዮዓብ የጦር ልብሱን ለብሶ፣ ወገቡም ላይ ሰይፉን ከነሰገባው ታጥቆ ነበር። ወደ ፊት ራመድ ሲልም ሰይፉ ከሰገባው ወደቀ።  ኢዮዓብም አሜሳይን “ወንድሜ ሆይ፣ ደህና ነህ?” አለው። ከዚያም ኢዮዓብ የሚስመው አስመስሎ በቀኝ እጁ የአሜሳይን ጢም ያዘ። 10  አሜሳይ፣ በኢዮዓብ እጅ ከነበረው ሰይፍ ራሱን አልጠበቀም፤ ኢዮዓብም በሰይፉ ሆዱ ላይ ወጋው፤+ አንጀቱም መሬት ላይ ተዘረገፈ። ዳግመኛ መውጋት እንኳ ሳያስፈልገው አንዴ ብቻ ወግቶ ገደለው። ከዚያም ኢዮዓብና ወንድሙ አቢሳ የቢክሪን ልጅ ሳባን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ። 11  ከኢዮዓብ ወጣቶች መካከል አንዱ አሜሳይ አጠገብ ቆሞ “ከኢዮዓብ ጎን የሚቆምና የዳዊት የሆነ ማንኛውም ሰው ኢዮዓብን ይከተል!” ይል ነበር። 12  በዚህ ጊዜ አሜሳይ መንገዱ መሃል ላይ በደም ተጨማልቆ ይንፈራገጥ ነበር። ሰውየውም ሰዉ ሁሉ እዚያ ሲደርስ እንደሚቆም ሲያይ አሜሳይን ከመንገዱ ላይ ወደ ሜዳው ገለል አደረገው። ይሁንና ሰዉ ሁሉ አሁንም እሱ ጋ ሲደርስ እንደሚቆም ሲያይ ልብስ ጣል አደረገበት። 13  አሜሳይን ከመንገዱ ላይ ካነሳው በኋላ ሰዉ ሁሉ የቢክሪን ልጅ ሳባን+ ለማሳደድ ኢዮዓብን ተከትሎ ሄደ። 14  ሳባም የእስራኤልን ነገዶች በሙሉ አልፎ ወደ ቤትማዓካዋ አቤል+ ሄደ። ቢክሪያውያንም ተሰብስበው ተከተሉት። 15  ኢዮዓብና ሰዎቹም* መጥተው ሳባን በቤትማዓካዋ አቤል እንዳለ ከበቡት፤ በከተማዋም ዙሪያ የአፈር ቁልል ደለደሉ፤ ከተማዋም በአፈር ቁልሉ መሃል ነበረች። ከኢዮዓብም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ የከተማዋን ቅጥር ለመጣል ከሥሩ ይሰረስሩ ነበር። 16  ከከተማዋም ውስጥ አንዲት ብልህ ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ስሙ፣ እናንተ ሰዎች ስሙ! እባካችሁ ኢዮዓብን ‘ወደዚህ ቅረብና ላነጋግርህ’ በሉት” አለች። 17  እሱም ወደ እሷ ቀረበ፤ ከዚያም ሴትየዋ “ኢዮዓብ አንተ ነህ?” አለችው፤ እሱም “አዎ፣ እኔ ነኝ” አላት። በዚህ ጊዜ “አገልጋይህ የምትልህን ስማ” አለችው። እሱም መልሶ “እሺ እየሰማሁ ነው” አላት። 18  እሷም እንዲህ አለች፦ “ቀደም ባሉት ጊዜያት ሰዎች ‘በአቤል ከተማ ይጠይቁ፤ ጉዳያቸውም እልባት ያገኛል’ ይሉ ነበር። 19  እኔ የእስራኤልን ሰላማዊና ታማኝ ሰዎች እወክላለሁ። አንተ በእስራኤል ውስጥ እንደ እናት የሆነችን ከተማ ልትደመስስ ትፈልጋለህ። የይሖዋን ውርሻ የምታጠፋው* ለምንድን ነው?”+ 20  ኢዮዓብም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ከተማዋን ማጥፋትም ሆነ መደምሰስ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው። 21  ነገሩ እንደዚያ አይደለም። ሆኖም ከኤፍሬም ተራራማ አካባቢ+ የመጣውና የቢክሪ ልጅ የሆነው ሳባ+ በንጉሥ ዳዊት ላይ ዓምፆአል።* ይህን ሰው አሳልፋችሁ ከሰጣችሁኝ ከተማዋን ትቼ እሄዳለሁ።” ከዚያም ሴትየዋ ኢዮዓብን “እንግዲህ የሰውየው ራስ በቅጥሩ ላይ ይወረወርልሃል!” አለችው። 22  ብልህ የሆነችው ሴትም ወዲያውኑ ወደ ሕዝቡ ሄደች፤ እነሱም የቢክሪን ልጅ የሳባን ራስ ቆርጠው ለኢዮዓብ ወረወሩለት። በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ ቀንደ መለከት ነፋ፤ እነሱም ከተማዋን ትተው በየአቅጣጫው ተበታተኑ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደቤቱ ሄደ፤+ ኢዮዓብም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ንጉሡ ተመለሰ። 23  ኢዮዓብ የመላው የእስራኤል ሠራዊት አዛዥ ነበር፤+ የዮዳሄ+ ልጅ በናያህ+ ደግሞ በከሪታውያንና በጴሌታውያን+ ላይ የበላይ ነበር። 24  አዶራም+ የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ በተመለመሉት ላይ የበላይ ነበር፤ የአሂሉድ ልጅ ኢዮሳፍጥ+ ደግሞ ታሪክ ጸሐፊ ነበር። 25  ሻዌ ጸሐፊ ነበር፤ ሳዶቅና+ አብያታር+ ደግሞ ካህናት ነበሩ። 26  በተጨማሪም ያኢራዊው ኢራ ዋና ኃላፊ* ሆኖ ዳዊትን ያገለግል ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ወደየድንኳንህ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቤተ መንግሥቱ።”
ቃል በቃል “እነሱም።”
ቃል በቃል “የምትውጠው።”
ቃል በቃል “እጁን አንስቷል።”
ቃል በቃል “ካህን።”