ሁለተኛ ሳሙኤል 18:1-33

  • አቢሴሎም ለሽንፈትና ለሞት ተዳረገ (1-18)

  • ዳዊት፣ አቢሴሎም መሞቱ ተነገረው (19-33)

18  ከዚያም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቆጠረ፤ በእነሱም ላይ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች ሾመ።+  በተጨማሪም ዳዊት ከሰዎቹ መካከል አንድ ሦስተኛውን በኢዮዓብ+ አመራር* ሥር፣ አንድ ሦስተኛውን ደግሞ የኢዮዓብ ወንድም በሆነው በጽሩያ+ ልጅ በአቢሳ+ አመራር ሥር እንዲሁም አንድ ሦስተኛውን በጌታዊው በኢታይ+ አመራር ሥር አድርጎ ላከ። ንጉሡም ሰዎቹን “እኔም አብሬያችሁ እወጣለሁ” አላቸው።  እነሱ ግን እንዲህ አሉት፦ “አንተማ መውጣት የለብህም፤+ ለመሸሽ ብንገደድ እንኳ እነሱ ስለ እኛ ደንታ አይሰጣቸውም፤* ግማሾቻችን ብንሞትም ግድ የላቸውም፤ ምክንያቱም አንተ ከእኛ ከአሥሩ ሺህ ትበልጣለህ።+ ስለዚህ ከተማው ውስጥ ሆነህ ድጋፍ ብትሰጠን ይሻላል።”  ንጉሡም “እሺ፣ እናንተ የተሻለ ነው ያላችሁትን አደርጋለሁ” አላቸው። በመሆኑም ንጉሡ በከተማዋ በር አጠገብ ቆመ፤ ሰዎቹም ሁሉ በመቶዎችና በሺዎች እየሆኑ ወጡ።  ንጉሡም ኢዮዓብን፣ አቢሳንና ኢታይን “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ በአቢሴሎም ላይ አትጨክኑበት” ሲል አዘዛቸው።+ ንጉሡ አቢሴሎምን አስመልክቶ ለአለቆቹ በሙሉ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰዎቹ ሁሉ ሰሙ።  ሰዎቹም ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ሜዳው ወጡ፤ ውጊያውም በኤፍሬም ጫካ ውስጥ ተካሄደ።+  በዚያም የእስራኤል ሰዎች+ በዳዊት አገልጋዮች ድል ተመቱ፤+ በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ከመካከላቸውም 20,000 ሰው ተገደለ።  ውጊያውም በአካባቢው ሁሉ ተዛመተ። በዚያን ቀን ሰይፍ ከበላው ይልቅ ጫካ የበላው ሰው በለጠ።  በኋላም አቢሴሎም ከዳዊት አገልጋዮች ጋር ድንገት ተገናኘ። አቢሴሎም በበቅሎ ላይ ተቀምጦ ይሄድ ነበር፤ በቅሎዋም ጥቅጥቅ ያለ ቅርንጫፍ ባለው አንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ስታልፍ ዛፉ የአቢሴሎምን ፀጉር ያዘው፤ በመሆኑም የተቀመጠባት በቅሎ ስታልፍ እሱ አየር ላይ* ተንጠልጥሎ ቀረ። 10  ከዚያም አንድ ሰው ይህን አይቶ ለኢዮዓብ+ “አቢሴሎምን አንድ ትልቅ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ አየሁት!” ብሎ ነገረው። 11  በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ ይህን የነገረውን ሰው “እና ካየኸው ያኔውኑ መትተህ መሬት ላይ ያልጣልከው ለምንድን ነው? እንዲህ ብታደርግ ኖሮ አሥር ሰቅል ብርና ቀበቶ እሸልምህ ነበር” አለው። 12  ሰውየው ግን ኢዮዓብን እንዲህ አለው፦ “1,000 የብር ሰቅል ቢሰጠኝ* እንኳ በንጉሡ ልጅ ላይ እጄን አላነሳም፤ ምክንያቱም ንጉሡ አንተን፣ አቢሳንና ኢታይን ‘ማናችሁም ብትሆኑ በወጣቱ በአቢሴሎም ላይ ጉዳት እንዳታደርሱበት ተጠንቀቁ’ ብሎ ሲያዛችሁ ሰምተናል።+ 13  ትእዛዙን በመተላለፍ የልጁን ሕይወት አጥፍቼ* ቢሆን ኖሮ ይህ ጉዳይ ከንጉሡ ተሰውሮ ሊቀር አይችልም ነበር፤ አንተም ብትሆን ልታስጥለኝ አትችልም።” 14  ኢዮዓብም “ከዚህ በላይ ከአንተ ጋር ጊዜ አላጠፋም!” አለው። ከዚያም ሦስት ቀስቶች* ይዞ በመሄድ አቢሴሎም በትልቁ ዛፍ መሃል ተንጠልጥሎ ገና በሕይወት እያለ ቀስቶቹን ልቡ ላይ ሰካቸው። 15  ከዚያም ከኢዮዓብ ጋሻ ጃግሬዎች አሥሩ መጥተው አቢሴሎምን መትተው ገደሉት።+ 16  ኢዮዓብም ቀንደ መለከት ነፋ፤ ሰዎቹም እስራኤላውያንን ከማሳደድ ተመለሱ፤ በዚህ መንገድ ኢዮዓብ ሰዎቹን አስቆማቸው። 17  እነሱም አቢሴሎምን ወስደው ጫካው ውስጥ በሚገኝ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ በላዩም ላይ በጣም ትልቅ የድንጋይ ቁልል ከመሩበት።+ እስራኤላውያንም በሙሉ ወደየቤታቸው ሸሹ። 18  አቢሴሎም በሕይወት ሳለ “ስሜ የሚታወስበት ልጅ የለኝም”+ በማለት በንጉሡ ሸለቆ*+ ለራሱ ዓምድ አቁሞ ነበር። ዓምዱንም በራሱ ስም ሰይሞት ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ የአቢሴሎም ሐውልት በመባል ይጠራል። 19  የሳዶቅ ልጅ አኪማዓስም+ “ይሖዋ ንጉሡን ከጠላቶቹ እጅ ነፃ በማውጣት ስለፈረደለት+ እባክህ እየሮጥኩ ሄጄ ወሬውን ልንገረው” አለ። 20  ኢዮዓብ ግን “ዛሬ ወሬውን የምትነግረው አንተ አይደለህም። ወሬውን ሌላ ቀን ትነግረዋለህ፤ የንጉሡ ልጅ ስለ ሞተ ዛሬ ወሬውን መናገር የለብህም” አለው።+ 21  ከዚያም ኢዮዓብ አንድ ኩሻዊ+ ጠርቶ “ሂድ፣ ያየኸውን ነገር ለንጉሡ ንገረው” አለው። በዚህ ጊዜ ኩሻዊው ለኢዮዓብ ከሰገደ በኋላ እየሮጠ ሄደ። 22  የሳዶቅ ልጅ አኪማዓስም እንደገና ኢዮዓብን “እባክህ፣ የመጣው ይምጣ እኔም ኩሻዊውን ተከትዬ ልሩጥ” አለው። ሆኖም ኢዮዓብ “ልጄ ሆይ፣ የምትናገረው ነገር ሳይኖር ለምን ትሮጣለህ?” አለው። 23  እሱ ግን አሁንም “ምንም ይሁን ምን፣ እባክህ ልሩጥ” አለው። ስለዚህ ኢዮዓብ “በቃ ሩጥ!” አለው። አኪማዓስም የዮርዳኖስን አውራጃ* አቋርጦ የሚያልፈውን መንገድ ይዞ መሮጥ ጀመረ፤ በኋላም ኩሻዊውን አልፎት ሄደ። 24  በዚህ ጊዜ ዳዊት በሁለቱ የከተማዋ በሮች+ መካከል ተቀምጦ ነበር፤ ጠባቂውም+ ከቅጥሩ ጋር ተያይዞ ወደተሠራው የበሩ ሰገነት ወጣ። ቀና ብሎም ሲመለከት ብቻውን የሚሮጥ አንድ ሰው አየ። 25  ጠባቂውም ተጣርቶ ይህንኑ ለንጉሡ ነገረው፤ ንጉሡም “ብቻውን ከሆነ ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። ሰውየውም እየቀረበ ሲመጣ 26  ጠባቂው ሌላ ሰው ሲሮጥ ተመለከተ። በመሆኑም የበር ጠባቂውን ተጣርቶ “ይኸው ሌላም ሰው ብቻውን እየሮጠ በመምጣት ላይ ነው!” አለው። ንጉሡም “ይህም ሰው ቢሆን ወሬ ይዞ የመጣ መሆን አለበት” አለ። 27  ጠባቂውም “የመጀመሪያው ሰው አሯሯጥ የሳዶቅን ልጅ የአኪማዓስን+ አሯሯጥ ይመስላል” አለ፤ በመሆኑም ንጉሡ “እሱማ ጥሩ ሰው ነው፤ ምሥራች ሳይዝ አይመጣም” አለው። 28  አኪማዓስም ንጉሡን ተጣርቶ “ሁሉም ነገር ሰላም ነው!” አለው። ከዚያም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ ሰገደ። ቀጥሎም “በጌታዬ በንጉሡ ላይ ያመፁትን* ሰዎች አሳልፎ የሰጠህ አምላክህ ይሖዋ ይወደስ!” አለ።+ 29  ሆኖም ንጉሡ “ለመሆኑ ወጣቱ አቢሴሎም ደህና ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ አኪማዓስ “ኢዮዓብ የንጉሡን አገልጋይና እኔን አገልጋይህን በላከ ጊዜ ከፍተኛ ትርምስ አይቻለሁ፤ ምን እንደሆነ ግን አላወቅኩም” አለ።+ 30  ንጉሡም “እሺ፣ እልፍ በልና እዚያ ቁም” አለው። እሱም እልፍ ብሎ ቆመ። 31  ከዚያም ኩሻዊው ደረሰ፤+ እሱም “ጌታዬ ንጉሡ፣ ያመጣሁትን ይህን ወሬ ይስማ፦ ዛሬ ይሖዋ፣ በአንተ ላይ ካመፁብህ ሰዎች ሁሉ እጅ ነፃ በማውጣት ፈርዶልሃል” አለ።+ 32  ይሁንና ንጉሡ ኩሻዊውን “ለመሆኑ ወጣቱ አቢሴሎም ደህና ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ ኩሻዊው “የጌታዬ የንጉሡ ጠላቶች ሁሉና በአንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ ያመፁብህ ሁሉ እንደዚያ ወጣት ይሁኑ!” አለ።+ 33  ይህም ንጉሡን ረበሸው፤ በውጭው በር ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍልም ወጥቶ አለቀሰ፤ ወዲያ ወዲህ እያለም “ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ፣ ልጄ አቢሴሎም! ምነው በአንተ ፋንታ እኔ በሞትኩ፤ ልጄ አቢሴሎም፣ ልጄ!” ይል ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “እጅ።”
ቃል በቃል “በእኛ ላይ ልባቸውን አያኖሩም።”
ቃል በቃል “በሰማይና በምድር መካከል።”
ቃል በቃል “መዳፎቼ ላይ ቢመዘንልኝ።”
ወይም “የልጁን ነፍስ ለማጥፋት ሴራ ጠንስሼ።”
“አነስተኛ ቀስቶች፤ ጦሮች” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “በትሮች።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “አውራጃውን።”
ቃል በቃል “እጃቸውን ያነሱትን።”