ሁለተኛ ሳሙኤል 17:1-29

  • ኩሲ የአኪጦፌልን ምክር ውድቅ አደረገ (1-14)

  • ዳዊት እንዲጠነቀቅ ተነገረው፤ ከአቢሴሎም አመለጠ (15-29)

    • ቤርዜሊና አብረውት ያሉት ሰዎች ለንጉሡ ስንቅ አቀበሉ (27-29)

17  ከዚያም አኪጦፌል አቢሴሎምን እንዲህ አለው፦ “እባክህ፣ 12,000 ሰዎች ልምረጥና ተነስቼ ዛሬ ማታ ዳዊትን ላሳደው።  በደከመውና አቅም ባጣ* ጊዜ ድንገት እደርስበታለሁ፤+ ሽብርም እለቅበታለሁ፤ አብረውት ያሉት ሰዎችም ሁሉ ይሸሻሉ፤ ንጉሡን ብቻ እመታለሁ።+  ከዚያም ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ። የሕዝቡ ሁሉ መመለስ የተመካው አንተ የምትፈልገው ሰው በሚደርስበት ነገር ላይ ነው። ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ሰላም ያገኛል።”  ይህ ሐሳብም በአቢሴሎምና በእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ ፊት መልካም ሆኖ ተገኘ።  ሆኖም አቢሴሎም “እስቲ አርካዊውን ኩሲን+ ጥሩትና እሱ ደግሞ የሚለውን እንስማ” አለ።  በመሆኑም ኩሲ ወደ አቢሴሎም ገባ። ከዚያም አቢሴሎም “አኪጦፌል እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል። ታዲያ እሱ እንዳለው እናድርግ? ካልሆነ የአንተን ሐሳብ ንገረን” አለው።  ኩሲም አቢሴሎምን “እዚህ ላይ እንኳ አኪጦፌል የሰጠው ምክር የሚያዋጣ አይደለም!” አለው።+  አክሎም ኩሲ እንዲህ አለ፦ “መቼም አባትህም ሆነ አብረውት ያሉት ሰዎች ኃያል ተዋጊዎችና+ በሜዳ እንዳለች ግልገሎቿን ያጣች ድብ+ ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ* መሆናቸውን በሚገባ ታውቃለህ። ደግሞም አባትህ ጦረኛ ነው፤+ ሌሊት ከሕዝቡ ጋር አያድርም።  ይህን ጊዜ እኮ አንድ ዋሻ* ውስጥ ወይም ሌላ ቦታ ተደብቋል፤+ እሱ ቀድሞ ጥቃት ከሰነዘረ ይህን የሰሙ ሁሉ ‘አቢሴሎምን የተከተሉት ሰዎች ድል ተመቱ!’ ብለው ያወራሉ። 10  ልቡ እንደ አንበሳ+ የሆነ ደፋር ሰው እንኳ በፍርሃት መራዱ አይቀርም፤ ምክንያቱም አባትህ ኃያል ተዋጊ፣ አብረውት ያሉትም ሰዎች ጀግኖች+ መሆናቸውን መላው እስራኤል ያውቃል። 11  እንግዲህ እኔ የምመክርህ ይህ ነው፦ ከብዛቱ የተነሳ በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ+ የሆነው ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ ያለው የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ወደ አንተ ይሰብሰብ፤ አንተ ራስህም እየመራህ ወደ ውጊያ ውሰዳቸው። 12  እኛም የገባበት ገብተን ጥቃት እንሰነዝርበታለን፤ በመሬት ላይ እንደሚወርድ ጤዛም እንወርድበታለን፤ እሱም ሆነ ከእሱ ጋር ያሉት ሰዎች አንዳቸውም አያመልጡም። 13  ወደ አንድ ከተማ ቢሸሽ እንኳ መላው እስራኤል ወደ ከተማዋ ገመድ ይዞ በመሄድ፣ ከተማዋን ጎትተን አንዲት ጠጠር ሳናስቀር ሸለቆ ውስጥ እንከታታለን።” 14  ከዚያም አቢሴሎምና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የአርካዊው የኩሲ ምክር ይሻላል!” አሉ።+ ምክንያቱም ይሖዋ በአቢሴሎም ላይ ጥፋት ለማምጣት ሲል ይሖዋ መልካም የሆነውን የአኪጦፌልን+ ምክር ለማክሸፍ ወስኖ* ነበር።+ 15  በኋላም ኩሲ ካህናት የሆኑትን ሳዶቅንና አብያታርን+ እንዲህ አላቸው፦ “አኪጦፌል እንዲህ እንዲህ በማለት አቢሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች መክሯቸው ነበር፤ እኔ ደግሞ እንዲህ እንዲህ ብዬ መክሬያቸዋለሁ። 16  አሁንም ለዳዊት ፈጥናችሁ መልእክት በመላክ እንዲህ ብላችሁ አስጠንቅቁት፦ ‘ዛሬ ሌሊት በምድረ በዳው ባሉት መልካዎች* እንዳታድር፤ የግድ መሻገር አለብህ፤ አለዚያ ንጉሡና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ያልቃል።’”*+ 17  ዮናታንና+ አኪማዓስም+ በኤንሮጌል+ ተቀምጠው ነበር፤ በመሆኑም አንዲት አገልጋይ ሄዳ መልእክቱን ነገረቻቸው፤ እነሱም ሁኔታውን ለንጉሥ ዳዊት ለመንገር ሄዱ። ምክንያቱም ወደ ከተማዋ ከገባን እንታያለን ብለው ፈርተው ነበር። 18  ይሁንና አንድ ወጣት አያቸውና ለአቢሴሎም ነገረው። ስለሆነም ሁለቱም በፍጥነት ከዚያ በመሄድ በባሁሪም+ ወደሚገኝ አንድ ሰው ቤት መጡ፤ እሱም ግቢው ውስጥ የውኃ ጉድጓድ ነበረው። እነሱም እዚያ ውስጥ ገቡ፤ 19  የሰውየውም ሚስት በጉድጓዱ አፍ ላይ ማስጫ ዘርግታ የተከካ እህል አሰጣችበት፤ ይህን ያወቀ ማንም ሰው አልነበረም። 20  የአቢሴሎም አገልጋዮችም ወደ ሴትየዋ ቤት መጥተው “አኪማዓስና ዮናታን የት አሉ?” አሏት። እሷም “በዚህ አልፈው ወደ ወንዙ ሄደዋል” አለቻቸው።+ ሰዎቹም ፍለጋቸውን ቀጠሉ፤ ሆኖም ሊያገኟቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 21  ሰዎቹ ከሄዱም በኋላ አኪማዓስና ዮናታን ከጉድጓዱ ወጥተው ወደ ንጉሥ ዳዊት በመሄድ “እናንተ ሰዎች፣ ተነስታችሁ በፍጥነት ወንዙን ተሻገሩ፤ ምክንያቱም አኪጦፌል ስለ እናንተ እንዲህ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቷል” አሉት።+ 22  ዳዊትና አብሮት የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወዲያውኑ ተነስተው ዮርዳኖስን ተሻገሩ። ጎህ ሲቀድም ዮርዳኖስን ሳይሻገር የቀረ አንድም ሰው አልነበረም። 23  አኪጦፌል፣ የሰጠው ምክር ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲያይ አህያውን ጭኖ በሚኖርባት ከተማ ወደሚገኘው ቤቱ ሄደ።+ ከዚያም ለቤተሰቡ አንዳንድ መመሪያዎችን ከሰጠ+ በኋላ ታንቆ ሞተ።+ በአባቶቹም የመቃብር ቦታ ተቀበረ። 24  ይህ በእንዲህ እንዳለ ዳዊት ወደ ማሃናይም+ ሄደ፤ አቢሴሎም ደግሞ ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ። 25  አቢሴሎም በኢዮዓብ+ ቦታ አሜሳይን+ በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ አሜሳይ የእስራኤላዊው የይትራ ልጅ ነበር፤ ይትራ የኢዮዓብ እናት ከሆነችው ከጽሩያ እህት ከአቢጋኤል+ ጋር ግንኙነት ነበረው፤ አቢጋኤል የናሃሽ ልጅ ነበረች። 26  እስራኤላውያንና አቢሴሎም በጊልያድ+ ምድር ሰፈሩ። 27  ዳዊት ማሃናይም ሲደርስ የአሞናውያን ከተማ ከሆነችው ከራባ+ የመጣው የናሃሽ ልጅ ሾባይ፣ ከሎደባር የመጣው የአሚዔል ልጅ ማኪርና+ ከሮገሊም የመጣው ጊልያዳዊው ቤርዜሊ+ 28  ለመኝታ የሚሆኑ ነገሮች፣ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ የሸክላ ዕቃዎች፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዱቄት፣ ቆሎ፣ ባቄላ፣ ምስር፣ የተጠበሰ እሸት፣ 29  ማር፣ ቅቤ፣ በግና አይብ* ይዘው መጡ። ይህን ሁሉ ይዘው የመጡት “መቼም ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቧል፣ ደክሟል፣ ተጠምቷል” ብለው በማሰብ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች እንዲበሉት ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እጆቹ በዛሉ።”
ወይም “በነፍሳቸው የተመረሩ።”
ወይም “ጉድጓድ፤ ገደል።”
ወይም “አዝዞ።”
ቃል በቃል “ይዋጣል።”
“በረሃማ ሜዳዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል። መልካ ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል ነው።
ቃል በቃል “የከብት እርጎ።”