ሁለተኛ ሳሙኤል 14:1-33

  • ኢዮዓብና ተቆአዊቷ ሴት (1-17)

  • ዳዊት ተቆአዊቷን ሴት የላካት ኢዮዓብ መሆኑን ደረሰበት (18-20)

  • አቢሴሎም ወደ ቤቱ እንዲመለስ ተፈቀደለት (21-33)

14  የጽሩያ+ ልጅ ኢዮዓብ የንጉሡ ልብ አቢሴሎምን እንደናፈቀ ተረዳ።+  በመሆኑም ኢዮአብ ወደ ተቆአ፣+ ሰው ልኮ አንዲት ብልህ ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፦ “እባክሽ፣ ሐዘንተኛ ምሰዪ፤ የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይትም አትቀቢ።+ ሰው ሞቶባት ለረጅም ጊዜ እንዳዘነች ሴት ሁኚ።  ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ በይው።” ከዚያም ኢዮዓብ ምን እንደምትል ነገራት።  ተቆአዊቷም ሴት ወደ ንጉሡ ከገባች በኋላ በግንባሯ ተደፍታ በመስገድ “ንጉሥ ሆይ፣ እርዳኝ!” አለች።  ንጉሡም “ምን ሆነሽ ነው?” አላት። እሷም እንዲህ አለችው፦ “እኔ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ።  እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ እነሱም ሜዳ ላይ ተደባደቡ። ገላጋይም ስላልነበረ አንደኛው ሌላኛውን መትቶ ገደለው።  በኋላም ቤተ ዘመድ ሁሉ በእኔ በአገልጋይህ ላይ ተነስቶ ‘ወራሹን ማጥፋት ቢሆንብንም እንኳ የወንድሙን ሕይወት* ስላጠፋ እሱን እንድንገድለው ገዳዩን አሳልፈሽ ስጪን’ ይለኝ ጀመር።+ በመሆኑም የቀረችኝን አንዲት ፍም* በማጥፋት ባሌን በምድር ላይ ያለስምና ያለዘር ሊያስቀሩት ነው።”  ከዚያም ንጉሡ ሴትየዋን “በቃ አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ የአንቺን ጉዳይ በተመለከተ ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት።  በዚህ ጊዜ ተቆአዊቷ ሴት ንጉሡን “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሐን ስለሆኑ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን” አለችው። 10  ከዚያም ንጉሡ “ከዚህ በኋላ ማንም ሰው ቢናገርሽ ወደ እኔ አምጪው፤ ዳግመኛም አያስቸግርሽም” አላት። 11  እሷ ግን “ደም ተበቃዩ+ በልጄ ላይ ጉዳት እንዳያደርስበትና እንዳይገድለው እባክህ ንጉሡ አምላኩን ይሖዋን ያስብ” አለችው። እሱም “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣+ ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ፀጉር እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አላት። 12  ሴትየዋም “እባክህ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድትናገር ፍቀድላት” አለች። እሱም “እሺ፣ ተናገሪ!” አላት። 13  ከዚያም ሴትየዋ እንዲህ አለች፦ “ታዲያ አንተ በአምላክ ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ለማድረግ ያሰብከው ለምንድን ነው?+ ንጉሡ የተሰደደውን የገዛ ልጁን ባለመመለሱ እንዲህ ብሎ ሲናገር ራሱን በደለኛ እያደረገ ነው።+ 14  ሁላችንም መሞታችን አይቀርም፤ የፈሰሰ ውኃ እንደማይታፈስ ሁሉ እኛም እንደዚሁ እንሆናለን። ሆኖም አምላክ ሕይወት* አያጠፋም፤ እንዲሁም የተሰደደ ሰው ከእሱ ርቆ በዚያው ተሰዶ እንዳይቀር እሱን ለመመለስ ምክንያት ይፈልጋል። 15  አሁንም ለጌታዬ ለንጉሡ ይህን ነገር ለመናገር የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ነው። በመሆኑም አገልጋይህ እንዲህ ብላ አሰበች፦ ‘እንግዲህ አሁን ንጉሡን ላነጋግረው። ምናልባትም ንጉሡ ባሪያው የጠየቀችውን ነገር ይፈጽምላት ይሆናል። 16  ንጉሡ ቃሌን ሰምቶ እኔንም ሆነ አንድ ልጄን አምላክ ከሰጠን ርስት ላይ ሊያጠፋን ከሚፈልገው ሰው እጅ ባሪያውን ይታደጋት ይሆናል።’+ 17  ከዚያም አገልጋይህ ‘የጌታዬ የንጉሡ ቃል እረፍት ይስጠኝ’ አለች፤ ምክንያቱም ጌታዬ ንጉሡ ጥሩውን ከመጥፎው በመለየት ረገድ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ነው። አምላክህ ይሖዋም ከአንተ ጋር ይሁን።” 18  ንጉሡም መልሶ ሴትየዋን “እባክሽ፣ የምጠይቅሽን ነገር አንድም ሳትደብቂ ንገሪኝ” አላት። ሴትየዋም “እሺ፣ ንጉሡ ጌታዬ ይናገር” አለች። 19  ከዚያም ንጉሡ “በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ የኢዮዓብ እጅ አለበት?” ሲል ጠየቃት።+ ሴትየዋም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ ጌታዬ ንጉሡ እንደተናገረው ነው፤* ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና አገልጋይህ የተናገረችውን ነገር ሁሉ የነገራት አገልጋይህ ኢዮዓብ ነው። 20  አገልጋይህ ኢዮዓብ ይህን ያደረገው ሁኔታውን ለመለወጥ ሲል ነው፤ ሆኖም ጌታዬ እንደ እውነተኛው አምላክ መልአክ ዓይነት ጥበብ አለው፤ በምድሪቱ ላይ የሚከናወነውንም ነገር ሁሉ ያውቃል።” 21  ከዚያም ንጉሡ ኢዮዓብን “እሺ፣ ይህን አደርጋለሁ።+ በል ሂድና ወጣቱን አቢሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።+ 22  በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ በመስገድ ንጉሡን አመሰገነ። ከዚያም “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ንጉሡ አገልጋዩ የጠየቀውን ነገር ስለፈጸመለት ዛሬ እኔ አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘሁ አወቅኩ” አለ። 23  ኢዮዓብም ተነስቶ ወደ ገሹር+ ሄደ፤ አቢሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። 24  ሆኖም ንጉሡ “ወደ ራሱ ቤት ይመለስ፤ ፊቴን እንዳያይ” አለ። በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ራሱ ቤት ተመለሰ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም። 25  መቼም በመልኩ ማማር የአቢሴሎምን ያህል የተወደሰ አንድም ወንድ በመላው እስራኤል አልነበረም። ከእግር ጥፍሩ አንስቶ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ምንም እንከን አይወጣለትም ነበር። 26  የራስ ፀጉሩን ሲቆረጠው ፀጉሩ በቤተ መንግሥቱ የድንጋይ ሚዛን* 200 ሰቅል* ይመዝን ነበር፤ ፀጉሩም በጣም ስለሚከብደው ሁልጊዜ በዓመቱ መጨረሻ ላይ መቆረጥ ነበረበት። 27  አቢሴሎም ትዕማር የምትባል አንዲት ሴት ልጅና ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት።+ ትዕማር በጣም ቆንጆ ነበረች። 28  አቢሴሎምም በኢየሩሳሌም ድፍን ሁለት ዓመት ተቀመጠ፤ ሆኖም የንጉሡን ፊት አላየም።+ 29  በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ንጉሡ ሊልከው ስለፈለገ ኢዮዓብን አስጠራው፤ ኢዮዓብ ግን ወደ እሱ ሳይመጣ ቀረ። ለሁለተኛ ጊዜም ሰው ላከበት፤ እሱ ግን አሁንም ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆነም። 30  በመጨረሻም አቢሴሎም አገልጋዮቹን “የኢዮዓብ እርሻ የሚገኘው ከእኔ እርሻ አጠገብ ነው፤ በእርሻው ላይም የገብስ አዝመራ አለ። ሂዱና እሳት ልቀቁበት” አላቸው። በመሆኑም የአቢሴሎም አገልጋዮች በእርሻው ላይ እሳት ለቀቁበት። 31  በዚህ ጊዜ ኢዮዓብ ተነስቶ ወደ አቢሴሎም ቤት በመምጣት “አገልጋዮችህ እርሻዬን በእሳት ያቃጠሉት ለምንድን ነው?” አለው። 32  አቢሴሎምም ኢዮዓብን እንዲህ አለው፦ “ወደ እኔ ናና ለንጉሡ ‘“ከገሹር የመጣሁት ለምንድን ነው?+ እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር። አሁንም ቢሆን የንጉሡን ፊት ማየት እፈልጋለሁ፤ ጥፋት ከተገኘብኝም ይግደለኝ” ብለህ እንድትነግርልኝ ልላክህ’ ብዬ መልእክት ላክሁብህ።” 33  በመሆኑም ኢዮዓብ ወደ ንጉሡ ገብቶ ይህንኑ ነገረው። ንጉሡም አቢሴሎምን ጠራው፤ አቢሴሎምም ወደ ንጉሡ ገብቶ በንጉሡ ፊት በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ሰገደ። ንጉሡም አቢሴሎምን ሳመው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍስ።”
የዘሯን የመጨረሻ ተስፋ ያመለክታል።
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
ወይም “ከተናገረው ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር ማለት የሚችል አንድም ሰው የለም።”
ይህ የሌሎቹን መለኪያዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚያስችል በቤተ መንግሥት ውስጥ የሚቀመጥ ሚዛን ወይም ከተለመደው ሰቅል የተለየ “ንጉሣዊ” ሰቅል ሳይሆን አይቀርም።
ወደ 2.3 ኪሎ ግራም ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።