ሁለተኛ ሳሙኤል 13:1-39

  • አምኖን ትዕማርን አስነወራት (1-22)

  • አቢሴሎም አምኖንን ገደለው (23-33)

  • አቢሴሎም ወደ ገሹር ሸሸ (34-39)

13  የዳዊት ልጅ አቢሴሎም ትዕማር+ የምትባል ቆንጆ እህት ነበረችው፤ የዳዊት ልጅ አምኖንም+ ወደዳት።  አምኖን በእህቱ በትዕማር ምክንያት በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ታመመ፤ ምክንያቱም ድንግል ስለነበረች በእሷ ላይ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል ሆኖ ተሰምቶት ነበር።  አምኖን፣ ኢዮናዳብ+ የተባለ ጓደኛ ነበረው፤ እሱም የዳዊት ወንድም የሆነው የሺምአህ+ ልጅ ነው፤ ኢዮናዳብም ብልህ ሰው ነበር።  እሱም አምኖንን “አንተ የንጉሥ ልጅ፣ በየቀኑ እንዲህ የምትጨነቀው ለምንድን ነው? ለምን አትነግረኝም?” አለው። አምኖንም “የወንድሜን የአቢሴሎምን እህት+ ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው።  በዚህ ጊዜ ኢዮናዳብ እንዲህ አለው፦ “የታመምክ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ። አባትህም ሊጠይቅህ ሲመጣ ‘እባክህ፣ እህቴ ትዕማር መጥታ ምግብ ትስጠኝ። ለታመመ ሰው የሚሆነውን ምግብ* እዚሁ እያየኋት ታዘጋጅልኝና በእጇ ታጉርሰኝ’ በለው።”  ስለዚህ አምኖን የታመመ መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ። ከዚያም አምኖን ንጉሡን “እባክህ፣ እህቴ ትዕማር ትምጣና እዚሁ እያየኋት ሁለት ቂጣ* ጋግራ በእጇ ታጉርሰኝ” አለው።  ዳዊትም “እባክሽ፣ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ* አዘጋጂለት” ብለው ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤት መልእክት ላከ።  በመሆኑም ትዕማር ወደ ወንድሟ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፤ እሱም እዚያ ተኝቶ ነበር። እሷም ሊጥ ካቦካች በኋላ እዚያው እያየ ጠፍጥፋ ጋገረችው።  ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ ቂጣውን አቀረበችለት። አምኖን ግን ለመብላት ፈቃደኛ አልሆነም፤ እሱም “ሁሉንም ሰው ከዚህ አስወጡልኝ!” አለ። ስለዚህ ሁሉም ሰው ትቶት ወጣ። 10  በዚህ ጊዜ አምኖን ትዕማርን “በእጅሽ እንድታጎርሺኝ ምግቡን* ወደ መኝታ ክፍል አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም የጋገረችውን ቂጣ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወደነበረበት መኝታ ክፍል ገባች። 11  እሷም ምግቡን እንዲበላ ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና “እህቴ ሆይ፣ ነይ፣ አብረሽኝ ተኚ” አላት። 12  እሷ ግን እንዲህ አለችው፦ “ወንድሜ ሆይ፣ ይሄማ ፈጽሞ አይሆንም! እባክህ አታዋርደኝ፤ በእስራኤል ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ተደርጎ አያውቅም።+ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አትፈጽም።+ 13  እኔስ ብሆን ይህን ነውሬን ተሸክሜ እንዴት እኖራለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል ውስጥ ካሉት ወራዳ ሰዎች እንደ አንዱ ትቆጠራለህ። ስለዚህ አሁን፣ እባክህ ንጉሡን አነጋግረው፤ እሱም ቢሆን እኔን አይከለክልህም።” 14  እሱ ግን ሊሰማት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ኃይል ተጠቅሞ በማስነወር አዋረዳት። 15  ከዚያም አምኖን እጅግ በጣም ጠላት፤ ለእሷ ያደረበት ጥላቻም ለእሷ ከነበረው ፍቅር በለጠ። አምኖንም “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት። 16  በዚህ ጊዜ “ወንድሜ ሆይ፣ ይሄማ አይሆንም፤ አሁን እኔን ማባረርህ ቀደም ሲል ከፈጸምክብኝ ነገር የከፋ ይሆናል!” አለችው። እሱ ግን ሊሰማት ፈቃደኛ አልሆነም። 17  ከዚያም አምኖን የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ “እባክህ ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው። 18  (እሷም የሚያምር* ልብስ ለብሳ ነበር፤ ምክንያቱም ድንግል የሆኑት የንጉሡ ሴቶች ልጆች እንዲህ ዓይነት ልብስ ይለብሱ ነበር።) በመሆኑም አገልጋዩ ወደ ውጭ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት። 19  ከዚያም ትዕማር ራሷ ላይ አመድ ነሰነሰች፤+ የለበሰችውንም የሚያምር ቀሚስ ቀደደች፤ በእጇም ራሷን ይዛ እያለቀሰች ሄደች። 20  በዚህ ጊዜ ወንድሟ አቢሴሎም+ “ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበር? እህቴ ሆይ፣ በቃ አሁን ዝም በይ። እንግዲህ እሱ ወንድምሽ ነው።+ ይህን ነገር በልብሽ አታብሰልስዪው” አላት። ከዚያም ትዕማር ከሌሎች ተገልላ በወንድሟ በአቢሴሎም ቤት ተቀመጠች። 21  ንጉሥ ዳዊት የሆነውን ነገር ሁሉ ሲሰማ እጅግ ተቆጣ።+ ሆኖም አምኖን የበኩር ልጁ በመሆኑ በጣም ይወደው ስለነበር ሊያስቀይመው አልፈለገም። 22  አቢሴሎምም አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አልተናገረውም፤ ምክንያቱም አቢሴሎም፣ አምኖን እህቱን ትዕማርን ስላዋረዳት+ ጠልቶት ነበር።+ 23  ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ አቢሴሎም በኤፍሬም+ አቅራቢያ ባለችው በበዓልሃጾር በጎቹን ያሸልት ነበር፤ አቢሴሎምም የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ ጋበዘ።+ 24  በመሆኑም አቢሴሎም ወደ ንጉሡ ገብቶ “አገልጋይህ በጎቹን እያሸለተ ነው። እባክህ፣ ንጉሡና አገልጋዮቹ ከእኔ ጋር ይሂዱ” አለው። 25  ንጉሡ ግን አቢሴሎምን “የእኔ ልጅ፣ ይሄማ አይሆንም! ሁላችንም ከሄድን ሸክም እንሆንብሃለን” አለው። አቢሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ ባረከው። 26  ከዚያም አቢሴሎም “እሺ አንተ ካልሄድክ እባክህ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ”+ አለው። ንጉሡም “ከአንተ ጋር የሚሄደው ለምንድን ነው?” አለው። 27  አቢሴሎም ግን አጥብቆ ለመነው፤ በመሆኑም ዳዊት አምኖንንና የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ ላካቸው። 28  ከዚያም አቢሴሎም አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፣ እኔም አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሞቅ ሲለው ‘አምኖንን ምቱት!’ እላችኋለሁ። እናንተም ትገድሉታላችሁ። አትፍሩ፤ የማዛችሁ እኔ አይደለሁም? በርቱ! ደፋሮች ሁኑ!” 29  በመሆኑም የአቢሴሎም አገልጋዮች በአምኖን ላይ ልክ አቢሴሎም እንዳዘዛቸው አደረጉበት፤ ከዚያም ሌሎቹ የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነስተው በየበቅሏቸው ላይ በመቀመጥ ሸሹ። 30  ገና በመንገድ ላይ ሳሉም ዳዊት “አቢሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ ሰው የለም” የሚል ወሬ ደረሰው። 31  በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተነሳ፤ ልብሱንም ቀዶ መሬት ላይ ተዘረረ፤ አገልጋዮቹም በሙሉ ልብሳቸውን ቀደው አጠገቡ ቆመው ነበር። 32  ሆኖም የዳዊት ወንድም የሺምአህ+ ልጅ የሆነው ኢዮናዳብ+ እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ ወጣቶቹን የንጉሡን ወንዶች ልጆች በሙሉ እንደገደሏቸው አድርጎ አያስብ፤ ምክንያቱም የሞተው አምኖን ብቻ ነው።+ ይህም በአቢሴሎም ትእዛዝ የተፈጸመ ነው፤ እሱ፣ አምኖን እህቱን+ ትዕማርን+ ካስነወረበት ቀን አንስቶ ይህን ነገር ለማድረግ ወስኖ ነበር።+ 33  አሁንም ጌታዬ ንጉሡ ‘የንጉሡ ወንዶች ልጆች በሙሉ አልቀዋል’ ለሚለው ወሬ ጆሮ አይስጥ፤ የሞተው አምኖን ብቻ ነው።” 34  ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሴሎም ሸሸ።+ በኋላም ጠባቂው ቀና ብሎ ሲመለከት ከኋላው ባለው ከተራራው አጠገብ በሚገኘው መንገድ ላይ ብዙ ሰዎች ሲመጡ አየ። 35  በዚህ ጊዜ ኢዮናዳብ+ ንጉሡን “ይኸው፣ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ተመልሰው መጥተዋል። የሆነውም ነገር ልክ አገልጋይህ እንደተናገረው ነው” አለው። 36  እሱም ተናግሮ እንደጨረሰ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያለቀሱ ገቡ፤ ንጉሡና አገልጋዮቹም በሙሉ አምርረው አለቀሱ። 37  አቢሴሎም ግን ኮብልሎ የገሹር ንጉሥ ወደሆነው ወደ አሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ+ ሄደ። ዳዊትም ለልጁ ብዙ ቀናት አለቀሰ። 38  አቢሴሎም ሸሽቶ ወደ ገሹር+ ከሄደ በኋላ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ። 39  በመጨረሻም የንጉሥ ዳዊት ነፍስ አቢሴሎምን ለማየት ናፈቀች፤ ምክንያቱም ዳዊት የአምኖን ሞት ካስከተለበት ሐዘን ተጽናንቶ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የማጽናኛ ምግብ።”
ቃል በቃል “የልብ ቅርጽ ያለው ሁለት ቂጣ።”
ወይም “የማጽናኛ ምግብ።”
ወይም “የማጽናኛ ምግቡን።”
ወይም “ያጌጠ።”