ሁለተኛ ሳሙኤል 10:1-19

  • በአሞናውያንና በሶርያውያን ላይ የተገኘ ድል (1-19)

10  ከጊዜ በኋላ የአሞናውያን+ ንጉሥ ሞተ፤ ልጁ ሃኑንም በእሱ ፋንታ ነገሠ።+  በዚህ ጊዜ ዳዊት “አባቱ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኝ ሁሉ እኔም ለናሃሽ ልጅ ለሃኑን ታማኝ ፍቅር አሳየዋለሁ” አለ። ስለሆነም ዳዊት፣ በአባቱ ሞት ከደረሰበት ሐዘን እንዲያጽናኑት አገልጋዮቹን ወደ ሃኑን ላከ። ሆኖም የዳዊት አገልጋዮች ወደ አሞናውያን ምድር ሲደርሱ  የአሞናውያን መኳንንት ጌታቸውን ሃኑንን “ዳዊት አጽናኞችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃል? ዳዊት አገልጋዮቹን ወደ አንተ የላከው ከተማዋን በሚገባ ለማጥናት፣ ለመሰለልና ለመገልበጥ አይደለም?” አሉት።  በመሆኑም ሃኑን የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ ግማሹን ጢማቸውን ላጫቸው፤+ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ላካቸው።  ዳዊትም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ መልእክተኞችን ወደ ሰዎቹ ላከ፤ ምክንያቱም በኀፍረት ተውጠው ነበር፤ ንጉሡም “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ+ ቆዩ፤ ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።  ውሎ አድሮ አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ጥንብ እንደተቆጠሩ ተገነዘቡ፤ በመሆኑም አሞናውያን፣ ሰዎችን በመላክ ከቤትሬሆብ+ ሶርያውያንና ከጾባህ+ ሶርያውያን 20,000 እግረኛ ተዋጊዎችን፣ የማአካን+ ንጉሥ ከ1,000 ሰዎች ጋር እንዲሁም ከኢሽጦብ* 12,000 ሰዎችን ቀጠሩ።+  ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን እንዲሁም እጅግ ኃያላን የሆኑትን ተዋጊዎቹን+ ጨምሮ መላውን ሠራዊት ላከ።  አሞናውያንም ወጥተው በከተማዋ መግቢያ ላይ ለውጊያ ተሰለፉ፤ የጾባህና የሬሆብ ሶርያውያን ደግሞ ከኢሽጦብና* ከማአካ ጋር ሆነው ለብቻቸው ሜዳ ላይ ተሰለፉ።  ኢዮዓብ ወታደሮቹ ከፊትና ከኋላ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ እሱ እየገሰገሱ መምጣታቸውን ሲያይ በእስራኤል ካሉት ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎች መካከል የተወሰኑትን መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።+ 10  የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ+ አመራር ሥር* ሆነው አሞናውያንን+ እንዲገጥሙ አሰለፋቸው። 11  ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ሶርያውያን ከበረቱብኝ አንተ ትደርስልኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እደርስልሃለሁ። 12  ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ስንል ብርቱና ደፋር መሆን አለብን፤+ ይሖዋም በፊቱ መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋል።”+ 13  ከዚያም ኢዮዓብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሶርያውያንን ለመግጠም ወደ እነሱ ሲገሰግሱ ሶርያውያኑ ከፊታቸው ሸሹ።+ 14  አሞናውያንም ሶርያውያን እንደ ሸሹ ሲያዩ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዋ ገቡ። ከዚያም ኢዮዓብ አሞናውያንን ከመውጋት ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 15  ሶርያውያንም በእስራኤላውያን ድል እንደተመቱ ሲያዩ በአዲስ መልክ ተደራጁ።+ 16  በመሆኑም ሃዳድኤዜር+ በወንዙ*+ አካባቢ ወደነበሩት ሶርያውያን መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም የሃዳድኤዜር ሠራዊት አለቃ በሆነው በሾባክ መሪነት ወደ ሄላም መጡ። 17  ዳዊት ወሬው በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ እስራኤላውያንን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን በመሻገር ወደ ሄላም መጣ። ሶርያውያንም ዳዊትን ለመግጠም ተሰለፉ፤ ከእሱም ጋር ተዋጉ።+ 18  ሆኖም ሶርያውያን ከእስራኤላውያን ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን መካከል 700 ሠረገለኞችንና 40,000 ፈረሰኞችን ገደለ፤ የሠራዊታቸው አለቃ የሆነውን ሾባክንም መታው፤ እሱም እዚያው ሞተ።+ 19  የሃዳድኤዜር አገልጋዮች የሆኑት ነገሥታት በሙሉ እስራኤላውያን እንዳሸነፏቸው ባዩ ጊዜ ወዲያውኑ ከእስራኤላውያን ጋር እርቅ በመፍጠር ለእነሱ ተገዙ፤+ ሶርያውያንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ከጦብ ሰዎች።”
ወይም “ከጦብ ሰዎችና።”
ቃል በቃል “እጅ።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።