አንደኛ ዜና መዋዕል 21:1-30

  • ዳዊት ሕዝቡን በመቁጠር በደል ፈጸመ (1-6)

  • ይሖዋ እስራኤልን መታ (7-17)

  • ዳዊት መሠዊያ ሠራ (18-30)

21  ከዚያም ሰይጣን* እስራኤልን ለማጥቃት ቆርጦ ተነሳ፤ ደግሞም እስራኤልን እንዲቆጥር ዳዊትን አነሳሳው።+  በመሆኑም ዳዊት ኢዮዓብንና+ የሕዝቡን አለቆች “ሂዱና ከቤርሳቤህ አንስቶ እስከ ዳን+ ድረስ ያሉትን እስራኤላውያን ቁጠሩ፤ ከዚያም ቁጥራቸውን አውቅ ዘንድ ንገሩኝ” አላቸው።  ኢዮዓብ ግን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ሕዝቡን 100 እጥፍ ያብዛው! ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ሁሉም የጌታዬ አገልጋዮች አይደሉም? ጌታዬ ይህን ማድረግ ለምን ፈለገ? በእስራኤልስ ላይ ለምን በደል ያመጣል?”  ይሁን እንጂ የንጉሡ ቃል በኢዮዓብ ላይ አየለ። በመሆኑም ኢዮዓብ ወጥቶ በመላው እስራኤል ተጓዘ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።+  ኢዮዓብም የተመዘገበውን የሕዝቡን ቁጥር ለዳዊት ሰጠው። በመላው እስራኤል ሰይፍ የታጠቁ 1,100,000 ወንዶች ነበሩ፤ በይሁዳ ደግሞ ሰይፍ የታጠቁ 470,000 ወንዶች ነበሩ።+  ይሁንና ኢዮዓብ የንጉሡን ቃል ተጸይፎ ስለነበር ሌዊንና ቢንያምን በቆጠራው ውስጥ አላካተተም።+  ይህ ነገር እውነተኛውን አምላክ በጣም አስቆጣው፤ በመሆኑም እስራኤልን መታ።  በዚህ ጊዜ ዳዊት እውነተኛውን አምላክ እንዲህ አለ፦ “ይህን በማድረጌ ከባድ ኃጢአት ፈጽሜአለሁ።+ አሁንም እባክህ የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤+ ታላቅ የሞኝነት ድርጊት ፈጽሜአለሁና።”+  ይሖዋም የዳዊት ባለ ራእይ የሆነውን ጋድን+ እንዲህ አለው፦ 10  “ሂድና ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሦስት ምርጫዎችን ሰጥቼሃለሁ። በአንተ ላይ አመጣብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ።”’” 11  ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ገብቶ እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ምረጥ፤ 12  ለሦስት ዓመት ረሃብ+ ይሁን ወይስ የጠላቶችህ ሰይፍ አሸንፎህ ለሦስት ወራት ጠላቶችህ ጥፋት ያድርሱብህ+ ወይስ ለሦስት ቀናት የይሖዋ ሰይፍ ይኸውም ቸነፈር+ በምድሪቱ ላይ መጥቶ የይሖዋ መልአክ በመላው የእስራኤል ግዛት ጥፋት+ ያምጣ?’ እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አስብበት።” 13  ስለዚህ ዳዊት ጋድን እንዲህ አለው፦ “ሁኔታው በጣም አስጨንቆኛል። ምሕረቱ እጅግ ታላቅ ስለሆነ+ እባክህ በይሖዋ እጅ ልውደቅ፤ ሰው እጅ ላይ ግን አትጣለኝ።”+ 14  ከዚያም ይሖዋ በእስራኤል ላይ ቸነፈር ላከ፤+ በዚህም የተነሳ ከእስራኤል 70,000 ሰዎች ሞቱ።+ 15  በተጨማሪም እውነተኛው አምላክ ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፋ መልአክ ላከ፤ ሆኖም መልአኩ ሊያጠፋት ሲል ይሖዋ ሁኔታውን አይቶ በደረሰው ጥፋት ተጸጸተ፤*+ ስለሆነም የሚያጠፋውን መልአክ “ይብቃ!+ አሁን እጅህን መልስ” አለው። የይሖዋ መልአክ በኢያቡሳዊው+ በኦርናን*+ አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። 16  ዳዊት ቀና ብሎ ሲመለከት የይሖዋ መልአክ በምድርና በሰማያት መካከል ቆሞ አየ፤ እሱም በኢየሩሳሌም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ ነበር።+ ዳዊትና ሽማግሌዎቹ ማቅ+ እንደለበሱ ወዲያውኑ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።+ 17  ዳዊትም እውነተኛውን አምላክ እንዲህ አለ፦ “ሕዝቡ እንዲቆጠር ያዘዝኩት እኔ አይደለሁም? ኃጢአት የሠራሁት እኔ ነኝ፤ በደል የፈጸምኩትም እኔ ነኝ፤+ ታዲያ እነዚህ በጎች ምን አደረጉ? አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፤ በሕዝብህ ላይ ግን ይህን መቅሰፍት አታውርድ።”+ 18  በዚህ ጊዜ የይሖዋ መልአክ፣ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርናን አውድማ ላይ ለይሖዋ መሠዊያ እንዲሠራ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን+ አዘዘው።+ 19  ዳዊትም ጋድ በይሖዋ ስም በነገረው ቃል መሠረት ወጣ። 20  ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦርናን ዞር ሲል መልአኩን አየው፤ ከእሱ ጋር የነበሩት አራት ወንዶች ልጆቹም ተሸሸጉ። በዚህ ጊዜ ኦርናን ስንዴ እየወቃ ነበር። 21  ኦርናን ቀና ብሎ ሲመለከት ዳዊት ወደ እሱ ሲመጣ አየ፤ ወዲያውኑም ከአውድማው ወጥቶ በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ለዳዊት ሰገደ። 22  ዳዊትም ኦርናንን እንዲህ አለው፦ “ለይሖዋ መሠዊያ እንድሠራበት አውድማውን ሽጥልኝ።* በሕዝቡ ላይ የሚወርደው መቅሰፍት እንዲቆም+ ሙሉውን ዋጋ ከፍዬ ልግዛው።” 23  ኦርናን ግን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “በነፃ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሡ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ። እነሆ ከብቶቹን ለሚቃጠል መባ፣ ማሄጃውን*+ ለማገዶ፣ ስንዴውን ደግሞ ለእህል መባ አቀርባለሁ። ሁሉንም ነገር እኔ እሰጣለሁ።” 24  ይሁን እንጂ ንጉሥ ዳዊት ኦርናንን እንዲህ አለው፦ “በፍጹም አይሆንም! ሙሉውን ዋጋ ሰጥቼ እገዛዋለሁ፤ ምክንያቱም የአንተ የሆነውን ነገር ወስጄ ለይሖዋ አልሰጥም ወይም ምንም ያልከፈልኩበትን ነገር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም።”+ 25  በመሆኑም ዳዊት የቦታውን ዋጋ 600 የወርቅ ሰቅል* መዝኖ ለኦርናን ሰጠው። 26  ዳዊትም በዚያ ለይሖዋ መሠዊያ+ ሠርቶ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችና የኅብረት መሥዋዕቶች አቀረበ፤ የይሖዋንም ስም ጠራ፤ እሱም የሚቃጠል መባ በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ከሰማያት በእሳት+ መለሰለት። 27  ከዚያም ይሖዋ መልአኩን+ ሰይፉን ወደ ሰገባው እንዲመልስ አዘዘው። 28  በዚህ ጊዜ ዳዊት፣ ይሖዋ በኢያቡሳዊው በኦርናን አውድማ መልስ እንደሰጠው ባየ ጊዜ በዚያ ቦታ ላይ መሥዋዕት ማቅረቡን ቀጠለ። 29  ሆኖም ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የይሖዋ የማደሪያ ድንኳንና የሚቃጠል መባ የሚቀርብበት መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባኦን ባለው ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይገኝ ነበር።+ 30  ይሁንና ዳዊት ከይሖዋ መልአክ ሰይፍ የተነሳ እጅግ ፈርቶ ስለነበር አምላክን ለመጠየቅ ወደዚያ መሄድ አልቻለም።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ተቃዋሚ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
በ2ሳሙ 24:16 ላይ አረውና ተብሎም ተጠርቷል።
ወይም “አዘነ።”
ቃል በቃል “ስጠኝ።”
ጥርስ መሳይ ጉጦች ያሉት የእህል መውቂያ።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።