አንደኛ ዜና መዋዕል 17:1-27
17 ዳዊት በራሱ ቤት* መኖር እንደጀመረ ነቢዩ ናታንን+ “የይሖዋ የቃል ኪዳኑ ታቦት በድንኳን ውስጥ ተቀምጦ+ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ+ በተሠራ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው” አለው።
2 ናታንም ዳዊትን “እውነተኛው አምላክ ከአንተ ጋር ስለሆነ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው።
3 በዚያው ሌሊት የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፦
4 “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።+
5 እስራኤልን ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱም የማደሪያ ድንኳን ወደ ሌላው የማደሪያ ድንኳን* እሄድ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም።+
6 ከመላው እስራኤል ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ ሁሉ ሕዝቤን እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው የእስራኤል ፈራጆች መካከል ‘በአርዘ ሊባኖስ፣ ቤት ያልሠራህልኝ ለምንድን ነው?’ ያልኩት ማን አለ?” ’
7 “አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን መንጋ ከምትጠብቅበት ስፍራ ወሰድኩህ።+
8 እኔም በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋለሁ፤+ ስምህንም በምድር ላይ እንዳሉ ታላላቅ ሰዎች ስም አደርገዋለሁ።+
9 ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ተረጋግተው እንዲቀመጡም አደርጋለሁ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም የሚረብሻቸው አይኖርም፤ ክፉዎችም እንደቀድሞው ዳግመኛ አይጨቁኗቸውም፤*+
10 በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን ከሾምኩበት+ ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ እንደነበሩት አያደርጉባቸውም። ጠላቶቻችሁም ሁሉ እንዲገዙላችሁ አደርጋለሁ።+ በተጨማሪም ‘ይሖዋ ቤት እንደሚሠራልህ’* እነግርሃለሁ።
11 “ ‘ “የሕይወት ዘመንህ አብቅቶ ከአባቶችህ ጋር ለመሆን በምትሄድበት ጊዜ ከአንተ በኋላ ዘርህን ይኸውም ከወንዶች ልጆችህ መካከል አንዱን አስነሳለሁ፤+ ንግሥናውንም አጸናለሁ።+
12 ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው፤+ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ።+
13 አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል።+ ታማኝ ፍቅሬንም ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደወሰድኩ+ ከእሱ ላይ አልወስድም።+
14 በቤቴና በንጉሣዊ ግዛቴ ላይ ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር አደርገዋለሁ፤+ ዙፋኑም ለዘላለም ይዘልቃል።” ’ ”+
15 ናታንም ይህን ቃል ሁሉና ይህን ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው።
16 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ገብቶ በይሖዋ ፊት ተቀመጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ኧረ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝስ ቤቴ ምን ስለሆነ ነው?+
17 አምላክ ሆይ፣ ይህ ሳያንስ ስለ አገልጋይህ ቤት ገና ወደፊት የሚሆነውንም ነገር ተናገርክ፤+ ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ከዚህ በላይ ከፍ ከፍ ሊደረግ እንደሚገባ ሰው* አድርገህ ተመልክተኸኛል።
18 ስለሰጠኸኝ ክብር አገልጋይህ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? አንተ አገልጋይህን በሚገባ ታውቀው የለ?+
19 ይሖዋ ሆይ፣ ለአገልጋይህ ስትል፣ ከልብህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ* ታላቅነትህን በመግለጥ እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ነገሮች ፈጽመሃል።+
20 ይሖዋ ሆይ፣ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤+ ከአንተ በቀር አምላክ የለም፤+ በጆሯችን የሰማነው ነገር ሁሉ ይህን ያረጋግጣል።
21 በምድር ላይ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ሌላ ብሔር ማን አለ?+ እውነተኛው አምላክ ሄዶ ሕዝቡ አድርጎ ዋጀው።+ ብሔራትን ከግብፅ ከዋጀኸው ሕዝብህ ፊት አባረህ+ ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በመፈጸም ስምህን አስጠራህ።+
22 ሕዝብህን እስራኤልን እስከ ወዲያኛው የራስህ ሕዝብ አደረግከው፤+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተም አምላኩ ሆንክ።+
23 አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህንና ቤቱን በተመለከተ የገባኸው ቃል እስከ ወዲያኛው የጸና ይሁን፤ ቃል እንደገባኸውም አድርግ።+
24 ሰዎች ‘የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ለእስራኤል አምላክ ነው’ እንዲሉ ስምህ የጸና* ይሁን፤ ደግሞም ለዘላለም ከፍ ከፍ ይበል፤+ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።+
25 አምላኬ ሆይ፣ አንተ ለአገልጋይህ ቤት የመሥራት* ዓላማ እንዳለህ አሳውቀኸዋልና። አገልጋይህ ይህን ጸሎት በልበ ሙሉነት ወደ አንተ የሚያቀርበው በዚህ ምክንያት ነው።
26 አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ እውነተኛው አምላክ አንተ ነህ፤ ለአገልጋይህም እነዚህን መልካም ነገሮች ለማድረግ ቃል ገብተህለታል።
27 በመሆኑም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በፊትህም ለዘላለም የጸና ይሁን፤ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ቀድሞውንም ባርከኸዋልና፤ ለዘላለምም የተባረከ ይሆናል።”
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ቤተ መንግሥት።”
^ “ከአንዱ የድንኳን ስፍራ ወደ ሌላው፣ ከአንዱም የመኖርያ ቦታ ወደ ሌላው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “አያደክሟቸውም።”
^ ወይም “ሥርወ መንግሥት እንደሚያቋቁምልህ።”
^ ወይም “ትልቅ ቦታ እንዳለው ሰው።”
^ ወይም “ከፈቃድህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ።”
^ ወይም “የታመነ።”
^ ወይም “ሥርወ መንግሥት የማቋቋም።”