አንደኛ ዜና መዋዕል 10:1-14

  • ሳኦልና ሦስት ወንዶች ልጆቹ ሞቱ (1-14)

10  ፍልስጤማውያንም ከእስራኤል ጋር እየተዋጉ ነበር። የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጤማውያን ፊት ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦአ ተራራ ላይ ተገደሉ።+  ፍልስጤማውያን ሳኦልንና ወንዶች ልጆቹን እግር በእግር ተከታተሏቸው፤ ፍልስጤማውያንም የሳኦልን ወንዶች ልጆች ዮናታንን፣ አቢናዳብንና ሜልኪሳን+ መተው ገደሏቸው።  ውጊያው በሳኦል ላይ በረታ፤ ቀስተኞቹም አገኙት፤ ደግሞም አቆሰሉት።+  ከዚያም ሳኦል ጋሻ ጃግሬውን “እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች መጥተው በጭካኔ እንዳያሠቃዩኝ+ ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለነበር ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም ሳኦል ሰይፉን ወስዶ በላዩ ላይ ወድቆ ሞተ።+  ጋሻ ጃግሬው ሳኦል መሞቱን ሲያይ እሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ሞተ።  ስለዚህ ሳኦልም ሆነ ሦስት ወንዶች ልጆቹ ሞቱ፤ የቤቱም ሰዎች ሁሉ አብረው ሞቱ።+  በሸለቆው ውስጥ የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ሠራዊቱ መሸሹን እንዲሁም ሳኦልና ልጆቹ መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ጥለው ሸሹ፤ ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው ከተሞቹን ያዙ።  በማግስቱ ፍልስጤማውያን የሞቱትን ሰዎች ልብስና ትጥቅ ለመግፈፍ ሲመጡ ሳኦልንና ወንዶች ልጆቹን በጊልቦአ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው።+  ስለሆነም ሳኦልን ገፈፉት፤ ራሱን ከቆረጡና የጦር ትጥቁን ከወሰዱ በኋላ ወሬው ለጣዖቶቻቸውና+ ለሕዝቡ እንዲዳረስ ወደ ፍልስጤም ምድር ሁሉ መልእክት ላኩ። 10  ከዚያም የጦር ትጥቁን በአምላካቸው ቤት አስቀመጡት፤ ራሱን ደግሞ በዳጎን ቤት+ ላይ ቸነከሩት። 11  በጊልያድ በምትገኘው በኢያቢስ+ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ፍልስጤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ ሲሰሙ+ 12  ተዋጊዎቹ ሁሉ ተነሱ፤ የሳኦልንና የልጆቹንም አስከሬን ተሸክመው ወደ ኢያቢስ አመጡ። ከዚያም አፅማቸውን በኢያቢስ በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤+ ለሰባት ቀንም ጾሙ። 13  ስለዚህ ሳኦል ለይሖዋ ታማኝ ሳይሆን በመቅረቱ ሞተ፤ ምክንያቱም የይሖዋን ቃል አልታዘዘም፤+ ደግሞም መናፍስት ጠሪን አማከረ፤+ 14  ይሖዋንም አልጠየቀም። ስለሆነም ለሞት አሳልፎ ሰጠው፤ ንግሥናውም ለእሴይ ልጅ ለዳዊት እንዲተላለፍ አደረገ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች