አንደኛ ሳሙኤል 6:1-21

  • ፍልስጤማውያን ታቦቱን ወደ እስራኤል መለሱ (1-21)

6  የይሖዋ ታቦት+ በፍልስጤማውያን ምድር ሰባት ወር ቆየ።  ፍልስጤማውያኑም ካህናትንና ሟርተኞችን+ ጠርተው “የይሖዋን ታቦት ምን ብናደርገው ይሻላል? ወደ ስፍራው እንዴት እንደምንመልሰው አሳውቁን” አሏቸው።  እነሱም እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦ “የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት የምትመልሱ ከሆነ ያለመባ እንዳትመልሱት። ከበደል መባ ጋር አድርጋችሁ ወደ እሱ መመለስ ይኖርባችኋል።+ የምትፈወሱት እንዲህ ካደረጋችሁ ብቻ ነው፤ ደግሞም እጁ ከእናንተ ላይ ያልተመለሰው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ።”  ስለዚህ “ወደ እሱ መላክ የሚኖርብን የበደል መባ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። እነሱም እንዲህ አሏቸው፦ “እናንተንም ሆነ ገዢዎቻችሁን ያሠቃየው መቅሰፍት ተመሳሳይ ስለሆነ በፍልስጤም ገዢዎች+ ቁጥር ልክ አምስት የወርቅ ኪንታሮቶችንና* አምስት የወርቅ አይጦችን ላኩ።  ምድሪቱን እያጠፉ ባሉት ኪንታሮቶቻችሁና አይጦቻችሁ+ አምሳያ ምስሎችን ሥሩ፤ የእስራኤልንም አምላክ አክብሩ። ምናልባትም በእናንተ፣ በአምላካችሁና በምድራችሁ ላይ የከበደውን እጁን ያቀልላችሁ ይሆናል።+  ግብፅና ፈርዖን ልባቸውን እንዳደነደኑት እናንተም ለምን ልባችሁን ታደነድናላችሁ?+ እሱ ክፉኛ በቀጣቸው+ ጊዜ እስራኤላውያንን ለቀቋቸው፤ እነሱም ሄዱ።+  ስለዚህ አሁን አዲስ ሠረገላ እንዲሁም እንቦሶች ያሏቸውና ቀንበር ያልተጫነባቸው ሁለት ላሞች አዘጋጁ። ከዚያም ሠረገላውን ጥመዱባቸው፤ እንቦሶቻቸውን ግን ከእነሱ ነጥላችሁ ወደ ቤት መልሷቸው።  የይሖዋን ታቦት ወስዳችሁ ሠረገላው ላይ አስቀምጡት፤ እንዲሁም ለእሱ የበደል መባ አድርጋችሁ የምትልኳቸውን የወርቅ ምስሎች በሣጥን አድርጋችሁ ታቦቱ አጠገብ አስቀምጡ።+ ከዚያም መንገዱን ይዞ እንዲሄድ ላኩት፤  ልብ ብላችሁም ተመልከቱ፦ ታቦቱ ወደ አገሩ ወደ ቤትሼሜሽ+ የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ከሄደ ይህን ታላቅ መከራ ያመጣብን እሱ ነው ማለት ነው። ካልሆነ ግን የእሱ እጅ እንዳልመታን እናውቃለን፤ ይህ የደረሰብንም እንዲያው በአጋጣሚ ነው።” 10  ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ። እንቦሶች ያሏቸውን ሁለት ላሞች ወስደው ሠረገላውን ጠመዱባቸው፤ እንቦሶቹንም በረት ውስጥ ዘጉባቸው። 11  ከዚያም የይሖዋን ታቦት እንዲሁም የወርቅ አይጦቹንና የኪንታሮቶቻቸውን ምስል የያዘውን ሣጥን ሠረገላው ላይ ጫኑ። 12  ላሞቹም ወደ ቤትሼሜሽ በሚወስደው መንገድ ቀጥ ብለው ሄዱ።+ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳይሉ አንዱን ጎዳና ተከትለው ‘እምቧ’ እያሉ ተጓዙ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ የፍልስጤም ገዢዎች እስከ ቤትሼሜሽ ድንበር ድረስ ከኋላ ከኋላቸው ይከተሏቸው ነበር። 13  የቤትሼሜሽ ሰዎች በሸለቋማው ሜዳ* ላይ ስንዴ እያጨዱ ነበር። እነሱም ቀና ብለው ታቦቱን ተመለከቱ፤ እሱን በማየታቸውም በጣም ተደሰቱ። 14  ሠረገላውም ወደ ቤትሼሜሻዊው ኢያሱ ማሳ ገብቶ እዚያ በሚገኝ አንድ ትልቅ ዓለት አጠገብ ቆመ። ሰዎቹም የሠረገላውን እንጨት ፈልጠው ላሞቹን+ ለይሖዋ የሚቃጠል መባ አድርገው አቀረቡ። 15  ሌዋውያኑም+ የይሖዋን ታቦትና አብሮት የነበረውን የወርቅ ምስሎቹን የያዘውን ሣጥን አውርደው በትልቁ ዓለት ላይ አስቀመጧቸው። በዚያም ቀን የቤትሼሜሽ+ ሰዎች ለይሖዋ የሚቃጠሉ መባዎችን አቀረቡ፤ መሥዋዕቶችንም ሠዉ። 16  አምስቱ የፍልስጤም ገዢዎችም ይህን ሲያዩ በዚያው ቀን ወደ ኤቅሮን ተመለሱ። 17  ፍልስጤማውያን ለይሖዋ የበደል መባ አድርገው የላኳቸው የወርቅ ኪንታሮቶች እነዚህ ናቸው፦+ ለአሽዶድ+ አንድ፣ ለጋዛ አንድ፣ ለአስቀሎን አንድ፣ ለጌት+ አንድ እንዲሁም ለኤቅሮን+ አንድ። 18  የወርቅ አይጦቹ ቁጥር አምስቱ የፍልስጤም ገዢዎች በሚያስተዳድሯቸው ከተሞች ሁሉ ይኸውም በተመሸጉት ከተሞችና በሥራቸው በሚገኙ አውላላ ሜዳ ላይ ባሉ መንደሮች ቁጥር ልክ ነበር። የይሖዋን ታቦት ያስቀመጡበት በቤትሼሜሻዊው ኢያሱ ማሳ ውስጥ የሚገኘው ትልቅ ዓለት እስከ ዛሬ ድረስ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል። 19  ይሁንና አምላክ የይሖዋን ታቦት ስለተመለከቱ የቤትሼሜሽን ሰዎች መታቸው። ከሕዝቡ መካከል 50,070 ሰዎችን* መታ፤ ሰዎቹም ይሖዋ ብዙ ሕዝብ ስለፈጀባቸው ያለቅሱ ጀመር።+ 20  በመሆኑም የቤትሼሜሽ ሰዎች “ታዲያ በዚህ ቅዱስ አምላክ+ በይሖዋ ፊት ማን ሊቆም ይችላል? ምናለ ከእኛ ላይ ዞር ቢልና ወደ ሌሎች ቢሄድ?” አሉ።+ 21  ስለዚህ ወደ ቂርያትየአሪም+ ነዋሪዎች መልእክተኞችን ልከው “ፍልስጤማውያን የይሖዋን ታቦት መልሰዋል። ወደዚህ ውረዱና ይዛችሁት ውጡ” አሏቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የፊንጢጣ ኪንታሮቶችንና።”
ወይም “በረባዳማው ሜዳ።”
ቃል በቃል “70 ሰዎችን፣ 50,000 ሰዎችን።”