አንደኛ ሳሙኤል 4:1-22

  • ፍልስጤማውያን ታቦቱን ማረኩ (1-11)

  • ኤሊና ልጆቹ ሞቱ (12-22)

4  የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ ደረሰ። ከዚያም እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ለመዋጋት ወጡ፤ ኤቤንዔዘርም አጠገብ ሰፈሩ፤ ፍልስጤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፍረው ነበር።  ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለመግጠም ተሰልፈው ወጡ፤ ውጊያውም እየተፋፋመ ሄደ፤ እስራኤላውያንም ውጊያው በተደረገበት ግንባር 4,000 ሰው በገደሉባቸው በፍልስጤማውያን ድል ተመቱ።  ሠራዊቱ ወደ ሰፈሩ በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ አሉ፦ “ይሖዋ በዛሬው ዕለት በፍልስጤማውያን ፊት ድል እንድንመታ የፈቀደው ለምንድን ነው?*+ አብሮን እንዲሆንና ከጠላቶቻችን እጅ እንዲያድነን የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከሴሎ ይዘነው እንሂድ።”+  በመሆኑም ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ላከ፤ እነሱም ከኪሩቤል በላይ* ዙፋን ላይ የተቀመጠውን+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ከዚያ ተሸክመው መጡ። ሁለቱ የኤሊ ልጆች ሆፍኒ እና ፊንሃስም+ ከእውነተኛው አምላክ የቃል ኪዳን ታቦት ጋር አብረው ነበሩ።  የይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈሩ ሲገባ እስራኤላውያን ሁሉ ምድር እስክትናወጥ ድረስ ጮኹ።  ፍልስጤማውያንም ጩኸቱን ሲሰሙ “በዕብራውያን ሰፈር የሚሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” አሉ። በመጨረሻም የይሖዋ ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አወቁ።  ፍልስጤማውያንም “አምላክ ወደ ሰፈሩ ገብቷል!”+ በማለት በፍርሃት ተዋጡ። በመሆኑም እንዲህ አሉ፦ “ወየው ጉዳችን! እንዲህ ዓይነት ነገር ሆኖ አያውቅም!  ወየው ጉዳችን! ከዚህ ባለ ግርማ አምላክ እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በተለያዩ መቅሰፍቶች የመታቸው አምላክ እኮ ይህ ነው።+  እናንተ ፍልስጤማውያን አይዟችሁ፣ ወንድነታችሁን አሳዩ፤ አለዚያ ዕብራውያን የእናንተ አገልጋዮች እንደነበሩ ሁሉ እናንተም የእነሱ አገልጋዮች ትሆናላችሁ።+ ወንድነታችሁን አሳዩ፤ ተዋጉ!” 10  በመሆኑም ፍልስጤማውያን ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ድል ተመቱ፤+ እያንዳንዱም ሰው ወደየድንኳኑ ሸሸ። በጣም ብዙ ሕዝብ አለቀ፤ ከእስራኤላውያንም ወገን 30,000 እግረኛ ወታደር ሞተ። 11  የአምላክም ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱ የኤሊ ልጆች ሆፍኒ እና ፊንሃስም ሞቱ።+ 12  አንድ ቢንያማዊ ልብሱን ቀዶና በራሱ ላይ አቧራ ነስንሶ+ ከጦር ግንባሩ እየሮጠ በዚያው ቀን ሴሎ ደረሰ። 13  ሰውየውም ሲደርስ ኤሊ በእውነተኛው አምላክ ታቦት+ የተነሳ ልቡ ስለተረበሸ መንገድ ዳር ወንበር ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር። ሰውየውም ወሬውን ለመንገር ወደ ከተማዋ ገባ፤ መላ ከተማዋም በጩኸት ትናወጥ ጀመር። 14  ኤሊም ጩኸቱን ሲሰማ “ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድን ነው?” በማለት ጠየቀ። ሰውየውም በፍጥነት ወደ እሱ ሄዶ ወሬውን ነገረው። 15  (በዚህ ወቅት ኤሊ ዕድሜው 98 ዓመት ነበር፤ ኤሊ ማየት ተስኖት የነበረ ቢሆንም ዓይኖቹ ፊት ለፊት ትኩር ብለው ይመለከቱ ነበር።)+ 16  ከዚያም ሰውየው ኤሊን “ከጦር ግንባሩ የመጣሁት ሰው እኔ ነኝ! ከጦር ግንባሩ ሸሽቼ የመጣሁትም ዛሬ ነው” አለው። በዚህ ጊዜ ኤሊ “ልጄ፣ ለመሆኑ የተከሰተው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 17  ወሬውን ያመጣውም ሰው እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ፊት ሸሽተዋል፤ ሕዝቡም ከፍተኛ ሽንፈት ደርሶበታል፤+ ሁለቱ ልጆችህ ሆፍኒ እና ፊንሃስም ሞተዋል፤+ የእውነተኛው አምላክ ታቦትም ተማርኳል።”+ 18  ሰውየው ስለ እውነተኛው አምላክ ታቦት በተናገረበት ቅጽበት ኤሊ በሩ አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ወደኋላው ወደቀ፤ በዕድሜ የገፋ ከመሆኑም ሌላ ሰውነቱ ከባድ ስለነበር አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እሱም ለ40 ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆኖ አገልግሏል። 19  የኤሊ ምራት የፊንሃስ ሚስት ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር። እሷም የእውነተኛው አምላክ ታቦት እንደተማረከ እንዲሁም አማቷና ባሏ እንደሞቱ ስትሰማ ሆዷን ይዛ ጎንበስ አለች፤ ድንገትም ምጥ ያዛትና ወለደች። 20  እሷም ልትሞት በምታጣጥርበት ጊዜ አጠገቧ ቆመው የነበሩት ሴቶች “አይዞሽ፣ ወንድ ልጅ ወልደሻል” አሏት። እሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብም አላለችውም። 21  ሆኖም የእውነተኛው አምላክ ታቦት በመማረኩ እንዲሁም በአማቷና በባሏ ላይ በደረሰው ነገር+ የተነሳ “ክብር ከእስራኤል በግዞት ተወሰደ”+ ስትል ለልጁ ኢካቦድ*+ የሚል ስም አወጣችለት። 22  “የእውነተኛው አምላክ ታቦት ስለተማረከ ክብር ከእስራኤል በግዞት ተወሰደ”+ አለች።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ይሖዋ ድል ያደረገን ለምንድን ነው?”
“መካከል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ክብሩ የት አለ?” የሚል ትርጉም አለው።