አንደኛ ሳሙኤል 3:1-21

  • ሳሙኤል ነቢይ ሆነ (1-21)

3  ይህ በእንዲህ እንዳለ ብላቴናው ሳሙኤል በኤሊ ፊት ይሖዋን ያገለግል ነበር፤+ ይሁን እንጂ በዚያ ዘመን ከይሖዋ የሚመጣ ቃል ብርቅ ነበር፤ ራእይ+ ማየትም ቢሆን ብዙ የተለመደ አልነበረም።  አንድ ቀን ኤሊ የተለመደው ቦታው ላይ ተኝቶ ነበር፤ ዓይኖቹ ስለደከሙ ማየት ተስኖታል።+  የአምላክም መብራት+ ገና አልጠፋም፤ ሳሙኤልም የአምላክ ታቦት ባለበት የይሖዋ ቤተ መቅደስ*+ ውስጥ ተኝቶ ነበር።  ከዚያም ይሖዋ ሳሙኤልን ጠራው። እሱም “አቤት” አለ።  ወደ ኤሊም እየሮጠ ሄዶ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። እሱ ግን “አይ፣ አልጠራሁህም። ተመልሰህ ተኛ” አለው። በመሆኑም ሄዶ ተኛ።  ይሖዋም እንደገና “ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። እሱ ግን “ኧረ አልጠራሁህም ልጄ። ተመልሰህ ተኛ” አለው።  (ሳሙኤል ይሖዋን ገና አላወቀውም ነበር፤ የይሖዋም ቃል ቢሆን ገና አልተገለጠለትም ነበር።)+  በመሆኑም ይሖዋ ለሦስተኛ ጊዜ እንደገና “ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። እሱም ተነስቶ ወደ ኤሊ በመሄድ “አቤት፣ ጠራኸኝ?” አለው። ኤሊም ብላቴናውን እየጠራው ያለው ይሖዋ መሆኑን አስተዋለ።  በመሆኑም ኤሊ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሂድና ተኛ፤ እንደገና ከጠራህ ‘ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ እየሰማ ስለሆነ ተናገር’ በል።” ሳሙኤልም ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ። 10  ይሖዋም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ እንደ ሌላው ጊዜም “ሳሙኤል፣ ሳሙኤል!” ሲል ጠራው። ሳሙኤልም “አገልጋይህ እየሰማ ስለሆነ ተናገር” አለ። 11  ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚሰቀጥጥ ነገር በእስራኤል ውስጥ አደርጋለሁ።+ 12  በዚያ ቀን ስለ ኤሊ ቤት የተናገርኩትን ነገር ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በእሱ ላይ እፈጽማለሁ።+ 13  እሱ በሚያውቀው ጥፋት የተነሳ በቤቱ ላይ ለዘለቄታው እንደምፈርድ ንገረው፤+ ምክንያቱም ልጆቹ አምላክን ረግመዋል፤+ እሱ ግን አልገሠጻቸውም።+ 14  በዚህም የተነሳ የኤሊ ቤት የፈጸመው ጥፋት መሥዋዕት ወይም መባ በማቅረብ ፈጽሞ እንደማይሰረይ ለኤሊ ቤት ምያለሁ።”+ 15  ሳሙኤልም እስከ ንጋት ድረስ ተኛ፤ ከዚያም የይሖዋን ቤት በሮች ከፈተ። ሳሙኤል ራእዩን ለኤሊ መንገር ፈርቶ ነበር። 16  ኤሊ ግን ሳሙኤልን ጠርቶ “ልጄ፣ ሳሙኤል!” አለው። እሱም “አቤት” አለው። 17  ኤሊም እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ለመሆኑ የነገረህ መልእክት ምንድን ነው? እባክህ አትደብቀኝ። እሱ ከነገረህ ነገር ውስጥ አንዲት ቃል እንኳ ብትደብቀኝ አምላክ እንዲህ ያድርግብህ፤ ከዚያም የከፋ ነገር ያምጣብህ።” 18  በመሆኑም ሳሙኤል እሱ የነገረውን በሙሉ ምንም ሳይደብቅ ነገረው። ኤሊም “ይህ ከይሖዋ ነው። እሱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ” አለ። 19  ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር፤+ የሚናገረውም ቃል ሁሉ እንዲፈጸም ያደርግ* ነበር። 20  ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እስራኤላውያን በሙሉ ሳሙኤል ተቀባይነት ያገኘ የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ ተገነዘቡ። 21  ይሖዋም በሴሎ ይገለጥ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ በሴሎ በይሖዋ ቃል አማካኝነት ራሱን ለሳሙኤል ገልጦለት ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

የመገናኛ ድንኳኑን ያመለክታል።
ቃል በቃል “መሬት ጠብ እንዲል አያደርግም።”